1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2003

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ኤ.ሢ.ሚላንና ባርሤሎና ከሰንበቱ ግጥሚያዎች ወዲህ ለሻምፒዮንነት በጣሙን ተቃርበዋል።

https://p.dw.com/p/RK5u
ምስል picture alliance/dpa

በአውሮፓ ክለቦች የሻምፒዮና ሊጋ ውድድርም ነገና ከነገ በስቲያ ሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንጀምርና የሻምፒዮናው ፉክክር በመጨረሻ በማንቼስተር ዩናይትድና በቼልሢይ መካከል የሚካሄድ ሆኗል። ማኒዩ ውድድሩ ሊጠቃለል አራት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በስድሥት ነጥቦች ብልጫ እየመራ ሲሆን ለሊጋው 19ኛ ሻምፒዮንነት የተቃረበ ነው የሚመስለው። ማንቼስተር ዩናይትድ በሰንበቱ ግጥሚያ ኤቨርተንን 1-0 ሲረታ አሁን በጥቅሉ 73 ነጥቦች አሉት። ብቸኛዋን ጎል በ 84ኛዋ ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ለቡድኑ አለኝታ የሆነውም ሃቪየር ሄርናንዴዝ ነበር።
አርሰናል በቦልተን ወንደረርስ 2-1 ሲሸነፍ ከሁለተኛው ወደ ሶሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። በአርሰናል መሸነፍ ተጠቃሚ የሆነው ደግሞ ቼልሢይ ነው። ቼልሢይ ዌስት-ሃም-ዩናይትድን 3-0 ሲረታ ከሊቨርፑል የሄደው የስፓኙ ኮከብ አጥቂ ፌርናንዶ ቶሬስም ለክለቡ የመጀመሪያ ጎሉን ለማስመዝገብ በቅቷል። ቼልሢይ ቶሬስን ለመግዛት 80 ሚሊዮን ዶላር ነው ያፈሰሰው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውስጥ በፊታችን ሰንበት ተመልካቾችን ትልቅ ግጥሚያ ይጠብቃቸዋል። ይህም በቀደምቱ በማንቼስተር ዩናይትድና በአርሰናል መካከል የሚካሄደው ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና ኦሣሱናን 2-0 በመርታት ሬያል ማድሪድን በስምንት ነጥቦች ርቀት አስከትሎ መምራቱን ቀጥሏል። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ዴቪድ ቪያና ሊዮኔል ሜሢ ነበሩ። ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ባርሣን በስፓኝ ኪንግስ-ካፕ ፍጻሜ ግጥሚያ 1-0 አሸንፎ ዋንጫዋን የወሰደው ሬያል ማድሪድ በሊጋ ውድድሩም ጠንካራ ጨዋታ በማሣየት ቫሌንሢያን 6-3 ረትቷል። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ጎንዛሎ፣ ሂጉዌንና ካካ ነበሩ።
ግጥሚያው ከነገ በስቲያ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ከባርሣ መልሶ ለሚገናኘው ለሬያል የማማቂያን ያህል ነበር ለማለት ይቻላል። በሌላ በኩል የባርሤሎናው ሜሢ ባለፈው ሰንበት 31ኛ የሊጋ ግቡን ሲያስቆጥር ክሪስቲያኖ ሮናልዶን በሁለት ጎሎች ብልጫ አስከትሎ እየመራ ነው። የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር ሊጠቃለል አምሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ባርሣ በ 88 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሬያል ማድሪድ ስምንት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። ሰንበቱን በሽንፈት ያሳለፉት ቫሌንሢያና ቪላርሬያል ደግሞ ሶሥተኛና አራተኛ ሆነው ይከተላሉ።

Flash-Galerie Bundesliga 31. Spieltag 2010/11 Mönchengladbach Dortmund
ምስል dapd

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ቀድሞ ሻምፒዮንነቱን ለማክበር የነበረው ውጥን ሳይሰምርለት ቀርቷል። ለዚሁ ምክንያቱም ሁለተኛው ሌቨርኩዝን አለመሸነፉና ዶርትሙንድም ባልተጠበቀ ሁኔታ በመጨረሻው በግላድባህ መረታቱ ነበር። የሊጋው ውድድር ሊጠቃለል ሶሥት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ የዶርትሙንድ የነጥብ ብልጫ አሁን መልሶ ከስምንት ወደ አምሥት ዝቅ ብሏል። ሁኔታው አደገኛ ሊሆን የሚችል ነው። ተከላካዩ ኔቨን ሱቦቲች በበኩሉ የቡድኑን ድክመት አምኖ ነው የተቀበለው።

