1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ጥንቅር፤ ጥር 11 ቀን፣ 2007 ዓም

ሰኞ፣ ጥር 11 2007

የአይቮሪኮስቱ አጥቂ ዊልፍሬድ ቦኒ በ32,3 ሚሊዮን ዩሮ ከስዋንሲ ሲቲ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ተዛውሯል። የክሮሺያው ግብ አዳኝ ወጣት አንድሬ ክራማሪችም የእንግሊዙ ሌስተር ሲቲን ተቀላቅሏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውጤቶች የሚንደረደረው የዛሬው የስፖርት ጥንቅራችን ዝውውርን የሚመለከቱ እና ሌሎች ስፖርት ነክ ዜናዎችን አካቷል።

https://p.dw.com/p/1EMuJ
Africa Cup Fans
ምስል P. Pabandji/AFP/Getty Images

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ ቸልሲ ኃያልነቱን እያስመሰከረ ነው። 47 ነጥብ ይዞ ከሚከተለው ማንቸስተር ሲቲ በአምስት ነጥብ በልጦ በአንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቸልሲ ከትናንት በስትታያ ስዋንሲ ሲቲን 5 ለባዶ በማሳፈር ያገኘው ሦስት ነጥብ ተደምሮለት 52 ነጥቦችን ለመሰብሰብ ችሏል። ለቸልሲ በመጀመሪያው እና በ36ኛው ደቂቃ ግቦቹን ያስቆጠረው ኦስካር ነው። በ20ኛው እና በ34ኛው ደቂቃ ደግሞ ዲዬጎ ኮስታ ተከታዮቹን ኹለት ግቦች ለማስቆጠር ችሏል። የማሳረጊያዋን አምስተኛ ግብ በ79ኛ ደቂቃ ላይ ለቸልሲ ከመረብ ያሳረፈው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው አንድሬ ሹርለ ነው።

39 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ አምስተኛ ላይ የሚገኘው አርሰናል ትናንት ማንቸስተር ሲቲን 2 ለዜሮ ሸኝቷል። ሁል ሲቲ በዌስትሐም ዩናይትድ 3 ለባዶ ተረትቷል። ሳውዝሐምፕተን 42 ነጥብ ሰብስቦ በደረጃ ሠንጠረዡ ሦስተኛ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ በ40 ነጥብ አራተና ደረጃ ላይ ተቆናጥል። ሊቨርፑል 35 ነጥብ ይዞ 8 ደረጃ ላይ ይገኛል። ነገ ከቸልሲ ጋር ይጋጠማል።

አንድሬ ሹርለ
አንድሬ ሹርለምስል dapd

ወደ ስፔን ላሊጋ እና የጣሊያን ሴሪኣ ከመሻገራችን በፊት የአትሌቲክስ ዜና ላሰማችሁ። ትናንት በተለያዩ ኹለት ክፍለ ዓለማት በተከናወኑ የማራቶን ሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶችም በሴቶችም ድል ቀንቷቸዋል። ሂውስተን አሜሪካ ውስጥ በተደረገው የማራቶን ሩጫ ብርሃኑ ደገፋ 2:08:03 በማስመዝገብ፣ ጌቦ ቡርቃ በ2:08:12ኹለተኛ ወጥቷል። በሦስተኛ ደረጃ ውድድሩን ያጠናቀቀው ደበበ ቶሎሳ 2:09:07 አስመዝግቧል። በሴቶች ውድድር ኢትዮጵያውያቱ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ደረጃን ተቆጣጥረዋል። የብር ጓል አራጌ በ2:23:23 1ኛ ወጥታለች። ጉቴኒ ሾኔ በ2:23:32 ኹለተኛ እንዲሁም ብሩክታይት ደገፋ 2:23:51 በማስመዝገብ ሦስተኛ ሆናለች።

ህንድ ውስጥ በተከናወነው የሙምባዩ ማራቶን ሩጫ ተስፋዬ አበራ በ2:09:46 አንደኛ ደረጄ ደበሌ በ2:10:31 ኹለተኛ ሲወጡ ኬኒያዊው ሉኬ ኬቢት በ2:10:57 ሦስተኛ ለመሆን ችሏል። በሴቶች የማራቶን ሩጫ ድንቅነሽ መካሻ በ2:30:00 አንደኛ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ቁመሺ ሲቻላ በ2:30:56 ኹለተኛ፣ ማርታ መርጋ ደግሞ በ2:31:045 ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች።

የማራቶን ሯጮች
የማራቶን ሯጮችምስል Fotolia/ruigsantos

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ ግራናዳን 2 ለባዶ አሸንፏል። ባርሴሎና ዴፖርቲቮ ላ ኮሩናን 4 ለዜሮ እንደማይሆን አድርጓል። በዚህ ጨዋታ ኮከቡ ሊዮኔል ሜሲ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሐትሪክ ሠርቷል። መሪው ሪያል ማድሪድ ጌታፌን 3 ለምንም ረትቷል። ኤልሼ ሌቫንቴን 1 ለባዶ አሸንፏል። ማላጋ በሴቪላ 2 ለባዶ ተረትቷል። የደረጃ ሠንጠረዡን ሪያል ማድሪድ በ45 ነጥብ ይመራል። ባርሴሎና በ44 ይከተላል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ41 ይሰልሳል።

በጣሊያን ሴሪኣ ደግሞ ጁቬንቱስ ሔላ ቬሮናን 4 ለምንም ድባቅ መትቷል። ፓሌርሞ ከኤ ኤስ ሮማ አንድ እኩል ተለያይቷል። ላትሲዮ በኒያፔል 1 ለምንም ተሸንፏል።

የኢቦላ ስጋት በአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታ?

