1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 1 2003

በኢጣሊያ የእግር ኳስ ሊጋ ኤ.ሢ.ሚላን ሰንበቱን ቀድሞ ለሻምፒዮንነት በቅቷል። ማንቼስተር ዩናይትድና ባርሤሎናም ድላቸውን ከፍጻሜ ለማድረስ ምንም ያህል አልቀራቸውም።

https://p.dw.com/p/RMot
ምስል dapd

መገባደጃው በተቃረበው በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ባለፈው ሰንበት ኤ.ሢ.ሚላን ከሰባት ዓመታት በኋላ የከተማ ተፎካካሪውን ኢንተርን ከዙፋኑ በማስወረድ የኢጣሊያ ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። ኤ.ሢ.ሚላን የኢጣሊያው ሤሪያ-አ ውድድር ሊያበቃ ገና ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ለዚህ ክብር የበቃው ባለፈው ቅዳሜ ከሮማ ጋር ባዶ-ለባዶ በመለያየት የምታስፈልገውን አንዲት ነጥብ ከወሰደ በኋላ ነው። ባለፉት ዓመታት ሻምፒዮንነቱን በሞኖፖል ይዞ የኖረው ኢንተር ሚላን በአንጻሩ ፊዮሬንቲናን 3-1 ቢያሸንፍም በሁለተኝነት ተወስኖ መቅረቱ ግድ ነው የሆነበት። ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን እንዳይከለስ በሚታገለው በሌቼ ባልተጠበቀ ሁኔታ 2-1 የተረታው ናፖሊ ደግሞ ሶሥተኛ ሲሆን ኡዲኔዘም ላሢዮን በተመሳሳይ ውጤት በማሸነፍ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳትፎ በሚያበቃው አራተኛ ቦታ ተቆናጧል። በሌላ በኩል ብሬሺያ እንደ ባሪ ሁሉ ወደታች ሲከለስ የአንዴው ጠንካራ ክለብ ሣምፕዶሪያም ሶሥተኛው ተሰናባች እንዳይሆን በጣሙን እያሰጋው ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ለ 19ኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን እጅግ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው ያደረገው። በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድርም ለፍጻሜ የደረሰው ማኒዩ ትናንት በተለይ የቅርብ ተፎካካሪውን ቼልሢይን 2-1 አሸንፎ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድሥት ከፍ ማድረጉ ምናልባትም በሻምፒዮናው ላይ ወሣኝ ሣይሆን አልቀረም። የፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ሊያበቃ የቀሩት ሁለት ግጥሚያዎች ብቻ ሲሆኑ ማንቼስተር ዩናይትድ ከግቡ ለመድረስ አንዲት ነጥብ ትበቃዋለች። በሌላ በኩል ቼልሢይ በዚህ የውድድር ወቅት በአጀማመሩ የታየበት ድክመት ሲታሰብ ለነገሩ ከሁለተኛው ቦታ መድረሱም በጣም የሚያስደንቅ ነው። አርሰናል በአንጻሩ በስቶክ ሢቲይ 3-1 በመሽነፉ ከቼልሢይ በሶሥት ነጥቦች ዝቅ ብሏል። አራተኛው ማንቼስተር ሢቲይ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋም የማንቼስተር ዩናይትድ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የፍጻሜ ተጋጣሚ ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና ትናንት የከተማ ተፎካካሪውን ኤስፓኞልን 2-0 ሲረታ ውድድሩን በበላይነት ለመፈጸም ከተቀሩት ሶሥት ግጥሚያዎች አንዲት ነጥብ ማግኘት ይበቃዋል። ሁለቱን ጎሎች ኢኒየስታና ፒኬ ሲያስቆጥሩ ባርሣ አሁን የሚመራው በ 91 ነጥቦች ነው። ምናልባት በፊታችን ረቡዕ በሌቫንቴ ካልተሸነፈ ቀድሞ ለተከታታይ ሶሥተኛ ሻምፒዮናው ሊበቃ ይችላል። በሌላ በኩል ዋነኛ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ ምንም እንኳ ሤቪያን 6-2 ቢያሽንፍም ለሻምፒዮንነት ያለው ዕድል ይበልጥ እየመነመነ ነው የሄደው። በስምንት ነጥቦች ብልጫ ነው የሚመራው። ዘንድሮ ክለቡን የሚያጽናና ነገር ቢኖር ምናልባት ኮከቡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በጎል አግቢነት ተሽላሚ ሊሆን መቻሉ ነው። በነገራችን ላይ ሮናልዶ በሤቪያ ላይ ከተቆጠሩት የሬያል ስድሥት ግቦች አራቱን በማስመዝገብ ከባርሤሎና ተፎካካሪው ከሊዮኔል ሜሢ በሁለት ጎሎች ለመብለጥ በቅቷል። በጠቅላላው ያስቆጠረው 33 ጎሎች ነው።

