1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊዎች መጥፎ ዕጣ-ፈንታ በኬንያ

ዓርብ፣ ግንቦት 28 2007

በኬንያ የሚኖሩ ሶማሊዎች፣ በየጊዜው ነው በፖሊስ የሚንገላቱት። ባለፉት ቀናት በኢንተርኔት የተለቀቁ ፎቶግራፎች፤ እንደሚያስረዱት፤ በተደጋጋሚ በሶማሌዎች ላይ በደሎች ተፈጽመዋል።በተለይ በሰሜናዊው ምሥራቅ ኬንያ ፤ በጋሪሳ! ፖሊሶች የሆነው ሆኖ ጉዳዩን

https://p.dw.com/p/1Fbf5
ምስል picture-alliance/dpa

[No title]

ለማጣራት ቃል ገብተዋል። በሶማሊያ የሚገኘውና ኬንያ ግዛት ውስጥ ዘልቆ በመግባት በተለያዩ ቦታዎች በጋሪሳ ብቻ ሳይሆን በወደብ ከተማ ሞምባሳና በመዲናይቱ በናይሮቢ አደጋ በመጣል ብዙ ሰላማዊ ሰዎች የገደለው አክራሪው እስላማዊ ድርጅት አሸባብ፤ ጥቃቱ ፈጽሞ ሊገታ አልቻለም። ኬንያ ጦሯን ሶማልያ ውስጥ ካስገባችበት ጊዜ አንስቶ፤ ይኸው ታጣቂ ኃይል የበቀል ርምጃ መውሰዱን አላቆመም። የኬንያ ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎችም ፤ በጥርጣሬ ፤ ሰላማዊ ሶማሌዎችን ጭምር የሚያስጨንቁበት ፤ የሚያንገላቱበት ሁኔታ አለ። HRW ፣ኬንያ ውስጥ ሶማሌዎችን በተለየ ሁኔታ መመልከቱና ኣድልዎ ማድረጉ አሁን የተጀመረ አይደለም ይላል።

Kenia Studenten trauern um Garissa-Kommilitonen 07.04.2015
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

በሰሜናዊው ምሥራቅ ኬንያ ግዛት ውስጥ፤ የኬንያ ዜጎች የሆኑ የሶማሊ ዝርዮች ይኖራሉ ። በእነዚህ ኅዳጣን ወገኖች ላይ ታዲያ አድልዎ መፈጸሙም ሆነ ማግለሉ ፤ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ታጋዩ ድርጅት HRW እንደሚለው፣ ረጅም ታሪክ ያለው ነው። የ HRW የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች ኀላፊ ሊስሊ ሌፍኮቭ--

«HRW ፣ በጋሪሳና በተለያዩ የሰሜን ምሥራቅ ከተሞች፤ ተመሳሳይ የማንገላታት ርምጃዎች በየጊዜው መፈጸማቸውን መዝግቧል። በዚያ የሚኖሩ ሶማሊዎች፤ በኬንያ ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች፤ በተከታታይ ድብደባና የሚያዋርድ ተግባር ይፈጸምባቸዋል።»

የኬንያ ፖሊሶች በቅርቡ ወጣት ሶማሌዎችን አሥረው መሩት ላይ በማስተኛት በቆመጥ ሲደበድቧቸውና በጅራፍ ሲገርፏቸው መታየቱ ዓለም አቀፍ ድንጋጤና ቁጣ ማስከተሉን፤ HRW ገልጿል። የተደብዳቢዎቹ ወጣቶች አበሳ፤ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ወሰን አቋርጠው ሥራ ፍልጋ ጋሪሳ መግባታቸው ነው። የኬንያ ፖሊሶች ለምን ይሆን በሶማሌዎቹ ላይ የሚጨክኑት? አሁምን ሌስሊ ሌፍኮቭ---

