1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ጥንቅር

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 20 2007

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የቸልሲው አሠልጣኝ መነጋገሪያ ሆነዋል። ጀርመናዊው የመኪና ሽቅድምድም ባለድሉ ሹማኸር የራስ ቅሉ ላይ አደጋ ከደረሰበት ዛሬ 1 ዓመት ሞላው። በዝውውር ዜናዎች፦ ፈርናንዶ ቶሬዝ የልጅነት ዘመኑን ወዳሳለፈበት ቡድኑ ሊያቀና ነው። የጣሊያኑ ሣምፕዶሪያ ቡድን የሊቨርፑሉ አጥቂ ማሪዮ ባሎቴሊን ልውሰድ ብሏል።

https://p.dw.com/p/1EC71
Skihelm-Kamera
ምስል Reuters

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት አርሰናል ዌስትሐም ዩናይትድን 2 ለ1 አሸንፏል። ማንቸስተር ሲቲ ከበርንሌይ 2 ለ2 አቻ ተለያይቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶትንሐም ሆትስፐር ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርተዋል። ፍፁም ቅጣት ምት የተነፈገው ቸልሲ ከሳውዝሐምተን ጋር አቻ ወጥቷል። አሠልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ «ዘመቻ ተከፍቶብናል» ብለዋል። ኩዊንስ ፓርክ ከክሪስታል ፓላስ እንዲሁም አስቶን ቪላ ከሰንደርላንድ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ግብ ሳይቆጠር ተጠናቋል።ሌስተር ሲቲ ሁል ሲቲን 1 ለባዶ፣ ኒውካስል ዩናይትድ ኤቨርተንን 3 ለ2 አሸንፈዋል። ስቶክ ሲቲ ዌስት ብሮሚችን 2 ለዜሮ ሸኝቷል።

ፈርናንዶ ቶሬዝ
ፈርናንዶ ቶሬዝምስል Reuters

በዚህም መሠረት ቸልሲ 46 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ በአንደኛነት ይመራል። ሆኖም ከማንቸስተር ሲቲ የሚለየው በሦስት ነጥብ ብቻ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ ከቸልሲ በ10 ነጥቦች ርቀት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሳውዝ ሐምፕተን ከማንቸስተር ዩናይትድ በ3 ነጥብ ዝቅ ብሎ 33 ነጥቦችን በመያዝ አራተኛ ደረጃን ተቆናጧል። አርሰናል በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ልዩነት ከሳውዝ ሐምፕተን ስር አምስተኛ ነው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑል ቁልቁል 10ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ዛሬ ከስዋንሲ ሲቲ ጋር ይፋለማል። ስዋንሲ ሲቲ ሊቨርፑልን በሦስት ነጥብ በልጦ፣ 28 ነጥቦችን በመያዝ ደረጃው ስምንተኛ ነው።

የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ በ14 ግቦች ኮከብ ግብ አግቢነቱን ይመራል። የቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ በ13 ግቦች ይከተለዋል። የኩዊንስ ፓርኩ ቻርሊ አውስቲን 12 ግቦች አስቆጥሮ ይሰልሳል። የአርሰናሉ አሌክሲስ ሳንቼዝ 10 ግቦች አሉት፤ አራተና ነው።