Fußball Bundesliga Werder Bremen gegen Borussia Dortmund
ምስል dapd

የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር የዶርትሙንድ ሻምፒዮንነት አንድ ሣምንት ቀድሞ ሲረጋገጥ ሰንበቱን ደግሞ ትኩረቱ ይበልጥ ያየለው ወደታች ላለመከለስ በሚደረገው ፉክክር ላይ ነበር። በዚሁ ፉክክርም ባባየርን ሙንሺን የጎል መዓት 8-1 የተሸነፈው ሣንት ፓውሊ ዘንድሮ ከአንደኛው ቡንደስሊጋ በመውረድ የመጀመሪያው ሆኗል። ውጤቱ በተለይም ክለቡን ከ 18 ዓመታት በኋላ ለቆ ለሚሄደው ተወዳጅ አሠልጣኝ ለሆልገር ስታኒስላቭስኪ ጥሩ መሽኛ አልነበረም። ቢሆንም ተመልካቹ ከተሰናባቹ አሠልጣኝ በፍቅር ነው የተለያየው። በሌላ በኩል ባየርን ሙንሺን በታላቅ ድሉ ከሃምቡርግ ጋር 1-1 የተለያየውን ሁለተኛውን ሌቬርኩዝንን በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ሊቃረብ በቅቷል። ይህም ሁለቱ ክለቦች ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ቀጥተኛ ተሳትፎ ለሚያበቃው ሁለተኛ ቦታ እስከመጨረሻ ይታገላሉ ማለት ነው።

በሌላ በኩል ባለፈው ሣምንት ሻምፒዮንነቱን ቀድሞ ያረጋገጠው ዶርትሙንድ በፌስታ የተዳከመ ይመስላል። በዚህ ሰንበት የተለመደ ጥንካሬውን ማሣየቱ አልተሳካለትም። በብሬመን በለየለት ሁኔታ 2-0 ተሸንፎ ተመልሷል። እርግጥ ውጤቱ ለዶርትሙንድ የሚለውጠው ነገር አይኑር እንጂ ዘንድሮ ገደ ቢስ ሆኖ ለቆየው ለብሬመን አንድ ሣምንት ቀድሞ ወደታች ከመከለስ መዳኑን እንዲያረጋግጥ ወሣኝ አስተዋጽኦ ነው ያደረገው። ከሁለቱ ጎሎች አንዷን ያስቆጠረው ክላውዲዮ ፒሣሮ የጨዋታውን ሂደት እንዲህ ተመልክቶታል።

“ግጥሚያው ቀላል እንደማይሆን ከጨዋታው በፊት ተናግረን ነበር። የፈለጉትን ሁሉን ነገር ሊያከብሩ ይችላሉ። ግን ይህ ጥንካሬያቸውን ያጣሉ ማለት አይደለም። በበኩላችን እንደ ዕድል ሆኖ በከፍተኛ ትኩረት ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ድላችን ታዲያ ለዚያውም በገዛ ሜዳችን በመሆኑ እጅግ ጠቃሚ ነበር። ለደጋፊዎቻችንም በጣም አስደሳች ነው የሆነው”

እንግዲህ እንደ ብሬመን ሁሉ ኮሎኝ፣ ሽቱትጋርትና ካይዘርስላውተርንም በየግጥሚያቸው በማሸነፍ በአንደኛው ቡንደስሊጋ ውስጥ መቀጠላቸውን ከወዲሁ ሲያረጋግጡ የሌሎቹ የፍራንክፉርት፣ የቮልፍስቡርግና የግላድባህ ዕጣ የሚለይለት በፊታችን ሣምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ነው። ግላድባህን ካነሣን ቡድኑ ባለፉት ሣምንታት ባሳየው ትግልና አጨዋወት ለመትረፍ ዕድል ያለው ነው የሚመስለው። በሰንበቱ ግጥሚያው ፍራይቡርግን 2-0 ሲረታ አንዷን ጎል ያስቆጠረውም ማርኮ ሮይስ ነበር።

“ጨዋታው በጣም ከባድ እንደሚሆን ቀድመን የምናውቀው ነገር ነበር። ፍራይቡርግ ጨርሶ የማይመች ቡድን ነው። እና ጨዋታው ቀላል አልነበረም። ስለዚህም አንደኛውን ጎል ካስገባን በኋላ ፈታ ብለን ለመጫወት በመቻላችንና በማሸነፋችን በጣሙን ደስተኛ ነን”

ደስታው ዘላቂ ይሁን አይሁን ከፊታችን ሣምንት የመጨረሻ የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች በኋላ የሚታይ ይሆናል። በሌላ በኩል በፈረንሣይ ሻምፒዮና አራት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ሊል አመራሩን ከአንድ ወደ አራት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግ በቅቷል። ይህ ሊሆን የቻለው ሁለተኛው ማርሤይ በኦላምፒክ ሊዮን 3-2 በመሸነፉ ነው። በተቀረ በኔዘርላንድ ደግሞ ትዌንቴ ኤንሼዴ የዳች ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። ክለቡ ለዚህ ክብር የበቃው የፍጻሜ ተጋጣሚውን አያክስ አምስተርዳምን በተጨማሪ ሰዓት 3-2 ከረታ በኋላ ነው። ሁለቱ ክለቦች ሊጋውን አንደኛና ሁለተኛ ሆነው የሚመሩም ሲሆን በፊታችን ሰንበት እርስበርሳቸው መልሰው ይገናኛሉ። በነገራችን ላይ ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ኤንሼዴ ድሉን ለመድገም አንዲት ነጥብ ትበቃዋለች።