«ጸጥታ አስከባሪዎቹ ፤ ሶማሌዎቹን አሸባብናና ባጠቃላይ አክራሪነትን የሚደግፉ ናቸው በማለት ይጨክኑባቸዋል።በተለይ የኬንያ የጸጥታ ይዞታ አደገኛ ሁኔታ እንደተደቀነበት ከተሰማቸው ለጭካኔአቸው ገደብ አይኖረውም። ፖሊሶች መጠን ሰፊ የማንገላታት ርምጃ የሚወስዱት፣ አሸባብ የኬንያ ጦር ኃይል እ ጎ አ በ 2011 ወደ ጎረቤት ሶማልያ ዘልቆ መግባቱን በመቃወም የብዙ ሰላማዊ ሰዎችን ደም አፍስሷል በማለት ነው። በጸጥታ አስከባሪዎቹ ዘንድ፣ የጠላትነቱ መንፈስ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተጠናክሯል። ለዚህ አንዱ መገለጫ፤ የኬንያ መንግሥት፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የሶማልያ ስደተኞች የሠፈሩበት ጣቢያ እንዲዘጋና ስደተኞቹ ወደ ሶማልያ ተገደው እንዲመለሱ እስከመጠየቅም ሆነ ማሳሰብ መድረሱ ነው።»

Flüchtinge in Dadaab Kenia
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

ባለፈው ሚያዝያ 4 አሸባሪዎች፤ በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ በምትገኘው ከተማ በጋሪሳ፤ የዩንቨርስቲውን ቅጥር ግቢ ወረው 148 ተማሪዎችን መግደላቸው የሚታወስ ነው። የሶማሌ ዝርያ የሆነ ሰው ሁሉ ኬንያ ውስጥ በጥርጣሬ ዐይን ሆኗል የሚታየው። «ሁላችሁም አሸባሪዎች ናችሁ!» እየተባሉ የሚዘለፉበት ሁኔታም አለ ። ዳባብ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከ 350,000 በላይ የሶማልያ ስደተኞች ይገኛሉ። ከ 10 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ተሰዶ ኬንያ የገባውና በስደተኛ ጣቢያ መኖር ማለት ምን እንደሆነ የሚያውቀው አሁን በናይሮቢ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ው ጋዜጠኛ ካባታ ቦሩ እንዲህ ይላል።

«የሶማልያ ስደተኞች ራሳቸው፤ የአሸባብ ሽብር ሰለባዎች ሆነዋል። ትውልድ ሀራቸውን ለቀው የተሰደዱት እጅግ አክራሪ ከሆኑት አሸባብ ሚሊሺያ ጦረኞችና ከገረረው የሸሪያ ሕጋቸው ለማምለጥ ነው። ኬንያ ውስጥ ደግሞ፤ እንደማንኛውም የኬንያ ዜጋ የአሸባሪዎች የጥቃት ሰለባዎች ይሆናሉ። የኬንያ መንግሥት በመጨረሻ ሊቀስም የሚገባው ትምህርት፤ ምናልባት ማን ስደተኛ ማን ደግሞ አሸባሪ እንደሆነ መለየትን ነው።»

ከትውልድ ሀገር ፤ በአሸባሪ ጨካኝ አካራሪ ታጣቂ ቡድን ተሳደው ኬንያ የገቡ፤ ስደተኞች፣ በሚጠራጠሩ የፀጥታ አስከባሪዎች የሚደርስባቸው መንገላታት አንዳንዴ ለመግለጽ የሚያስቸግር ነው። አሁንም ጋዜጠኛ ካባታ ቦሩ---

S
ምስል Bettina Rühl

«ባለፈው ጊዜ የኬንያ ፖሊስ ጸረ- ሽብር ርምጃ ያለውን አሰሳ በአመዛኙ ሶማሌዎችና ስደተኞች በሚኖሩበት ኢስትሊ በተባለው የናይሮቢ ከተማ አንድ ሠፈር ውስጥ አካሂዶ ነበር።

ኢስትሊ፣ ሶማሌዎች ሰፊ ንግድ የሚያካሂዱበት ሞቅ ያለ ሠፈር ነው። ፖሊስ የወሰደው የጭካኔ ርምጃ፤ በንግድ የተሳካ ተግባር በሚያከናውኑት ሶማሌዎች ላይ ቅናት መኖሩንም አይጠቁምም ማለት አይቻልም። ኢስትሊ ውስጥ አምና የተፈጸመ ድርጊት እማኝም ነበርሁ። ሰዎች፣ ተዋክበዋል መንገላታት ደርሶባቸዋል። ሱቃቸው እንዲፈራርስ ተደርጓል። በሴቶችላይ የጭካኔ ተግባር ተፈጽሟል። ብዙዎች ሶማሌዎች፤ ናይሮቢን ለቀው መውጣት እንዳለባቸው ተሰምቷቸዋል። በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ነው።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