የኢኳቶሪያል ጊኒ መዲና ማላቦ አየር ማረፊያ። መንገደኞች በአዲስ መልክ በተሰራው የአየር መንገዱ አስፋልት ላይ እያቀኑ ነው። የአየር ማረፊያው የውስጠኛው ክፍል አነስ ያለ ነው።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ሠንደቅ-ዓላማ
የኢኳቶሪያል ጊኒ ሠንደቅ-ዓላማምስል picture alliance/ANP

በመግቢያው ላይ ማሪያ ሬይስ ሳንቶስ የተባለች የህክምና ባለሙያ አስቆመችን። ነጭ ጋዋን የለበሰችው ይህች ወጣት የህክምና ባለሙያ በያዘችው የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሣሪያ አዲስ ገቢ መንገደኞችን በመላ ትለካለች።

«በእዚህ የሰውነት ሙቀት መጠን ከ38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከፍ አለማለቱን እንለካለን። ማንኛውም ሰው ከፍተኛ ትኩሳት የሌለበት መሆኑን እናጣራለን።»

በመንገደኞች ላይ የኢቦላ ተሐዋሲ ይኑር አይኑር ለማወቅ የማጣራቱ ሥራ ኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል። እንደውም ካለፉት ወራቶች አንስቶ ይኽ እለት ከእለት ድርጊት ሆኗል። እንደ አምባሳደሪት ማሪ ክሩዝ ገለጣ ከሆነ በተለይ ባለፈው ሰኔ ወር ሀገሪቱ ባስተናገደችው የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ወቅት ይኽ የማጣራቱ ሥራ ውጤታማ ነበር።

«አሁን ከፊታችን ባሉት ጨዋታዎች የተነሳ የማጣራቱን ሥራ አጠናክረነዋል። በርካታ ድንኳኖችን አዘጋጅተናል። የህክምና ባለሙያዎች ሌሎች ሠራተኞች በአየር ማረፊያዎች እና የፍተሻ ኬላዎች በርከት እንዲሉ አድርገናል። መንገደኞች ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከመግባታቸው በፊት የኢቦላ ማጣራት ሥራ እናከናውናለን። በእዚህ እንኳን እንተማመናለን። ተሐዋሲው መዛመት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ አንዳችም የኢቦላ ተጠርጣሪ አላጋጠመንም። ይኽ ይቀየራል ብለን አናስብም።»

የኢኳቶሪያል ጊኒ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን
የኢኳቶሪያል ጊኒ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንምስል picture-alliance/dpa/Stringer

የኢቦላ ተሐዋሲ በምዕራብ አፍሪቃ ሦስት ሃገራት በአሁኑ ወቅት ከ8,000 በላይ ሰዎችን ለኅልፈተ ሕይወት ዳርጓል። የአፍሪቃ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዕቅድንም በተወሰነ መልኩም ቢሆን አዛብቶበታል። የዘንድሮውን ጨዋታ ለማሰናዳት የተመረጠችው ሀገር ሞሮኮ ውድድሩ ሊጀመር ኹለት ወራት ሲቀሩት ማዘጋጀት እንደማትችል አስታውቃለች። የሞሮኮ ምክንያት ኢቦላ ሊዛመትብኝ ይችላል የሚል ነበር። ጨዋታውን ለማዘጋጀት አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉት እንደ ደቡብ አፍሪቃ እና ሱዳን ያሉ ሃገራት ራሳቸውን ገለል ማድረጉን ነው የመረጡት።

«ኢኳቶሪያል ጊኒ የአፍሪቃ ዋንጫን ካሰናዱ ከጥቂት ሃገራት መካከል አንዷ ነበረች። ይኽ በአፍሪቃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የሚታደምበት ጨዋታ ነው። ይኽን ጨዋታ የማሰናዳት ፍቃድ ለማግኘት በርካታ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል። ስለዚህ የነበራቸው አማራጭ ወይ መሠረዝ አለያም ዝግጁ ለሆነ አንድ ሀገር መስጠት ነበር። ኢኳቶሪያል ጊኒ ደግሞ አስተማማኝ አማራጭ ነበረች።»

