1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 13 2004

የአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ባለፈው ሰንበት ብዙ አስደናቂ ውጤቶች የታዩበት ነበር።

https://p.dw.com/p/Rsfy
ምስል picture-alliance/ dpa

በእግር ኳስ እንጀምርና ሰንበቱ በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ ለአንዳንድ ሃያላን ቡድኖች ሲበዛ ፈታኝ ሆኖ ነበር ያለፈው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ የከተማ ተፎካካሪውን መንቼስተር ዩናይትድን 6-1 በመቅጣት አመራሩን አጠናክሮ በሻምፒዮንነት አቅጣጫ ለመቀጠል ቆርጦ መነሣቱን አስረግጧል። ለማኒዩ ሽንፈቱን ይበልጥ መሪር የሚያደርገው በተለይም በገዛ ሜዳው በኦልድ-ትሬፎርድ ስታዲዮም እንዳልሆነ ሆኖ መረታቱ ነው። ለባለድሉ ለማንቼስተር ሢቲይ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ማሪዮ ባሎቴሊና ኤዲን ጄኮ እያንዳዳቸው ሁለት፤ እንዲሁም ሤርጆ አጉዌሮና ዴቪድ ሢልቫ ናቸው።
ላለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ለማንቼስተር ዩናይትድ በትናንቱ ሽንፈት በሜዳው ለ 18 ወራት ጸንቶ የቆየው የድል ጉዞ ሲቋረጥ ለሢቲይ ደግሞ የፕሬሚየር ሊግ አመራሩን ወደ አምሥት ነጥቦች ከፍ እንዲያደርግ በጅቶታል። ሶሥተኛው ቼልሢይ ሁሴ ቦሲንግዋና ዲዲየር ድሮግባ ገና በመጀመሪያው አጋማሽ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተውበት በዘጠኝ ሰዎች ሲጫወት በኩዊንስ-ፓርክ-ሬንጀርስ 1-0 በመሸነፍ ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ለማለት የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ኒውካስል-ዩናይትድ በተመሳሳይ 19 ነጥቦች አራተኛ ነው። በጎል አግቢነት የሁለቱ ቀደምት የማንቼስተር ክለቦች አጥቂዎች ሴርጆ አጉዌሮና ዌይን ሩኒይ እኩል ዘጠኝ አስቆጥረው ይመራሉ።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ጥንካሬው ያልተጠበቀው የዘንድሮው አስደናቂ ክለብ ሌቫንቴ በዚህ ሰንበትም ቪላርሬያልን 3-0 በመርታት በሃያ ነጥቦች መምራቱን ቀጥሏል። ሬያል ማድሪድ ደግሞ ማላጋን 4-0 ሲያሸንፍ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። ለክለቡ ከአራት ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበር። ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የሚታገለው ባርሤሎና በአንጻሩ በገዛ ሜዳው ከሤቪያ ባዶ-ለባዶ በመለያየት ከሁለት ወደ ሶሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። በተረፈ ሤቪያ አራተኛ ሲሆን አምሥተኛው ደግሞ ቫሌንሢያ ነው። በጎል አግቢነት የሬያል ኮከቦች ሮናልዶ አሥር፤ እንዲሁም ሂጉዌይን ዘጠኝ በማስቆጠር በመከታተል ይመራሉ።