Marathonläufer beim Kölner Marathon
ምስል DW/N. Karbasova

አትሌቲክስ

የኬንያ አትሌቶች በመካከለኛና በረጅም ርቀት ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ የበላይነት ማሳየታቸው እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። ሁኔታው ባለፈው አርብ ዶሃ ላይ ተካሂዶ በነበረው የዲያመንድ ሊግ አትሌቲክስ ውድድርም የተለየ አልነበረም። የኬንያ አትሌቶች በወንዶች ስምንት መቶና 1,500 ሜትር ሩጫ ሲያሸንፉ በሴቶች ደግሞ በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ቀዳሚ ሆነዋል። ለኢትዮጵያ አስደሳቹ ውጤት የመኮንን ገብረ መድህን በ 1,500 ሜትር ሶሥተኛ መውጣትና በሶሥት ሺህ ሜትር ደግሞ የኔው አላምረው አሸናፊ መሆኑ ነበር። ታሪኩ በቀለም በዚሁ ርቀት ስምንተኛ ሆኗል። በሴቶች 1,500 ሜትር ቃልኪዳን ገዛኸኝ አምስተኛ ስትወጣ በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ሶፊያ አሰፋና ብርቱካን አለሙ አራተኛና አምሥተኛ ሆነዋል። በካታር የስፖርት ክለብ የተካሄደውን የዶሃውን የዲያመንድ ሊግ ውድድር አሥር ሺህ ተመልካቾች በቅርብ ሲከታተሉ በአጭር ርቀት አይለው የታዩት በተለይም የአሜሪካ አትሌቶች ነበሩ። በውድድሩ በርከት ያሉ የዓመቱ ታላላቅ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በሰንበቱ የማራቶን ሩጫ ንጽጽርም ኬንያ ከኢትዮጵያ የላቀችው ነበረች። በፕራግ ማራቶን በወንዶች ሶሥት ኬንያውናን ተከታትለው ቀደምቱ ሲሆኑ በሴቶችም አሸናፊ ሆነዋል። በሴቶች ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡት የሺመቤት ታደሰና በላይነሽ ዘመድኩን ነበሩ። በዚህ በጀርመን በሶሥት ከተሞች የማራቶን ሩጫዎች ሲካሄዱ ኢትዮጵያውያንም የተሳካ ተሳትፎ አድርገዋል። በማይንስ ከተማ 12ኛ የጉተንበርግ ማራቶን በወንዶች ባኔ ቶላ ሲያሸንፍ በሴቶችም ጂጂ ሮባ ቀዳሚ ሆናለች። በዱስልዶርፍ በወንዶች ኬንያዊው ናሃሾን ኪማዮ ሲያሸንፍ በሴቶች ድሉ የኢትዮጵያዊቱ አትሌት የመሪማ መሐመድ ነበር። በሃኖቨር ማራቶን ደግሞ በወንዶች የደቡብ አፍሪቃው ሉሳፎ አፕሪል፤ በሴቶች ደግሞ ኬንያዊቱ ጆርጂና ሮኖ አሸንፈዋል።

Formel 1 Sebastian Vettel Sieg 08.05.2011
ምስል AP

ቴኒስና የአውቶሞቢል እሽቅድድም

በቴኒሱ መድረክ ላይ የርቢያው ኮከብ የኖቫክ ጆኮቪች አልበገር ባይነት ባለበት ቀጥሏል። ጆኮቪች በማድሪድ-ኦፕን በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነውን ራፋኤል ናዳልን በገዛ አገሩ ሜዳ በለየለት ውጤት ሲረታ ከማይደፈር ዙፋኑ አውርዶታል ለማለት ይቻላል። ውጤቱ 7-5, 6-4 ነበር። ጆኮቪች በያዝነው 2011 ዓ.ም. አንዴም ያልተሸነፈ ሲሆን የትናንቱ የማድሪድ ድሉም በተከታታይ 32ኛው መሆኑ ነው። ኢስታምቡል ላይ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ደግሞ ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል አሸናፊ ሆኗል።

“ዛሬ ሁሉም ነገር ከኋላ እስከ ፊት በሚገባ የሰመረ ነበር። ግሩም አጀማመርም ነው ያደረግነው። እና ከዚህ የተሻለ አካሄድ ሊኖር አይችልም”
የ 23 ዓመቱ ወጣት ፌትል ዘዋሪ በዘንድሮው ውድድር ከአራት ሶሥቱን እሽቅድድም ማሸነፉ ሲሆን በጠቅላላው በ 93 ነጥቦች ይመራል። በ 59 ነጥቦች ሁለተኛው የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን ነው። የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን የጀርመኑ ሚሻኤል ሹማኸር በአንጻሩ በትናንቱ ውድድርም በ 12ኛ ቦታ ተወስኖ ቀርቷል።

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