ሲል የስፖርት ጋዜጠኛው ኤሜኬ ኤንያዲኬ ተናግሯል።ቃታር በበኩሏ ካልቻላችሁ የአፍሪቃ ዋንጫን እኔ ላሰናዳላችሁ ፈቃዴ ነው ስትል አስታውቃ ነበር። ሆኖም የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎችን በሌላ አህጉር ማስተናገድ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያን ጋቦን ውስጥ እንደማዘጋጀት ማለት ነው። የአፍሪቃ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቃል አቀባይ ጁኒየር ቢንያም የኢቦላ ስርጭት ጨዋታዎቹን እንደማይረብሽ ተናግረዋል።

«የኢቦላ ተሐዋሲ ስርጭት የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎችን ይረብሻል ብዬ አላስብም የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ካለፈው ሚያዝያ አንስቶ አከናውነናል። ከእግር ኳስ ጋር በተገናኘ የተመዘገበ አንዳችም የኢቦላ ክስተት የለም።»

ንኮሣዛና ድላሚኒ ዙማ
ንኮሣዛና ድላሚኒ ዙማምስል picture-alliance/dpa/ Y.Valat

የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበሪት ድላሚኒ ዙማ በበኩላቸው በኢቦላ ተሐዋሲ የተነሳ ማንኛውም ሰው ላይ መገለል እንዳይከሰት ማሳሰቢያቸውን አሠምተዋል።

«ማንንም የምናገልበት ምክንያት የለም። ምክንያቱም እኛው እራሳችን ማግለል ከጀመርን፥ መላው አፍሪቃ ከአፍሪቃ ውጪ መገለሉ አይቀርም።»

በኢኳቶሪያል ጊኒ አየር መንገዱ ውስጥም ቢሆን ማንኛውም መንገደኛ ያለምንም ልዩነት የኢቦላ ተሐዋሲ ምልክት ይኑርበት አይኑርበት ለማወቅ የማጣራት ምርመራ ይደረግለታል። እጅግ በርካታ ደጋፊዎች ጨዋታውን ወደሚያዘጋጀው ሀገር ይጎርፉ ይሆናል የሚለው አስተያየት ለጊዜው ቢያንስ ከጥርጣሬ የሚዘል አልሆነም። ያ ታዲያ ሙሉ ለሙሉ በኢቦላ ፍራቻ ነው ለማለት አያስደፍርም። ይልቁንስ በኢኳቶሪያል ጊኒ የመጠለያ እጥረት እና የቪዛ አገልግሎቱ እጅግ መወደድ እንደምክንያት ሊወሰድ የሚችል ነገር ነው።

የባታ ስታዲየም- ኢኳቶሪያል ጊኒ
የባታ ስታዲየም- ኢኳቶሪያል ጊኒምስል picture-alliance/dpa/abaca

ዝግጅቱ የት ይሁን በሚል ውዝግብ አስነስቶ የነበረው 30ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች በኢኳቶሪያል ጊኒ ከቅዳሜ አንስቶ ጀምሯል። በመክፈቻው የመጀመሪያ ጨዋታ ኮንጎ ብራዛቪልን የገጠመችው አስተናጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ ቀድማ ባገባችው አንድ ግብ ስትመራ ነበር። ሆኖም ባለቀ ሠዓት በተቆጠረባት አንድ ግብ የማሸነፍ እድሏን አምክናለች። በኹለተኛው ጨዋታ ጋቦን ቡርኪናፋሶን 2 : 0 አሸንፋለች። የጀርመን ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቡድን አጥቂ ፒዬር ኤሜሪክ እና ማሊክ ኢቮና ናቸው ለጋቦን ግቦቹን ያስቆጠሩት። ጨዋታው እሁድ እለትቀጥሎ በምድብ ለ ዛምቢያ - ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አንድ እኩል ተለያይተዋል። በመቀጠል የተፋለሙት ቱኒዚያእና ኬፕቬርዴ በተመሳሳይ አቻ ተለያይተዋል። ዛሬ የሚከናወኑት ኹለትም ጨዋታዎች እጅግ በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው። ፍልሚያው በጋና እና በሴኔጋል እንዲሁም በአልጄሪያ እና ደቡብ አፍሪቃ መካከል ነው።

የአይቮሪኮስቱ አጥቂ ዊልፍሬድ ቦኒ ከስዋንሲ ሲቲ ወደ ማንቸስተር ሲቲ የተዛወረው በ32,3 ሚሊዮን ዩሮ ነው። የክሮሺያው ግብ አዳኝ የ23 ዓመቱ ወጣት አንድሬ ክራማሪችም የእንግሊዙ ሌስተር ሲቲን በ13,59 ሚሊዮን ዩሮ ተቀላቅሏ። ይኽ ወጣት በእዚህ ዓመት ለሚጫወትበት ቡድን እና ለክሮሺያ እስካሁን 28 ግቦችን አስቆጥሯል።

ዳካር ውስጥ በተደረገው የመኪና ሽቅድምድም ደግሞ የቃታሩ ተወላጅ የ44 ዓመቱ ኧል አቲያህ ለኹለተኛ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን ችሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