Fussball 1. Bundesliga Hannover 96 Vs. FC Bayern Muenchen
ምስል dapd

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር በፍጹም የበላይነት ሲመራ የቆየው ባየርን ሙንሺን ትናንት ከአሥር ግጥሚያዎች በኋላ ለሁለተኛ ሽንፈቱ በቅቷል። የክለቡን የድል ጉዞ 2-1 በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን የገታው ሃኖቨር 96 ነው። ባየርን እርግጥ ከሽንፈቱ በኋላም በ 22 ነጥቦች ለብቻው የሚመራ ሲሆን ሣምንቱ የበጀው በተለይም ላለፈው ጊዜ ሻምፒዮን ለዶርትሙንድ ነበር ለማለት ይቻላል። ቡድኑ ኮሎኝን 5-0 በመርታት ባየርንን በሁለት ነጥቦች ልዩነት ሲቃረብ ሻልከም ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። ቀደምቱ ባየርን ዘንድሮ ለሻምፒዮነት የረባ ተፎካካሪ የለውም እየተባለ ከቆየ በኋላ አሁን የማቆልቆል አዝማሚያ እየያዘ ይሆን? ቡድኑ ለመሆኑ ምን ያህል ጠንካራ ነው? ማንስ ሊፎካከረው ይችላል? በነዚህ ነጥቦች ያነጋገርኩት የዶቼ ቬለ የጀርመንኛ ክፍል የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጅ አርኑልፍ በትቸር እንደሚያምነው ከሆነ ባየርን ጨርሶ አይዳከምም።

“በፍጹም! ባየርን ሙንሺን ካለፈው ሻምፒዮን ከዶርትሙንድ የሶሥት ነጥቦች ብልጫ ሲኖረው አሁንም የሊጋው መሪ ሆኖ ነው የሚቀጥለው። እርግጥ በትናንቱ ሽንፈት በጥቂቱ ተገትቷል። ሆኖም ትናንትም ቢሆን መጥፎ አልነበረም የተጫወተው። ግን ያሳዝናል ብዙ የጎል ዕድሎቹን መጠቀሙ ሳይሳካለት ቀርቷል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የገባቸበት ወሣኝ ሁለተኛ ጎል ደግሞ የተደረበች በመሆኗ የምትያዝ አልነበረችም። ምን ማድረግ አይቻልም። እናም ባየርን ሙንሺን በበላይነት ቡንደስሊጋውን መምራት እንደሚቀጥል አምናለሁ። የትናንቱ ሽንፈት ሂደቱን ገታ ያደረገ ነበር። ይሁን እንጂ የማቆልቆል አዝማሚያን የሚያሳይ አይደለም”

ባየርን ባለፈው ማክሰኞም በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ከናፖሊ እኩል-ለእኩል ብቻ ነበር የተለያየው። ቀደም ሲል ግን ብዙዎች ታዛቢዎች ግጥሚያው ለጀርመኑ ቀደምት ክለው ቀላል እንደሚሆን ነበር የተነበዩት። ግን ይህ አልሆነም። ምንድነው ምክንያቱ? አርኑልፍ በትቸር!

“ለነገሩ ከናፖሊም ጋር ቢሆን ባየርን ያሣየው ጨዋታ ያን ያህል መጥፎ አልነበረም። እርግጥ ከእኩል-ለአኩል ውጤት አላለፈም። የሆነው ሆኖ በናፖሊ ደጋፊዎች ጩኸት ታጅቦ በውጭ መጫወቱ መዘንጋት የለበትም። ቡድኑ አመራሩን ወደ 1-1 የለወጠችው ጎል ከተቆጠረችበት በኋላ ደግሞ ውጤቱን በዚያው ለማቆየት መከላከሉን ነው የመረጠው። ባየርን ሙንሺን ምድቡን በሰባት ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ገና በሜዳው ሁለት ግጥሚያዎች ይቀሩታል። በጥቅሉ ቡድኑ ኢጣሊያ ውስጥም ሆነ እዚህ ያሳየው ጨዋታ ብዙም የሚያስከፋ አልነበረም። ጥቂት ዕድል ከድቶታል። ግን ቀውስ ላይ እየወደቀ አይደለም”