“ዛሬ እርስበርሳችን አንዱ ሌላውን በማደናቀፍ ነበር የተጫወትነው። እና አልፎ አልፎ ታዲያ ግላድባህ መሃል ገብቶ ሁኔታውን መጠቀሙ አልቀረም። ጥሩ የማጥቃት ጨዋታ ነው ያሳዩት። ማሸነፋቸውም አግባብ የሌለው አልነበረም”
በዶርትሙንድ መሰናከል ሌቨርኩዝን ሻምፒዮን ለመሆን ያለውን ዕድል ይዞ ይቀጥላል ማለት ነው። ባየርን ሙንሺን በአንጻሩ ከፍራንክፉርት 1-1 በመለያየት ወደ አራተኛው ቦታ ሲንሸራተት ፍራይቡርግን 3-1 የረታው ሃኖቨር በቦታው ተተክቷል። ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ማጣሪያ ለመድረስ ለሚያበቃው ሶሥተኛ ቦታ ሁለቱ ክለቦች የሚያደርጉት ትግል እንግዲህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንድና ሁለት የለውም።
ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ላለመከለስ ከታች በሚደረገው ፉክክር ደግሞ በተለይም ብሬመን፣ ካይዘርስላውተንና ሽቱትጋርት ሣምንቱን ያደረጉት ዕርምጃ ምናልባትም ወሣኝነት የሚኖረው ነው። ብሬመን ሣንት ፓውሊን 3-1 ሲረታ ሽቱትጋርት ሃምቡርግን 3-0 እንዲሁም ካይዘርስላውተርን ሻልከን 1-0 ለማሽነፍ ችሏል። የሽቱትጋርቱ ጎል አግቢ ካካዉ የቡድኑን ድል እጅግ ጠቃሚ አድርጎ ነው የተመለከተው።

“እኛና መላው ሽቱትጋርትም ወደታች መውረድ አንፈልግም። እናም በአንደኛው ሊጋ ውስጥ ለመቆየት ጠቃሚ ዕርምጃ በማድረጋችን ደስታዬ ከመጠን ያለፈ ነው። ገና ሶሥት ግጥሚያዎች ይቀሩናል። እና የምንፈልገውም ሆፈንሃይምን አሸንፈን ሁሉንም ነገር በስኬት ለመፈጸም ነው”
በሊጋው ተዋረድ መጨረሻ ቮልፍስቡርግ፣ ግላድባሕና ሣንት ፓውሊ የመጨረሻዎቹ ሆነው ነው የሚገኝ የሚገኙት። ወደታች የማቆልቆሉን አደጋ ካነሣን ኮሎኝም እንዳይወርድ ያሰጋዋል። በጠቅላላው የጀርመኑ ቡንደስሊጋ ውድድር እስከመጨረሻው ሣምንት ትግል የተመላበት ሆኖ የሚቀጥል ነው የሚመስለው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ሢ.ሚላን ከሰባት ዓመታት ወዲህ እንደገና ሻምፒዮን ለመሆን ባለው ተሥፋ ባለፈው ሰንበትም ጠቃሚ ዕርምጃ አድርጓል። ቡድኑ ብሬሺያን 1-0 ሲያሸንፍ አራት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው በስምንት ነጥቦች እየመራ ነው። ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ኢንተር ሚላንም በበኩሉ ግጥሚያ ላሢዮን 2-1 በመርታት ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። ኢንተርን ለሁለተኝነቱ የጠቀመው በተለይም የናፖሊ በፓሌርሞ መሸነፍ ነው። በነገራችን ላይ ባሪ ደግሞ ከወዲሁ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ተከልሷል።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ለረጅም ጊዜ አመራሩን እንደያዘ የቆየው የሊል ትናንት 1-1 በሆነ ውጤት መወሰን በኦላምፒክ ማርሤይ እንዳይበለጥ የሚያሰጋው ሆኗል። ባለፈው ቅዳሜ የፈረንሣይን ሊጋ ዋንጫ ለማሸነፍ የበቃው ማርሤይ በወቅቱ አንድ ጨዋታ ጎሎት ከሊል የሚያንሰው በሁለት ነጥቦች ብቻ ነው። ቀሪ ግጥሚያውን ካሸነፈ አመራሩን ሊጨብጥ ይችላል። በኔዘርላንድ ሊጋም ሻምፒዮናው በሶሥት ክለቦች ፉክክር ጦፎ እንደቀጠለ ነው። ውድድሩ ሊጠቃለል ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በወቅቱ ትዌንቴ ኤንሼዴ በ 68 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን አያክስ አምስተርዳም አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በ 67 ሁለተኛ ነው፤ አይንድሆፈን ደግሞ በ 65 ይከተላል።

