1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ የጎርፍ አደጋ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 18 2008

የኤልኒኞ ተጽዕኖ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ድርቅ ሲያስከትል እንደ ሶማሊያ ባሉ ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የጎርፍ መጥለቅለቅ ማስከተሉ ተዘግቧል። በደቡብ ሶማሊያ በተከሰተው ጎርፍ የተነሳ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደጋ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA ) እስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1GwlD
03.07.2014 online karte somalia eng

[No title]

በሶማሊያ ካለፈዉ መስከረም 26 2008 አንስቶ መጣል የጀመረው ከባድ ዝናብ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዳስከተለ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ OCHA ገለጠ። የኤልኒኞ ተጽዕኖ ባስከተለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የተነሳ በተለይ በደቡብ እና መካከለኛው ሶማሊያ የጁባ እና ሸበሌ ወንዞች ሞልተው በመፍሰሳቸዉ የጎርፍ መጥለቅለቁ እንደተከሰተ ተናግረዋል። በጎርፉ መጥለቅለቅ ወደ ዘጠኝ መቶ ሺህ ነዋሪ ለአደጋ መጋለጡን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (OCHA )የሶማሊያ ቅርንጫፍ ምክትል ኃላፊ ሶፊ ጋርዴ ቶምሌን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

«ቀደም ሲል ከነበረን መረጃ በመነሳት ወደ 90,000 ሰዎች ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ በሚል ተዘጋጅተን ነበር።ሆኖም ግን በትክክል ቁጥራቸው ምን ያህል ነው የሚለውን ለማወቅ ተጨማሪ ጥናት ማድረግ ይኖርብናል።»

Infografik El Niño Erklärgrafik Englisch

በጎርፉ መጥለቅለቅ የተነሳ በሶማሊያ ጎጆዎች ተጠርገው መወሰዳቸው፣ የውኃ ጉድጓዶች እና መጸዳጃ ሥፍራዎች ከጥቅም ውጪ መሆናቸውም ተዘግቧል። በሶማሊያ 3,2 ሚሊዮን ሕዝብ ማለትም ከአጠቃላይ ነዋሪ አንድ ሦስተኛው የሕይወት አድን ርዳታ እንደሚያስፈልገው ቀደም ሲል የተገለጠ ሲሆን፤ አንድ ሚሊዮኑ በጎርፉ የተነሳ ተፈናቅሎ ነበር ተብሏል። ዝናቡ ባስከተለው ጎርፍ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ለጊዜው ከሰፈሩበት አካባቢም ጎርፉ በመድረሱ ወደ ሌላ ስፍራ ለመሔድ መገደዳቸዉ ተገልጧል። በጎርፉ አደጋ የሞቱም እንዳሉ ተጠቅሷል።

«በበርካታ ቦታዎች የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ይነገራል፤ ከባለሥልጣናትም ይኽንኑ ሰምተናል። ይሁንና ግን ለዚህም ጥናት አድርገን ግልፅ የሆነ መረጃ እስኪኖረን ድረስ ቁጥሩ ይህን ያኽል ነው ለማለት አንችልም።»

ምን ያህል ሰው በጎርፉ አደጋ እንደተጋለጠ ሙሉ መረጃ የለንም ያሉት ሶፊ ጋርዴ ሆኖም ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ጎርፉ እጅግ ብርቱ የሚባል አደጋ ማድረሱን ጠቁመዋል። የኤልኒኞ ተፅዕኖ ተከትሎ በሶማሊያ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከ500,000 እስከ 900,000 ሰዎች አደጋ እንደተደቀነባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።በሶማሊያ አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታው ሁናቴ አስጊ ቢሆንም ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን ለማግኘት መንገድ እንደማይታጣ ኃላፊዋ ተናግረዋል።

«በበርካታ ቦታዎች የሰብአዊ ርዳታ ለማዳረስ እጅግ አስቸጋሪ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን በሁሉም ግዛቶች የምንደርስበት መንገድ አለን። ፀጥታው አስጊ በሆነበት ቦታ ያሉ ነዋሪዎች ጋር እንኳን የምንደርስበት በርካታ መንገዶች አሉን።»

በምስራቅ አፍሪቃ ሀገሮች በኢልኒኞ ተጽዕኖ የተነሳ ከስድሳ ዓመት ወዲህ እጅግ የከፋ ድርቅ እና ብርቱ ዝናብ ብሎም የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊከሰት እንደሚችል የተተነበየው ቀደም ሲል ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