ማንቸስተር ሲቲ
ማንቸስተር ሲቲምስል Alex Livesey/Getty Images

ቸልሲ ከሣውዝሐምተን ጋር አንድ እኩል የተለያየበት ጨዋታ ብዙዎችን አወዛግቧል። ጨዋታው በተጀመረ 55ኛው ደቂቃ ላይ የቸልሲው አማካይ ሴስ ፋብሬጋስ በሳውዝሐምተኑ ተከላካይ ማት ታርጌት ይጠለፍን ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ ይወድቃል። ዳኛው ግን በተቃራኒው ሴስ ፋብሬጋስን ለማጭበርበር ሞክረሃል በሚል ቢጫ ሰጥተውታል። ክስተቱ በዝግታ ሲታይ በእርግጥም የማት ቀኝ እግር ፋብሬጋስን ማደናቀፉን ማሳበቁ አልቀረም። የቸልሲው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ዳኛው ፍፁም ቅጣት ምት ሳይሰጡ ጭራሽ ተጨዋቻቸውን በቢጫ መቅጣታቸው አድልዎ እንደሆነ ገልጠዋል። ጆዜ ሞሪንሆ «ግልጽ የሆነ ዘመቻ» ተከፍቶብኛል ሲሉ ቅሬታቸውን አሠምተዋል። ተንታኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ተቺዎች እና አሠልጣኞች ባደረሱት ተፅዕኖ ዳኞች ስህተት እየሰሩ መሆናቸውንም አሠልጣኙ ተናግረዋል።

ጆዜ ሞሪንሆ የእንግሊዝ ጋዜጦች እና መገናኛ አውታሮች አብይ መነጋገሪያ ሆነዋል። ሞሪንሆ የሚፋለሙት በአምስት ግንባር ነው አለ አንድ የእንግሊዝ ጋዜጣ። ከፊት ለፊታቸው የፕሬሚየር ሊግ ፍትጊያ አለ። ሻምፒዮንስ ሊግ ኹለተኛው ግንባር መሆኑ ነው። ኤፍ ኤ ካፕ እና ካፒታል ዋን ካፕም ከፊታቸው ተደቅኗል። ይሄ ብቻም አይደል እንደጋዜጣው ከሆነ፤ ሞሪንሆ ከዳኞች ጋር የጀመሩት ፍልሚያ አምስተኛ ግንባር ተብሎ ተዘግቦበታል።

ጆዜ ሞሪንሆ
ጆዜ ሞሪንሆምስል Reuters/Eddie Keogh

የቸልሲው አጥቂ ፈርናንዶ ቶሬዝ የልጅነት ዘመኑን ወዳሳለፈበት የቀድሞ ቡድኑ እንደሚመለስ ይፋ ሆኗል። ቸልሲ የክሮሺያው የፊት አጥቂ አንድሬ ክራማሪችን ወደ ቡድኑ ለማስመጣት 7,8 ሚሊዮን ፓውንድ መመደቡ ተገልጧል። እነዚህን እና ሌሎች የዝውውር ዜናዎችን ወደ በኋላ ላይ እናሠማለን።

የመኪና ሽቅድምድም

የራስ ቅሉ ከድንጋይ ጋር ተላትሞ የጭንቅላት አደጋ ከደረሰበት ልክ ዛሬ አንድ ዓመት ሞላው፤ ጀርመናዊ የመኪና አሽከርካሪ ሚሻኤል ሹማኸር። በበረዶ ግግር የተዋጡት የአልፐፕስ ተራራዎች ለዓለማችን ቁጥር አንድ የመኪና ሽቅድምድም አሽከርካሪው ሚሻኤል ሹማኸር አዲስ አይደሉም። ሁሌም በበረዶ እየተንሸራተተ በመጫወት ለመዝናናት ወደዚያ ያቀናል። የዛሬ ዓመት በእርግጥ ወደበረዷማ ተራራዎቹ ሲወጣ ጥቂት ቀናቶችን እዚያው ለማሳለፍ በማሰብ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚብተውን አዲስ ዓመትን እና የልደት ቀኑን እዛው በአልፕስ ለማክበርም አቅዶ ነበር። ሆኖም 45ኛ ዓመቱ ሊደፍን እጅግ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት በበረዶው ላይ በፍጥነት ይንሸራተትና የራስ ቅሉ ከድንጋይ ጋር ይላተማል። ራሱ ላይ የደፋው መከላከያ ቆብ ተጠርምሶ የራስ ቅሉ በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል። ራሱንም ይስታል። በፍጥነት ሀኪም ቤት ቢወሰድም አደጋው ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አዕምሮው ውስጥም ጉዳት እንዳስከተለ ሐኪሞች በወቅቱ አስታውቀዋል። ሹማኸር ለረዥም ጊዜያት ሐኪም ቤት ውስጥ ራሱን እንደሳተ ለመቆየት ተገዷል። ሹማኸር ራሱን ማወቁ በሥራ አስኪያጁ በኩል ይፋ የሆነው አደጋ ከተከሰተ ከስድስት ወራት በኋላ ነበር። ስዊትዘርላንድ ጔኔቫ ወሚገኘው ቤቱ ተዛውሮ የሕክምና ክትትል ከጀመረ ሦስት ወራት ተቆጥሯል። ዛሬ ሹማኸር አደጋ የደረሰበት አንደኛ ዓመቱ ቢሆንም ሥራ አስኪያጁ ሣቢኔ ኬህም «ከፊት ለፊቱ ረዥም እና ከባድ ጊዜያት ይጠብቁታል» ሲሉ ያለበትን አስቸጋሪ ሁናቴ ተናግረዋል።

