1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 26 2003

ብራዚል ውስጥ ከሶሥት ዓመታት በኋላ ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳሳ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የማጣሪያው ዙር የምድብ ዕጣ ባለፈው ቅዳሜ ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ ላይ ወጥቷል።

https://p.dw.com/p/RdSB
ምስል dapd

በአውሮፓው ዘጠኝ ማጣሪያ ምድቦች ውስጥ አንዳንድ ከበድ ያሉ ዕጣዎች ሲወጡ ከነዚሁ መካከል ጠንካሮቹ የቀድሞዎቹ የዩጎዝላቪያ ሬፑብሊኮች ሰርቢያና ክሮኤሺያ የሚገናኙበት ምድብ-አንድ ነው። የሰርቢያው አሰልጣኝ ቭላዲሚር ፔትሮቪች ምድቡ ጠንካራውና እያንዳንዱ ጨዋታ ከባድ የሚሆንበት እንደሆነ ነው ዕጣው ከወጣ በኋላ የተናገረው። ይሄው ምድብ ቤልጂግን፣ ስኮትላንድን፣ ማቄዶኒያንና ዌልስንም የሚጠቀልል ሲሆን በእርግጥም ፈታኝ እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም።
በምድብ-ሁለት ኢጣሊያ ዴንማርክንና ቼክ ሬፑብሊክን የመሳሰሉ ጠንካራ ተፎካካሪዎች የሚጠብቋት ሲሆን የዋንጫው ባለቤት ስፓኝም በምድብ-ዘጠኝ ከፈረንሣይና ከቤላሩስ መታገል ይኖርባታል። እንግሊዝም ከሞንቴኔግሮ፣ ከኡክራኒያና ከፖላንድ ጋር ፈታኝ ምድብ ነው የገጠማት። በተቀረ ሌሎቹ ቀደምት አገሮች ጀርመን፣ ኔዘርላንድ ወይም ፖርቱጋል ከወዲሁ ቀንቷቸዋል ለማለት ይቻላል። ይሁንና ያልተጠበቀ ነገር ሊከሰትም የማይችልበት ምክንያት የለም።

በደቡብ አሜሪካ ክልል አስተናጋጇ ብራዚል ያለ ማጣሪያ ለፍጻሜው ውድድር ስታልፍ አሠልጣኙ ማኖ ሜኔዜስ የቡድኑ ግዴታ ማንኛውንም ተጋጣሚ ለመቋቋም በሚገባ መዘጋጀት መሆኑን አስገንዝቧል። የአካባቢው የመጀመሪያ የምድብ ግጥሚያዎች በፊታችን ጥቅምት ወር መግቢያ ላይ ይካሄዳሉ። በዚሁ አንድ-ወጥ የደቡብ አሜሪካ ማጣሪያ ምድብ ውድድር የሚሳተፉት ዘጠኝ አገሮች አርጄንቲና፣ ቦሊቪያ፣ ቺሌ፣ ኮሉምቢያ፣ ኤኩዋዶር፣ ፓራጉዋይ፣ ፔሩ፣ የዘንድሮዋ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኡሩጉዋይና ቬኔዙዌላ ናቸው። የማጣሪያው ውድድር እስከ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. የሚዘልቅ ሲሆን በመጨረሻ በቀጥታ ለፍጻሜው የሚያልፉት ቀደምቱ አራት አገሮች ይሆናሉ። አምሥተኛው ደግሞ ከሰሜን፣ ማዕከላዊና ካራይብ ማሕበራት ኮንፌደሬሺን ከኮንካካፍ አካባቢ አራተኛ ጋር ተጋጥሞ በማሸነፍ የማለፍ ዕድል ይኖረዋል።

