1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶርያ አማፅያን ይዞታ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 12 2004

ሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በመንግስት ዋና ፅሕፈት ቤት አቅራቢያ ግጭት መቀስቀሱን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ኗሪዎችና የአይን ምስክሮችን የጠቀሰዉ የሮይተርስ ዘገባ እንዳመለከተዉ ደማስቆ ዉስጥ መንገዶችን በመዘጋጋት መሳሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ያስከተሉ

https://p.dw.com/p/15bBl
ምስል dapd/Shaam

የፕሬዝደንት በሽር አልአሰድ ታማኞች ላይ አማፅያን ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ግጭቱ ተባብሷል። አማፅያኑ መዲናዋን የመቆጣጠር ዓላማ እንዳላቸዉ ተናግረዋል። ትናንት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ህይወት የቀጠፈዉ የአማፅያኑ ጥቃትም የስኬታቸዉ ተምሳሌት ነዉ ባይ ናቸዉ በዶቼ ቬለ የመካከለኛዉ ምስራቅ ተንታኝ ፎልከር ፔርተዝ።

ትናንት ደማስቆ ዉስጥ የደረሰዉ የቦምብ ጥቃት የፕሬዝደንት በሽር አልአሰድ አማቻችን ጨምሮ ሶስት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ህይወት አጥፍቷል። ከሟቾቹ አንዱ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል አዶድ ራያህ መሆናቸዉ ይፋ ሲሆን የሶርያ ነፃ ጦር ኃይል ኃላፊነቱን ወስዷል። ቻይና ማንኛዉም ወገን የሚፈፅመዉን የሽብር ተግባር በመቃወም ጥቃቱን አዉግዛለች።

Themenbild Spezialseite Unruhen in Syrien Farsi
ምስል Reuters

ከእሁድ አንስቶ በሶሪያዋ ዋና ከተማ በተባባሰዉ ጦርነት ምክንያት በርካታ ኗሪዎች ሽሽት መጀመራቸዉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። በዉጊያና ግጭቱም በደማስቆ ከተማ አካባቢ እስካሁን የ78 በራሷ በመዲናዋ ደግሞ የ38 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተነግሯል። የመንግስት ኃይሎች የከተማዋ ኗሪዎች በ48 ሰዓታት ዉስጥ እንዲወጡ የሚል የጊዜ ገደብ ዛሬ መስጠታቸዉ ተገልጿል። አመፅና ተቃዉሞ ያየለበት የፕሬዝደንት አልአሰድ መንግስት እዉነታዉ አልተገለፀለትም ይላሉ  የመካከለኛዉ ምስራቅ ተንታኝ ፎልከር ፔርተዝ፤

 «ባለፉት ቀናት የአገዛዙ ዋና አካላት ሲከዱ ታይቷል። ባለፈዉ ግማሽ ዓመት እንደታየው ማለት ነዉ። አብዮቱ ከተቀጣጠለ አንስቶ ታዛቢዎች አገዛዙ በመጨረሻ ወደተጨባጩ እዉነታ ይመጣል ብለዉ ነበር። ሆኖም አገዛዙ በዚህ ረዥም ጊዜ ዉስጥ ይህን ያወቀ አይመስልም ወይም ለማወቅ አልፈለገም።»

አማፅያኑ በደማስቆ የቀጠሉት የተጠናከረ ዉጊያ እና የትናንቱ የቦምብ ጥቃት በአልአሰድ መንግስት ባለስልጣናት ከሥራ መልቀቅ ታጅቧል። ፎልከር ፔርተዝ  እንደሚሉት ከሆነም ይህ የአማፅያኑ ስኬት ተምሳሌት ነዉ።

«እንደእዉነቱ ከሆነ እስካሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ሥራቸዉን አልለቀቁም። ሌላዉ ቀርቶ በጀነራልነት ማዕረግ የሚገኙ መኮንኖችም መክዳታቸዉ አልተሰማም። ይህ ግን በመጪዉ ጥቂት ቀናት ሊቀየር ይችል ይሆናል። ከቅርብ ባለስልጣናት የበሽር አልአሰድ ጓደኛ የሆኑት ማናፍ ትላስ ሥራቸዉን ለቀዋል። የትላስ አባት በሃፊዝ አልአሰድ ዘመነ ሥልጣን የመከላከያ ሚኒስትር ነበሩ። አሁን ትላስ ለአገዛዙ ጀርባቸዉን በመስጠት አዲስ መንግስት ለመመሥረት ፈቃደኝነታቸዉን ገልፀዋል። በኢራቅ የሶርያ አምባሳደር አቅጣጫቸዉን ቀይረዋል። አሁን በማዕከላዊ ሥልጣኑ አካባቢ ትልቅ የደህንነት ክፍተት አለ። ይህም ለአማፂያኑ ወቅቱን የስኬታቸዉ ተምሳሌት ያደርገዋል።» 

Militär in Syrien Assad Soldaten Damaskus Bürgerkrieg LKW
ምስል AP

ከዚህ በመነሳት በአጭር ቀናት ሊከተሉ ስለሚችሉ ሁኔታዎች ፔርተዝ ሲናገሩ፤

«ጥቃቱ ከሁለቱም ወገን ይጠናከራል። አገዛዙ እስካሁን ጥቃቱን አጠናክሮ በመቀጠል የአመፁን እንቅስቃሴ እቆጣጠራለሁ የሚል እምነት አለዉ። አማፅያኑ በበኩላቸዉ ከቀን ወደቀን በግጭቱ አሸናፊ ሆነዉ እንደሚወጡ እያረጋገጡ ነዉ። ያለፉት ጥቂት ቀናት ስኬቶች እምነታቸዉን አጠናክሮላቸዋል። ነገር ግን አንዳቸዉም በድርድር መፍትሄ ለማምጣት አልፈለጉም። በድርድሩ ቢያንስ አንዱ ወገን፤ ሲሆን ሁለቱም ድልን ሊያገኙ እንደሚችሉ አላስተዋሉም።»

ኬርሽተን ክኒፕ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