ሚሻኤል ሹማኸር
ሚሻኤል ሹማኸርምስል picture-alliance/dpa

አዳዲስ የዝውውርና አጫጭር ዜናዎች

የቸልሲው አጥቂ ፈርናንዶ ቶሬዝ የልጅነት ዘመኑን ወዳሳለፈበት የቀድሞ ቡድኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ሊያቀና መሆኑ ዛሬ ተነገረ። ፈርናንዶ ቶሬዝ ከኹለት ቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ ከቸልሲ ወደ ጣሊያኑ ኤስ ሚላን በማቅናት በቋሚነት መጫወት እንደሚፈልግ ገልጦ ነበር። ሆኖም ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ እንደሚያቀና ቡድኑ በድረ-ገፁ ማረጋገጫ ሰጥቷል። ዝውውሩ በውሰት ሲሆን ለአንድ ዓመት የሚቆይ መሆኑም ይፋ ሆኗል። ቶሬዝ በ50 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ቸልሲ ከመዛወሩ በፊት ለሊቨርፑል ለ4 ዓመት ተሰልፎ ተጫውቷል። ወደ ሊቨርፑል ከማቅናቱ በፊት ደግሞ የ17 ዓመት ልጅ ሳለ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ማሊያን ለብሶ ተጫውቷል። የዛሬ 13 ዓመት ግድም መሆኑ ነው። በወቅቱ ለአትሌቲኮ ማድሪድ ተሰልፎ በ244 ግጥሚያዎች 91 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሎ ነበር። ፈርናንዶ ቶሬዝ የፊታችን ሰኞ የሐኪም ምርመራውን አጠናቆ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ልምምድ እንደሚጀምር ቡድኑ ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ሊቨርፑል የዌስት ብሮሚቹ አጥቂ የ21 ዓመቱ ሣይዶ ቤራሂኖ ላይ ዓይኑን ጥሏል። ሣይዶ በ23.5 ሚሊዮን ፓውንድ ሊቨርፑልን ሊቀላቀል መሆኑ ተሰምቷል። የዌስት ብሮሚቹ አጥቂ ከ21 ዓመት በታች የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ 133 ጊዜ ተሰልፎ 9 ግቦችን ማስቆጠሩ ይታወቃል። ሊቨርፑል ሣይዶን ለማስመጣት ሲሯሯጥ ቀደም ሲል ለቡድናችን ያስፈልገናል ያለለት የባየር ሙይንሽኑ የክንፍ ተጨዋች ዤርዳን ሻቃሪን ፈጣኖች ሊሞጨልፉት ነው። ዤርዳን ከባየር ሙይንሽን በውሰት ወደጁቬንቱስ ሊያቀና እንደሆነ ተዘግቧል። የቀድሞው የሊቨርፑል አሠልጣኝ ዴቪድ ሞየስ በበኩላቸው አሁን ለሚያሠለጥኑት የስፔኑ ሪያል ሶሴዳድ ቡድን የሊቨርፑሉ ኤምሬ ካንን በውሰት ማምጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። የጣሊያኑ ሣምፕዶሪያ ቡድን የሊቨርፑሉ አጥቂ ማሪዮ ባሎቴሊን ከሰሞኑ መውሰድ እንደሚፈልግ ዛሬ ይፋ አድርጓል። ከአራት ወራት በፊት በ16 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ሊቨርፑል የመጣው ማሪዮ ባሎቴሊ በ15 ጨዋታዎች ኳስ ከመረብ ያሳረፈው ለኹለት ጊዜ ብቻ ነው።