ኮንካካፍን ካነሣን በአካባቢው ማጣሪያ ሜክሢኮና ዩ.ኤስ.አሜሪካ እንደተለመደው ትልቅ የማለፍ ዕድል ያላቸው ሲሆን ኮስታ ሪካና ኤል ሣልቫዶርም ተሥፋ ሊጥሉ ይችላሉ። የእሢያው ማጣሪያ በአምሥት ምድብ ሲደለደል በምድብ-አንድ ቻይና ከዮርዳኖስ፣ ከኢራቅና ከሢንጋፑር ትጋጠማለች። ደቡብ ኮሪያ ከኩዌይት፣ ከተባበሩት አረብ ኤሚሮችና ከሊባኖስ ስትመደብ ጃፓን ደግሞ የምትፎካከረው ከኡስቤኮች፣ ከሶሪያና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ነው። ይሄኛው ከሁሉም ጠንከር ያለው ምድብ ይመስላል። አውስትራሊያም በምድብ-አራት ከሳውዲት አረቢያ፣ ከኦማንና ከታይላንድ ጋር ቀለል ያለ ምድብ ገጥሟታል።

የአፍሪቃው ማጣሪያም ከሁለተኛው ዙር አንስቶ በአሥር ምድቦች የሚካሄድ ሲሆን ለዚሁ ውድድር ለመድረስ 24 አገሮች ቀዳሚ ግጥሚያ ይጠብቃቸዋል። ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር ሶማሊያን ማሸነፍ የሚኖርባት ሲሆን ኤርትራ ከሩዋንዳ፣ ኬንያ ከሴይሼልስ፣ ቶጎ ከጊኒ ቢሣው፣ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ከስዋዚላንድ ይጋጠማሉ። ኢትዮጵያ ካለፈች በሁለተኛው ዙር በምድብ-አንድ ከደቡብ አፍሪቃ፣ ከቦትሱዋናና ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሬፑብሊክ ጋር ነው የምትደለደለው። ይህም ብዙም የከፋ ዕጣ አይመስልም። በነገራችን ላይ ኤርትራም ሩዋንዳን ካሸነፈች በምድብ-ስምንት ከአልጄሪያ፣ ከማሊና ከቤኒን ጋር መሰለፍ ትችላለች።
እነዚሁ የመጀመሪያው ዙር ግጥሚያዎች የሚካሄዱት በፊታችን ሕዳር ወር ውስጥ ነው። በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ላይ ካተኮርን ባለፈው አርብና ቅዳሜ ደግሞ የክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚዮች ተካሂደዋል። በምድብ-አንድ የሱዳኑ አል-ሂላል የሞሮኮውን ራጃ-ካዛብላንካን 1-0 ሲረታ በምድብ-ሁለትም የቱኒዚያው ኤስፔራንስ አል-አህሊ ካይሮን በተመሳሳይ ውጤት አሸንፏል። በምድብ-ሁለት ሌላ ግጥሚያ ደግሞ የሞሮኮው WAC ካዛብላንካ የአልጄሪያ ተጋጣሚውን MC አልጀርን 4-0 ሸኝቷል። ከነዚህ ግጥሚያዎች በኋላ ምድብ-አንድን አል-ሂላል በአራት ነጥብ የሚመራ ሲሆን በምድብ-ሁለት ቀደምቱ ካዛብላንካና ኤስፔራንስ ናቸው።

