የሶሪያ አማፅያንን ማስታጠቅና ዉዝግቡ
ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2005
የሶሪያ አማፅያን ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የጦር መሣሪያ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አጥብቀው ያሳስባሉ ። አሜሪካንን የመሳሰሉ አንዳንድ ምዕራባውያን ሃገራት አማፅያኑን ሊያስታጥቋቸው አቅደዋል ። ይህ እርምጃ ግን በእጅጉ እየተተቸ ነው ። ብዙዎች የጦር መሣሪያዎቹ የማይፈለጉ ወገኖች እጅ መግባታቸው አይቀርም የሚል ስጋት አላቸው ። የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ደግሞ ምዕራባውያን ፣አማፅያንን ካስታጠቁ የእጃቸውን ማግኘታቸው አይቀርም ሲሉ እያስጠነቀቁ ነው ።
የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አልአሳድ ፣ ምዕራባውያን ለሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎች የጦር መሣሪያ መስጠት ከጀመሩ አሸባሪነትን መደገፋቸው መሆኑ ግልፅ ነው ብለዋል ። አሳድ ፍራንክፉርተር አልገማይነ ከተባለው እለታዊው የጀርመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ «በርግጥ ምዕራባውያን አማፅያንን ካስታጠቁ የአውሮፓ ምድር በአሸባሪዎች እጅ መውደቁ አይቀሬ ነው ብለዋል ።
አውሮፓ ለአማፅያን በምትሰጠው የጦር መሣሪያ እርዳታ የእጅዋን ማግኘትዋ አይቀርም ሲሉም አስጠንቅቀዋል ። በዚህ የተነሳም በሶሪያው ፕሬዝዳንት አመለካከት አውሮፓ ከደማስቆ መንግሥት ጋር ከመተባበር ውጭ ሌላ ምርጫ አይኖራትም ። አሳድ በርግጥ እንደ አንድ ገለልተኛ የውይይት ተሳታፊ የሚታዩ ሰው አይደሉም ። በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ለሶሪያ ተቃዋሚ ወገኖችም ቢሆን ጦር መሣሪያ መስጠቱ ብዙ ወቀሳዎች እየቀረቡበት ነው ። የጀርመን መንግሥትም ሆነ በርካታ ጠበብት ለተቃዋሚዎች የጦር መሣሪያ መሰጠቱን በጥራጣሬ ዓይን ነው የሚያዩት ። ዩናይትድ ስቴትስ ብሪታኒያና ፈረንሳይ ደግሞ አማፅያንን ለማስታጠቅ እያሰቡ ነው ። ዩናይትድ ስቴትስ እስካሁን በአብዛኛው ጥይት የማይበሳው ሰደሪያ ና የምሽት አጉሊ መነፅሮችን የመሳሰሉትን ነበር ወደ ሶሪያ የምትልከው ። ዋሽንግተን የአሳድ መንግሥት መርዘኛ የጦር መሣሪያዎችን መጠቀሙን አረጋገጥኩ ካለች ወዲህ ለሶሪያ አማፅያን የጦር መሣሪያ በመስጠት ድጋፏን ለማጠናከር ትፈልጋለች ። ስቶክሆልም ስዊድን በሚገኘው የሰላም ተቋም አጥኚ ፒተር ቬትዘማን የጦር መሳሪያዎችን መስጠት ግጭቱን ያስቆማል ብለው አያምኑም ። የጦር መሳሪያዎቹ ወደ ሌላ ወገን ሊተላለፉ ይችላሉ ፣ ይህ ምናልባትም ጦርነቱ እንዲባባስ ሊያደርግም ይችላል ።
«ሶሪያ ውስጥ ለሚገኙ ማንኛቸውም አማጺ ቡድኖች የሚላክ የጦር መሣሪያ ወደ ማይፈለጉ ሰዎች እጅ ሊገባ የመቻሉ ግልፅ አደጋ አለ ። በአማፅያኑም በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውልም ይችላል ። ምናልባትም መሣሪያዎቹን የሚቀበሉት አማፅያን ዓለም ዓቀፍ የጦር ህግጋትና ደንቦችን የተከተለ ውጊያ እንዴት እንደሚካሄድ ላያውቁ ይችላሉ ። »
የሶሪያ አማፅያን በተለያዩ ቡድኖች የተለፋፈሉ ናቸው ወደ ሃገሪቱ የሚገባው የጦር መሣሪያም አክራሪዎች እጅ ይገባል የሚል ስጋት አለ ። መሣሪያዎቹ ለማይፈለጉ ወገኖች ከተሰጡ ደግሞ እንደ ቬትዘማን አባባል ጥፋቱ የከፋ ሊሆን ይችላል ።
« ያ ማለት የጦር መሣሪያዎቹን ህዝብን ለመፍጀት ይጠቀሙበታል ። በተለያዪ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውልም ይችላል ። »
እነዚህ መሣሪያዎችም አንድ ቀን በምዕራቡ ዓለም ላይ ሊደገኑ የመቻላቸው ስጋት እንዳለ ነው ። ከልምድ እንደሚታወቀው በጦርነት ቀጣናዎች የጦር መሳሪያዎች ይጠፋሉ ።ለምሳሌ ከሊቢያው ጦርነት በኋላ የፈረንሳይ ፀረ ታንክ ሚሳይሎች ደብዛቸው ጠፍቷል ። እነዚህ መሳሪያዎች የማሊን መንግሥት በሚወጉት አማፅያን እጅ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል ።
የጦር መሣሪያዎች ከሊቢያ ወደ ሶሪያ እየገቡ ነው የሚሉ ዘገባዎችም አሉ ። ከሁሉ አስጊው ግን ከምድር ወደ ሰማይ የሚወነጨፉ ፀረ አውሮፕላን ሚሳይሎች ጉዳይ ነው ። እነዚህ ሮኬቶች ለመንገደኛ አውሮፕላኖችም አደገኛ መሆናቸውን የጀርመን መንግሥት የጦር መሣሪያዎች ጠቢብ ሮልፍ ኒክል ያስረዳሉ
«በትከሻ የሚያዙ ፀረ አውሮፕላን ሮኬቶች በመሰረቱ አደገኛ ናቸው ። በርሳቸው እምነትየህዝብ ማመላለሻ አውሮፕላኖችንም ለአደጋ ያጋልጣሉ ። ስለዚህ «ማንፓት» የሚባሉት እነዚህ መሳሪያዎች በዓለም ዓቀፍ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ አደጋ እንዳያስከትሉ መጀመሪያ ቁጥጥር ሊደረግባቸውና ተሰብስበውም ሊደመሰሱ ይገባል ። ሊቢያ ውስጥ እነዚህ መሳሪያዎች ተስብስበው ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ እገዛ አድርገናል ።»
ኒልስ ናውማን
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