ማሪዮ ባሎቴሊ
ማሪዮ ባሎቴሊምስል imago/BPI

ቸልሲ የክሮሺያው የፊት አጥቂ አንድሬ ክራማሪችን በሚቀጥለው ወር ወደ ቡድኑ ለማስመጣት 7,8 ሚሊዮን ፓውንድ መመደቡ ተገልጧል። የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን የአርሰናሉ አጥቂ ሉቃስ ፖዶሊስኪን ለመውሰድ መቃረቡ ተነግሯል። ኢንተር ሚላኖች ከትናንት በስትያ ከአርሰናል ዋና ሰዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ጀርመናዊውን የአርሰናል አጥቂ ለመውሰድ ተቃርበናል ብለዋል። አርሰናል በበኩሉ የዌስት ሐሙ ተከላካይ ዊንተን ራይድን ለማስመጣት 4 ሚሊዮን ፓውንድ መመደቡ ታውቋል።

አጫጭር ዜናዎች

በአውሮጳ የዜና አውታሮች ባለፈው ዓርብ ድምፅ በተሰጠበት የአውሮጳ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኞች ጀርመናዊው ማኑኤል ኖየር በአንድ ነጥብ ተበልጦ ኹለተኛ ሆኗል። በ82 ነጥብ የአውሮጳ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ተብሎ የተሸለመው በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ባለድሉ እንግሊዛዊው ሌዊስ ሐሚልተን ነው። ሠርቢያዊው የሜዳ ቴኒስ ዝነኛ ኖቫክ ጆኮቪች ክሪስቲያኖ ሮናልዶን በልጦ በ74 ነጥብ ሦስተኛ ሆኗል። ለሪያል ማድሪድ የሚጫወተው የፖርቹጊዙ አጥቂ ክሪስቲኖ ሮናልዶ ድምፅ ከሰጡት ጋዜጠኞች ያገኘው ነጥብ 72 ሲሆን፤ ደረጃው አራተኛ ነው።

ማኑዌል ኖየር
ማኑዌል ኖየርምስል Bongarts/Getty Images/L. Baron

የፈረንሣዩ ማርሴይ አማካይ ማሪዮ ላሚና የትውልድ ሀገሩ ጋቦን ለአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታ እንዲሰለፍ ያደረገችለትን ጥሪ ውድቅ ማድረጉ ተሰማ። ማሪዮ ሌሚና ከ20 ዓመት በታች የፈረንሣይ ቡድን ውስጥ ተሰልፎ የዓለም ዋንጫ መጨበጡ ይታወቃል። ማሪዮ በፈረንሣይ ዋናው ቡድን ጥሪ ይደረግልኛል በሚል ተድፋ እየተጠባበቀ መሆኑም ታውቋል ። የጋቦን ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዙሪያ ተሰልፈው የሚጫወቱ ድንቅ ተጨዋቾችን ማካተቱ ተገልጧል።

ከተጨዋቾቹ መኻከል የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ፒየር ኤመሪክ፣ የካርዲፉ ተከላካይ ብሩኖ ማንጋ እና የቻርልተን አትሌቲክ አጥቂ ፍሬድሪክ ቡሎት ይገኙበታል ተብሏል። የጋቦን ቡድን በምድብ ኤ ውስጥ ይገኛል። ምድቡ የአፍሪቃ ዋንጫ አስተናጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኮንጎ ይገኙበታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