DFB-Pokal FC Heidenheim - Werder Bremen Flash-Galerie
ምስል dapd

የጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር

በዚህ በጀርመን ደግሞ የቡንደስሊጋው የ 2011/12 የውድድር ወቅት በፊታችን አርብ የሚጀመር ሲሆን ባለፈው ሰንበት ከወዲሁ የመጀመሪያ የአገሪቱ ፌደሬሺን ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ዙር ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። በዚሁ ውድድር ዘንድሮም እንደተለመደው ገና ከጅምሩ ዳዊት ጎልያድን ማሸነፉ አልቀረም። ከቀደምቱ የቡንደስሊጋ ክለቦች መካከል ለምሳሌ ብሬመን፣ ሌቨርኩዝንና ቮልፍስቡርግ በብዙ ደረጃ ዝቅተኛ በሆኑ ክለቦች ተቀጥተው የውርደት ስንብት ነው ያደረጉት። ቮፍስቡርግ በኤር.ቤ.ላይትሲግ 3-2 ሲሽነፍ ብሬመን በሶሥተኛው ዲቪዚዮን ክለብ በሃይደንሃይም 2-1 መቀጣቱ ክለቡን ከከፋ ቀውስ ላይ ሊጥል የሚችል ነው። ማኔጀሩ ክላውስ አሎፍስ በሁኔታው ግራ ከመጋባቱ ባሻገር የክለቡ ሽንፈት የውርደትን ያህል እንደሆነ ከመግለጽም አልተቆጠበም።
“እግር ኳሰ ስህተት ሊሰራበት የሚችል ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን እኛም ዛሬ በወሣኙ ሰዓት ላይ ይህንኑ አድርገናል። በመጨረሻ ደግሞ ሁኔታውን ልንቀይረው አልቻልንም። ይህ እርግጥ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው። ሆኖም ግን ትልቅ ውርደት ነው የደረሰብን”

ያለፈው የቡንደስሊጋ ውድድር ወቅት ሁለተኛ ሌቨርኩዝን የደረሰበት ውርደት ደግሞ ከሁሉም የከፋው ነበር። ቡድኑ ዲናሞ ድሬስደንን 3-0 ከመራ በኋላ ያለቀለት መስሎ የታየ ድሉን በመጨረሻ አራት ጎሎች ተቆጥሮበት በ 4-3 ውጤት አስረክቧል። ሌሎቹ ቀደምት የቡንደስሊጋ ክለቦች ዶርትሙንድ፣ ሻልከና መሰሎቻቸው የበላይነት በማሣየት በቀላሉ ወደ ሁለተኛው ዙር ሲሻገሩ ባየርን ሙንሺን ደግሞ ዛሬ ማምሻውን በሁለተኛ ዲቪዚዮን ተጋጣሚው በብራውንሽዋይግ ጉድ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል። የሚቀጥለው ዙር ዕጣ የሚወጣው በፊታችን ቅዳሜ ነው። ሌላው አስደናቂ የጀርመን የእግር ኳስ ዜና ዩርገን ክሊንስማን የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆኖ መሰየሙ ነው። ክሊንስማን በ 2006 ዓ.ም. የዓለም ዋንጫ ውድድር አስተናጋጁን የጀርመንን ብሄራዊ ቡድን እስከ ግማሽ ፍጻሜ ማድረሱ ይታወሣል።

አትሌቲክስ

ባለፈው አርብ ምሽት ስቶክሆልም ላይ በተካሄደው የዳያመንድ ሊግ አትሌቲክስ ውድድር ጃማይካውያንና አሜሪካውያን በአጭር ርቀት፤ እንዲሁም ኬንያውያን በመካከለኛና ረጅም ሩጫ ቀደምቱ ሆነው ታይተዋል። በወንዶች ሁለት መቶ ሜትር ጃማይካዊው የዓለም ሻምፒዮን ዩሤይን ቦልት ሲያሸንፍ በአራት መቶ ሜትርም የአገሩ ልጅ ጀርሜይን ጎንዛሌስ ቀዳሚ ሆኗል። ጃማይካ በሴቶች አራት መቶ ሜትር መሰናክልና በስምንት መቶ ሜትርም ፍጹም የበላይነት ስታሳይ በሴቶች መቶ ሜትር ደግሞ አሜሪካዊቱ ካሜሊታ ጄተር አሸንፋለች።

