1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ በጋዜጠኛዉ እይታ

ዓርብ፣ ሐምሌ 21 1998

ከፕሬዝደንት ሞሃመድ ዚያድ ባሬ ዉድቀት በኋላ ሶማሊያ ላለፉት 15ዓመታት በጦር አበጋዞች ማን አለብኝነት ስትታመስ ዜጎቿም ለስደት፤ ለችግርና በሽታ ተዳርገዉ ነዉ የከረሙት።

https://p.dw.com/p/E0iL
የፈራረሰችዉ ሶማሊያ
የፈራረሰችዉ ሶማሊያምስል AP

ይህ ገና እልባት ሳያገኝ አገሪቱም ህግ አልባ ሆና አንዱ ወገን የሽብርተኞች ምሽግ ትሆናለች ሲል ሌላዉም በዓለም ህገ ወጥ የተባሉ ተግባራት ተመልካች ስለሌለ ሲካሄድባት ነዉ የኖረችዉ እያለ ሰሞኑን ደግሞ ሌላ ችግር በዚችዉ በአፍሪቃ ቀንድ አገር ተደንቅሯል። የሶማሊያ ችግር የአጎራባቾቿም ችግር እንደሚሆን በመታመኑም ስጋቱ የአንድ ወገን ሳይሆን የጋራ ነዉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርነዉ በኬንያ ናይሮቢ የፈርንሳይ የዜና ወኪል ማትም AFP ዘጋቢ የሆነዉን ጋዜጠኛ ቦጎንጎ ቦሲሬ የሶማሊያ ችግር የዉስጥ ሳይሆን የዉጪ ጣልቃ ገብነት ዉጤት ነዉ ይላል።
ጋዜጠኛ ቦሲሬ ሶማሌዎችም በባህላቸዉ ለየት ያለ የግጭት አፈታት ስልት ስላላቸዉ እርስ በርሳቸዉ ይጋጫሉ ብሎ አይገምትም።

እንዲህ የምትላቸዉ ሰዎች እኮ ናቸዉ በጎሳ በጎሳ ተቧድነዉ በጦር አበጋዞች ሲታመሱ አገሪቱንም ወደህግ አልባ ግዛትነት ለዉጠዋት የከሙት ብለዉም የእሱ እምነት ሶማሊያን ወደግጭት የሚከታት ነገር ካለ የዉጪ ጣልቃ ገብነት ብቻ ነዉ የሚል ነዉ።

«ዩናይይትድ ስቴትስ በየካቲት ዘጠኝ የጦር አበጋዞችን ፅንፈኛ የምትለዉን የእስላማዊ ሸንጎ እንዲወጉ አሰማራች። በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገዉ ዉጊያ እስላማዊዉ ሸንጎ አሸንፊ ሆኖ የጦር አበጋዞቹን ከመቋዲሾ አባረረ። መቋዲሾን ከተቆጣጠሩ ከሳምንት በኋላ ለዘብተኛ የሆኑትና የእምነት ሰባኪዉ የሸንጎዉ መሪ ሼክ ሸሪፍ ሼክ አህመድ ጆዉሃ ላይ ለዓለም ዓቀፍ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የፕሬዝደንት አብዱላሂ የሱፍ አህመድን የሽግግር መንግስት የሚደግፈዉ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮቹን ማንቀሳቀሱን ተናገሩ። ሆኖም የእሳቸዉን ክስ የአዲስ አበባ መንግስትም ሆነ የሶማሊያዉ የሽግግር መንግስት ደጋግመዉ አስተባበሉ። በሽብር ላይ ለከፈተችዉ ጦርነት ኢትዮጵያን እንደዓይነተኛ አጋር የምትቆጥረዉ አሜሪካም ወታደሮቹ መግባታቸዉን የሚያሳይ ነገር የለም አለች።»

በዚህ መካከል ባለፈዉ ሳምንት የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የእስላማዊዉ ሸንጎ ከባይደዋ 45ኪሎ ሜትር ላይ ሆኖ መዋጋት መጀመሩን ይህም በቅርቡ ካርቱም ላይ የተፈራረሙትን የተኩስ አቁም ዉል የሚጥስ መሆኑን ለዘጋቢዎች ተናገሩ።

የጎረቤት አገር ወታደሮችም የእሳቸዉን መንግስት ለመከላከል እንደተባለዉ ወደሶማሊያ ምድር አልገቡም አሉ። የአካባቢዉ ኗሪዎች ግን በድጋሚ ከ100 በላይ የሚሆኑ ወታደሮች፤ ተሽከርካሪዎችና ታንኮችን ማየታቸዉን ተናገሩ። ይህ በእንዲህ እንዳለም