በዓለምአቀፉ የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ የሆነው የስፓኙ ራፋኤል ናዳል ትናንት በባርሤሎና-ኦፕን ፍጻሜ ግጥሚያ የአገሩን ልጅ ዴቪድ ፌሬርን 6-2, 6-4 በመርታት በሁለት ውድድሮች ከስድሥት ጊዜ በላይ በማሸነፍ ታሪክ ለማስመዝገብ በቅቷል። የ 34 ዓመቱ ኮከብ ከሣምንት በፊት በሞንቴካርሎ-ኦፕን ይህንኑ ተጋጣሚውን በማሸነፍ ለተከታታይ ሰባተኛ ድሉ መብቃቱ አይዘነጋም።

በሞሮኮ-ፌስ የዓለም ቴኒስ ማሕበር የሴቶች ፍጻሜ ደግሞ ኢጣሊያዊቱ አልቤርታ ብሪያንቲ የሩሜኒያ ተጋጣሚዋን ሢሞና ሃሌፕን በሁለት ምድብ ጨዋታ 6-4, 6-3 በማሸነፍ ለመጀመሪያ የውድድር ድሏ በቅታለች። በሣምንቱ ቴኒስ ከሁሉም በላይ ታዛቢዎችን ያስደነቀው እርግጥ በዚህ በጀርመን በሽቱትጋርት የፖርሼ ግራን ፕሪ ፍጻሜ የታየው ውጤት ነበር። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በ 32ኛ ቦታ የምትገኘው ጀርመናዊት ዩሊያ ጎርጌስ የዓለም አንደኛ የሆነችውን የዴንማርኳን ካሮሊን ቮዝኒያችኪን ግሩም በሆነ አጨዋወት ማሸነፏ ነው። በጥንድ ደግሞ ሣማንታ ስቶሱርና ሣቢነ ሊሢችኪ ባለድል ሆነዋል።

አሜሪካ ውስጥ በላውረንስ-ካንሣስ የአትሌቲክስ ውድድር ጃማይካዊቱ ኮከበ አትሌት ቬሮኒካ-ካምፕቤል-ብራውን በ 200 ሜትር አሸናፊ ሆናለች። ካምፕቤል በዚሁ ርቀት የአቴንና የቤይጂንግ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ መሆኗ የሚታወስ ነው። ጃማይካዊቱ አትሌት በመጪው የለንደን ኦሎምፒክ በመሳተፍ በሶሥት ተከታታይ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በሁለት መቶ ሜትር ሩጫ አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያዋ ሴት ለመሆንም ታልማለች። የወቅቱ የዳያመንድ ሊግ የአራት መቶ ሜትር መሰናክል ሻምፒዮን አሜሪካዊው ቤርሽዋን ጃክሰን ደግሞ በተለመደ ርቀቱ የበላይነቱን አስመስክሯል።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት የጀርመኑ ሻልከና ማንቼስተር ዩናይትድ የሚገናኙ ሲሆን በታዛቢዎች ግምት ወደ ፍጻሜ የማለፍ ትልቅ ዕድል የሚሰጠው የእንግሊዙ ክለብ ነው። ይሁንና በጀርመን ታሪክ ለሻምፒዮና ሊጋው ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው አራተኛ ክለብ ያለፉትን ዘጠኝ የአውሮፓ ግጥሚያዎቹን በማሸነፉ ጨርሶ የሚናቅ አይደለም። ቡድኑ ታላቅ ትግል እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ነው። ያም ሆነ ይህ ለማኒዩ ከፍጻሜ ከደረሰ በአራት ዓመታት ውስጥ ለሶሥተኛ ጊዜ ይሆናል።

በሻምፒዮናው ሊጋ ሁለተኛ ግጥሚያ በፊታችን ረቡዕ ምሽት እርስበርስ የሚገናኙት ሁለቱ የስፓኝ ቀደምት ክለቦች ባርሤሎናና ሬያል ማድሪድ ናቸው። ሬያል ባለፈው ረቡዕ በብሄራዊው ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ አሸናፊ ነበር። ድሉን በሣምንቱ በአውሮፓ ደረጃም ይደግመው ይሆን? ሁለቱም ቡድኖች በቴክኒክ የሰከኑና እጅግ ጠንካሮች በመሆናቸው እንዲህ ብሎ ከወዲሁ መተንበዩ በጣሙን ያዳግታል። የሚያሳዝነው ከሁለት አንዱ በግማሽ ፍጻሜው የሚሰናበት መሆኑ ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