የኬንያ አትሌቶች ከ 1,500 እስከ አምሥት ሺህ ሜትር መላውን ድል ሲጠቀልሉ በወንዶች 1,500 ሜትር ሢላስ ኪፕላጋትና አስቤል ኪፕሮፕ በመከታተል አሸንፈዋል። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ሌላው ኬንያዊ ፓውል ኮች አንደኛ ሲሆን በሴቶች አምሥት ሺህ ሜትር ደግሞ ቪቪየን ቼሩዮት፣ ሣሊይ ኪፕየጎና ሲልቪያ ኪቤት በመከታተል ለድል በቅተዋል። በሴቶች ስምንት መቶ ሜትር ጃማይካዊቱ ሢንክሌር አሸንፋለች።

Formel 1 Ungran Grand Prix Flash-Galerie
ምስል dapd

ፎርሙላ-አንድ/ቴኒስ/ዋና

ትናንት ሁንጋሪያ ውስጥ የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ የብሪታኒያው ዘዋሪ ጄሰን በተን ሆኗል። ያለፈው ውድድር ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ምንም እንኳን ሁለተኛ ቢወጣም የቅርብ ተፎካካሪው ሉዊስ ሃሚልተን በአራተኝነት በመወሰኑ ተጎጂ አልሆነም። የነጥብ ልዩነቱን እንዲያውም ከፍ ሊደርግ በቅቷል። ይሁን እንጂ ዜባስቲያን ፌትል ቀዳሚ ባለመሆኑ ጥቂትም ቢሆን ቅር መሰኘቱ አልቀረም።

“በአጠቃላይ ሲታይ የዛሬው ውጤት ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። በሁለተኛው ቦታ እርካታ ነው የሚሰማኝ። ሆኖም ግን ማሽነፍም እችል እንደነበር ሳስበው ጥቂትም ቢሆን መቆጨቴ አልቀረም”

በእርግጥም ፌትል ከመጀመሪያው ቦታ መነሣቱ ሲታሰብ በመቀደሙ መቆጨቱ ብዙ አያስደንቅም። ለማንኛውም እሽቅድድሙን በሶሥተኝት የፈጸመው የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ነበር። ከትናንቱ እሽቅድድም በኋላ ፌትል በአጠቃላይ 234 ነጥቦች ሲኖሩት የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር በ 149 በሁለተኝነት ይከተለዋል። ሉዊስ ሃሚልተን በ 146 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው።

በሎስ አንጀለስ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ የላትቪያው ኤርኔስትስ ጉልቢስ የአሜሪካ ተጋጣሚውን ማርዲይ ፊሽን ትናንት በሶሥት ምድቦች ጨዋታ 2-1 በመርታት ለሁለተኛ የውድድር ድሉ በቅቷል። በካሊፎርኒያ ዓለምአቀፍ የሴቶች ውድድር ደግሞ አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ የፈረንሣይዋን ማሪዮን ባርቶሊን በሁለት ምድብ ጨዋታ በማሸነፍ ካለፈው ዓመት የዊምብልደን ቴኒስ በኋላ እንደገና ለውድድር ድል በቅታለች።

ዘገባችንን በዋና ለማጠቃለል ቻይና-ሻንግሃይ ላይ ሲካሄድ የቆየው የዓለም የዋና ሻምፒዮና ትናንት በአሜሪካ የሜዳሊያ ድል ተፈጽሟል። አሜሪካ ለ 17 ወርቅ ሜዳሊያዎች ስትበቃ አስተናጋጇ ቻይናም በ 15 ወርቅ ሁለተኛ ሆናለች። በስምንት ወርቅ ሶሥተኛ ሩሢያ፣ እንዲሁም በአራት ወርቅ አራተኛ ብራዚል! ውድድሩ ከሁለት ዓመታት በፊት በሮማ ከታየው ሲነጻጸር አዲስ ክብረ-ወሰን ብርቅዬ ሆኖ የተገኘበት ነበር። ያኔ 43 አዳዲስ ክብረ-ወሰኖች ሲመዘገቡ የዘንድሮው በሶሥት ብቻ ተወስኖ ቀርቷል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