«ዩናይትድ ስቴትስ በሽብርተኝነትና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸዉ ብላ የምትፈልጋቸዉ የእስላማዊዉ ሸንጎ ፅንፈኛ መሪ ሼክ ዳሂሪ ሀሰን አዌስ እዚያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ቅዱሱን ጦርነት አወጁ። ሸንጎዉን በመደገፍና እዛ የገቡትን የኢትዮጵያ ወታደሮች በመቃወም ተደጋጋሚ ሰልፎችም በመቋዲሾ ተካሄደ። ይህ ግን አሁንም በሁለቱም ወገን ማስተባበያ እየተሰጠበት ነዉ። ትናንት ደግሞ ኤርትራ ያዉ ከኢትዮጵያ ጋር እንደማትስማማ ይታወቃል። በሶማሊያና በአካባቢዉ ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ባይደዋን ለቀዉ ወደአዲስ አበባ ይመለሱ ብላ መግለጫ ሰጥታለች።ይህም መግለጫ የካዛኪስታን መሆኗን የሚያሳይ ምልክት ያላት አንድ እቃ ጫኝ አዉሮፕላን መቋዲሾ አርፋ መሳሪያ ካራገፈች በኋላ ነዉ።»

ቆይ እስቲ እዚህ ጋ የአዉሮፕላኑን ነገር ስታነሳ የካዛኪስታን መሆኗን ነዉ የጠቀስከዉ። ዘገባዎች ደግሞ የኤርትራ ነዉ ይላሉ። ከሌላ አገር ነዉ ማለት ነዉ?

«አይ አዉሮፕላኑ የካዛኪስታን ብሄራዊ ባንዲራ ቀለሞች አሉት። እስላማዊዉ ሸንጎዉ አዉሮፕላን እንደሌለዉ ይታወቃል። ቢኖረዉም ዓርማዉ ይህ አይሆንም። እነዚያ የቀድሞ የሶቪየት ህብረት ግዛቶች አዉሮፕላኖቻቸዉን ለተለያዩ አገልግሎቶች ያከራያሉ። የሽግግር መንስቱ ነዉ መሳሪያ ከኤርትራ ይዞ የመጣ ነዉ የሚለዉ። ምክንያቱም እስላማዊዉ ሸንጎ በእስላማዊ ኃይሎች ይደገፋል። ይህን አዉሮፕላን ተከራይተዉ አስመራ ላይ መሳሪያ ጭነዉ መቋዲሾ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ነዉ የተራገፈዉ ይላል መንግስት። እስላማዊዉ ሸንጎ እስካሁን ይህን አላረጋገጠም።»

በቅርበት ጉዳዩን እንደሚከታተል ጋዜጠኛ ነገሮችን ስታስተዉል ለመሆኑ ይህ ሁኔታ በምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት የሚያስከትለዉ ተፅዕኖዉ ምን ያህል ነዉ ትላለህ?

«እዉነት ለመነገር ጦርነቱ የኢትዮጵያን ወታደሮች ካካተተ ከድሮዉም በተለያዩ ችግሮች ሲጎዳ የነበዉ ይህን አካባቢ የባሰ ይጎዳዋል። እስላማዊዉ ሸንጎ በኤርትራ ይደገፋል፤ የሽግግር መንግስቱ ደግሞ በኢትዮጵያ። እነዚህ ሁለቱ ደግሞ እስከዛሬ ያልተፈታ የከረመ ግጭት ያላቸዉ ሀገራት ናቸዉ። ኬንያ ለረጅም ዓመታት ስደተኞችን በመቀበል የተቸገረች አገር ናት። እናም በሶማሊያ ጦርነት ኖረ ማለት የኢትዮጵያንና የኬንያን ዘላቂ ሰላምና ኑሮ ያናጋል።»

ከመነሻዉ የሶማሊያ ችግር የዉስጥ ሳይሆን የዉጪ ነዉ ብሎ ለሚያምነዉ ለAFP ዘጋቢ የመጨረሻ ጥያቄዬ ራሳቸዉ ሶማሌዎች ችግራቸዉን ለመፍታት የሚችሉ ይመስልሃል አልኩት፤

«ጥሩ ጥያቄ ነዉ፤ ለ15ዓመታት እንዲህ ሆነዉ ለቆዩት ሶማሌዎች ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ችግራቸዉን እዚያዉ ሶማሌ ዉስጥ እርስ በርሳቸዉ እንዲፈቱት መተዉ አለበት ነዉ የምለዉ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ፤ የመን፤ ዩናይትድ ስቴትስና ኤርትራ የተጣለዉን የመሳሪያ እቀባ እየጣሱ ነዉ። የዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ማንም እልደግፍም ብሎ ሶማሌዎች የራሳቸዉን ችግር በዉይይት እንዲፈቱ ቢፈቅድላቸዉ ፤ ይህ ብቻ ነዉ ብቸኛዉ መንገድ።»