1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊላንድ ጥያቄና የአፍሪቃ ሕብረት

ዓርብ፣ ጥር 25 1999

ከእንግዲሕ ሁኔታዉን ማየት የአፍሪቃ ሕብረት መሪዎች ፋንታ ነዉ።

https://p.dw.com/p/E0Yl
ሶማሊያ አንድም ሁለትምነች
ሶማሊያ አንድም ሁለትምነችምስል AP


እራስዋን የሶማሊ ላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራዉ ሰሜን ሶማሊያ የነፃ ሐገርነት አለም አቀፍ እዉቅና እንድታገኝ የምታደርገዉን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደቀጠለች ነዉ።የሶማሊ ላንድን ፍላጎትና ጥረትና በመጋራት ሩዋንዳ የመጀመሪያዋ ሐገር ሆናለች።ባለፈዉ ሰኞ እና ማክሰኞ አዲስ አበባ ተሰይሞ በነበረዉ የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት የሶማሊያ ላንድ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አብዱላሒ ዱዋሌን ሐገራቸዉ ከሩዋንዳና ሌሎች በስም ካልጠቀሷቸዉ ሐገራትና ተቋማት ላገኘችዉ ድጋፍ አመስግነዋል።እዚያዉ አዲስ አበባ የነበረዉ ባልደረባችን ሉድገር ሻዶምስኪ ዱዋሌን አነጋግሯቸዉ ነበር።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።


ከሃያ-አመታት በላይ ሶማሊያን በብረት ጡንቻ የገዙት የፕሬዝዳት መሐመድ ዚያድ ባሬ መንግሥት ከፈረሰ ወዲሕ ደቡብ ሶማሊያ በርስ በርስ ጦርነት ሥትታመሥ ሰሜንዋ አንፃራዊ ሠላም ሰፍኖባት፤ የተረጋጋ አመራር ተመሥርቶባት ነዉ የቆየችዉ።አስራ-ስድስት ዘመን።በዚሕ ዘመን ሁሉ የጥንቷ የብሪታንያ ቅኝ ተገዢ ሶማሊ ላንድ ራስዋን እንደነፃ መንግሥት ብትቆጥረም ነፃነትዋን በይፋ ያወቀላት አንድም ሐገር የለም።

ሐርጌሳ ላይ መንግሥት ያቆሙት የሐገሪቱ ፖለቲከኞች እዉቅና ለማግኘት መጣር መጋራቸዉ አልቀረም።ጥረታቸዉ እስካሁን ከሙሉ ይፋ ነፃነት አላደረሳቸዉም። ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች ከተጠቃች እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ከሁለት ሺሕ አንድ በሕዋላ አሸባሪዎች በሶማሊያ እና በአካባቢዉ ይመሽጋሉ የሚለዉ ሥጋት ግን ለሶማሌ ላንዶች ሕልም-እዉንነት የመጀመሪያዉን ብልጭታ አይነት ነዉ-የሆነዉ።

ለፀረ-ሽብር ያደመዉ አለም ለሐርጌሳዉ መንግሥት የመንግሥትነት እዉቅና ባይሰጥም እንደ ጥሩ ሸሪክ በቀጥታም በተዘዋዋሪዎም አብሮት እየሰራ ነዉ።አሁን ደግሞ ሶማሊያ ላንድ ምኞትዋን በይፋ የሚጋራ ሐገር አግኝታለች።ሩዋንዳን።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አብዱላሒ ዱዋሌ ሌሎችም አሉ ይላሉ።ሁሉንም ያመስግናሉ።

«ሩዋንዳን በጣም እናመሰግናለን።ባለፉት ጊዚያት የጎበኘናቸዉን የምዕራብ አፍሪቃ፤ የማዕከላዊና የምሥራቅ አፍሪቃ፣ የደቡባዊ አፍሪቃ ሐገራትንም እናመሰግናለን።ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰሩ ታላላቅ ባልደረቦቼንም በጣም አመሰግናለሁ።»

የመንግሥታቸዉ ጥረት አሁን ከደረሰበት መድረሱ ለዱዋሌ በርግጥ ድል ነዉ።አዲስ አበባ ተስይሞ በነበረዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመጋረጃ ጀርባም ቢሆን ሥለሶማሊያ ላንድ ጉዳይ እያነሳ በመጣሉ ዱዋሌ ደስተኛ ናቸዉ።

«ከብዙዎቹ ጉዳዮች መሐል የጉዳዩ ሕጋዊነት፤ ሥነ ምግባራዊነቱ፤ ያለ ሌሎች ድጋፍ ሶማሊላንድ በራስዋ ጥረት እራስዋን እራስዋን በመቻሏ እና በሁለት እግሯ በመቆሟ ከታላቅ ደስታ ጋር ነዉ ወደ ሐገሬ የምመለሰዉ።»

ደስታዉ ዳር መዝለቁ ግን ብዙ አጠራጣሪ ነዉ።በኢትጵያ ጦር ድጋፍ መቅዲሾን የተቆጣጠረዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት መተዳደሪያ ደንብ ቻርተር፣ አለማ ግቡም አንዲት ሶማሊያን ማስተዳደር ነዉ።ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሽግግር መንግሥቱ ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚሰጡት ሐገራትና ተቋማት ደግሞ የሶማሊ ላንድ ወዳጆችም ናቸዉ።እነዚሕ ሐይላት ከሶማሊያን አንድነት ወይም ሁለት (የሶማሊ ላንድን ነፃነት ከመቀበል) አንዱን መምረጥ ግድ ይላቸዋል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዱዋሌ ተስፋችን እንደስካሁን በተስፋ አይቀርም ባይ ናቸዉ።

«ኢጋድ አሜሪካኖች፤ ኖርዌ፣ የአረብ ሊግ፣ ሌሎችም ጉዳዩን እየተከታተሉት ነዉ።ከዚሕ ሁሉ መሐል አንድ ተጨባጭ ዉጤት ይወጣል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር።ከእንግዲሕ ግን የሆነ ዉጤት ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋል።»

የሶማሊላንድን ጉዳይ እንዲያጠና የአፍሪቃ ሕብረት የሰየመዉ ኮሚሽን የጥናት ዉጤቱን ለሕብረቱ አቅርቧል።በኮሚሽኑ ዘገባ መሠረት አብዛኛዉ የሶማሊ ላንድ ሕዝብ፣ የግዛቱ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ማሕበራት በሙሉ የግዛቲቱን ነፃነት ደጋፊዎች ናቸዉ።በቅርቡ በመላዉ ሶማሊያ ላንድ በተደጋጋሚ በተደረጉ ሠላማዊ ሰልፎች የተሳተፈዉም ሕዝብ ነፃነትን ጠያቂ ነዉ።ዱዋሌ እንደሚሉት የአፍሪቃ መሪዎች ሐቁን አይተዉ መወሰን አለባቸዉ።

«ከእንግዲሕ ሁኔታዉን ማየት የአፍሪቃ ሕብረት መሪዎች ፋንታ ነዉ።ሶማሊላንድ የት መሆን እንዳሚገባት፤ ታሪክ ይፈርዳል።የሥነ-ምግባራዊና የሞራላዊ እሴቶችን፣ ፍትሕን በሙሉ ለታሪክ ብይን መተዉ ነዉ።»