ባየርን ሙንሺን እንግዲህ በተለይ በቡንደስሊጋው ውድድር በሻምፒዮንነት አቅጣጫ መገስገሱን እንደሚቀጥል ሲታመን ጥያቄው በረባ ሁኔታ የሚፎካካረው ክለብ አለ ወይ ነው። በወቅቱ በአምሥት ነጥቦች ልዩነት ስድሥት ክለቦች ቀረብ ብለው የሚከተሉት ሲሆን ምናልባትም ከዶርትሙንድ በስተቀር ሌሎቹ አስፈላጊው ጥንካሬ አላቸው ለማለት እምብዛም አያስደፍርም።

“አዎን፤ ከባየርን ሙንሺን ጎን ዶርትሙንድ ተፎካካሪ የሚሆን እየመሰለ ነው። ክለቡ ያለፉትን ግጥሚያዎቹን በሙሉ በማሸነፍ ራሱን አጠናክሯል። በሌላ በኩል በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የሚገኝበት ሁኔታ የተለየ ነው። ከውድድሩ ወጪ መሆኑ አያጠራጥርም። በተረፈ ከዶርትሙንድ ሌላ ለሻምፒዮንነት የሚፎካከር ሌላ አንድም ቡድን አይታየኝም። ሻልከ ሶሥተኛ፣ ሃኖቨር አራተኛ፣ ሽቱትጋርት አምሥተኛ ሲሆኑ እነዚህ ክለቦች ለፉክክር የሚያበቃው ጽናት ይጎላቸዋል። ሻምፒዮናው ምንም እንኳ ዶርትሙንድ በዚህ የውድድር ወቅት ባየርን ሙንሺንን መቋቋም መቻሉ ቢያጠራጥርም በሁለቱ ፉክክር የሚለይለት ነው የሚመስለው”

ያለፈው ሻምፒዮን የዶርትሙንድ ተጫዋቾች ወጣቶች ሲሆኑ እርግጥ የባየርን መሰሎቻቸውን ያህል ልምድ የላቸውም። ፈጣን በሆነ የማጥቃት አጨዋወት ስልታቸው አቅማቸው እስከ ውድድሩ መጨረሻ መብቃቱም ሊየነጋግር ይችላል። እንደ አርኑልፍ በትቸር ግን ዶርትሙንድ ዘንድሮም በከፍተኛ ደረጃ መጫወት የሚችል ቡድን ነው።

“ባለፈው የውድድር ወቅትም እንደዚሁ ነበር የተጫወቱት። የማጥቃት፣ የመታገልና ብዙ የመሮጥ ስልት ነው የነበራቸው። አሁን ባለፈው ቅዳሜ ኮሎኝን 5-0 ሲያሸንፉ ደፍጥጠውት ነው ያለፉት ለማለት ይቻላል። እናም የአካል ድክመት ችግር ይገጥማቸዋል ብዬ አላስብም። እንዲያውም ከአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ስለሚወጡ ትኩረታቸውን በሙሉ በቡንደስሊጋው ላይ ሊያሳርፉ ይችላሉ። አሁን ሁለተኛው ቦታ ላይ ደርሰዋል። እና እስከ ውድድሩ መጨረሻም ላይ እንደሚቆዩ ነው የምገምተው”

ሂደቱ ምናልባትም በገናው ዕረፍት ዋዜማ የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ ጨርሶ ባይለይለት እንኳ በተወሰነ ደረጃ መልክ ሊይዝ ይችል ይሆናል። ለማንኛውም በአውሮፓ በየሊጋው ከተካሄዱት የሰንበት ግጥሚያዎች በኋላ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኡዲኔዘ አመራሩን ሲይዝ ላሢዮና ጁቬንቱስ በቅርብ ይከተሉታል። በፈረንሣይ ሻምፒዮና ፓሪስ ሣንት-ዣርማን በአመራሩ ሲቀጥል በሆላንድ አልክማር፤ እንዲሁም በፖርቱጋል ደግሞ ፖርቶ ቀደምቱ ናቸው።

BdT Berlin Marathon
ምስል AP

በአትሌቲክስ ባለፈው መስከረም የበርሊንን ማራቶን በትንፋሽ እጥረት የተነሣ አቋርጦ መውጣት ተገዶ የነበረው ሃይሌ ገ/ሥላሴ ትናንት በእንግሊዝ የበርሚንግሃም ታላቅ ሩጫ በቀላሉ በማሸነፍ የቀድሞ ጥንካሬውን ሊያሳይ በቅቷል። ኤሣ ራሼድ ሁለተኛ ሲወጣ ያለፈው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ሩጫ አራተኛ የሞሮኮው አብደራሂም ቡራምዳኔ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። ለሃይሌ ገ/ስላሴ ቀጣዩ ታላቅ ውድድር በፊታችን የካቲት ወር ጃፓን ውስጥ የሚካሄደው የቶኪዮ ማራቶን ነው።

Maria Sharapova FLASH-GALERIE
ምስል picture-alliance/dpa

ቴኒስ

በቴኒስ የስቶክሆልም-ኦፕን ፍጻሜ ግጥሚያ ፈረንሣዊው ጂል ሞንፊልስ የፊንላንድ ተጋጣሚውን ጃርኮ ኒሚነንን በሶሥት ምድብ ጨዋታ ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ለዓመቱ የመጀመሪያ ድሉ በቅቷል። ሞንፊልስ በዚሁ ድል በመጪው ወር በአገሩ በሚካሄደው የፓሪስ ውድድር ለማሸነፍ የበለጠ ተሥፋ ጥሏል። ከዚሁ ሌላ በሞስኮ የክሬምሊን ዋንጫ ውድድር በወንዶች ፍጻሜ የሰርቢያ ተጫዋቾች ያንኮ ቲፕሣሬቪችና ቪክቶር ትሮይስኪ እርስበርስ ሲገናኙ ቲፕሣሬቪች አሸናፊ ሆኗል። በሴቶች ደግሞ የስሎቫኪያ ዶሚኒካ ቺቡልኮቫ የኤስቶኒያ ተጋጣሚዋን ካያ ካኔፒን ሁለት-ለአንድ ረትታለች።
በተረፈ ዛሬ በወጣው የዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ በወንዶች የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች በ 13,860 ነጥቦች በአንደኝነት የሚመራ ሲሆን የስፓኙ ራፋኤል ናዳል ሁለተኛ፤ እንዲሁም የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ ሶሥተኛ ናቸው። ጆኮቪች በሰፊ ነጥብ ስለሚመራ ለረጅም ጊዜ ቀደምት ሆኖ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። በሴቶች የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪና ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ ግንባር ቀደም እንደሆኑ ሲቀጥሉ የቼክ ሬፑብሊኳ ፔትራ ክቪቶቫ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ልትል በቅታለች። በነገራችን ላይ ማሪያ ሻራፖቫ በወቅቱ ጥንካሬዋ ከቀጠለች በቅርቡ አንደኝነቱን ለመያዝ ያላት ዕድል ከፍተኛ ነው።

ያለፈው ሰንበት በሞተር ቢስኪሌት ስፖርት መድረክ ላይ በደረሰ ዘግናኝ አደጋ አሳዛኝ ሆኖም ነው ያለፈው። የ 24 ዓመቱ ኢጣሊያዊ ማርኮ ሢሞንቼሊ በማሌዚያ-ሴፓንግ ግራንድ-ፕሪ በሁለተኛው ዙር ላይ ከተገለበጠ በኋላ በሁለት ሞተር ቢስክሌቶች ተገጭቶ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱን አጥቷል። ወጣቱን ስፖርተኛ ለሞት ያበቃው በተለይም የአናት መከላከያ ቆቡ መውለቁ ነው። ያሳዝናል፤ የስፖርቱ የቅርብ አዋቂዎች እንደሚሉት በሞተሩ ስፖርት ውድድር ሙሉ የደህንነት ዋስትናን ማረጋገጥ የሚቻል ነገር አይደለም።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