1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 10 2003

በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የዘንድሮው የለንደን ማራቶን ትናንት በኬንያ አትሌቶች ፍጹም የበላይነት ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/RIgR
ምስል AP

በእግር ኳሱ ዓለም የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድር ወደ ፍጻሜው መገስገሱን ሲቀጥል የኢትዮጵያ ሴት ብሄራዊ ቡድን ደግሞ ለለንደን ኦሎምፒክ በሚደረገው የአፍሪቃ ማጣሪያ ጋናን አልፎ ለግምሽ ፍጻሜ መድረሱ ታዛቢን እያስደነቀ ነው። ይህ ታላቅ ዕርምጃ ሲሆን በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ወንዶች የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ የኢፊይ ኦኑራ በስነ-ምግባር ጉድለት መሰናበትም ማነጋገሩ አልቀረም።

BdT Berlin Marathon
ምስል AP

የኬንያ ልዕልና በለንደን ማራቶን

የትናንቱ የለንደን ማራቶን አሸናፊዎች በወንዶችም ሆነ በሴቶች ኬንያውያን ሆነዋል። ኤማኑዌል ሙታይ ግሩም በሆነ የሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከአርባ ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡትም ኬንያውያኑ ማርቲን ሌልና ፓትሪክ ማካው ነበሩ። ሣምንቱን የሃይሌ ገብረ ስላሤን የዓለም ክብረ-ወሰን እሰብራለሁ ሲል ለጋዜጠኞች አስታውቆ የነበረው የኢትዮጵያ አትሌት ጸጋዬ ከበደ በበኩሉ በአምሥተኝነት ተወስኖ ቀርቷል።
በነገራችን ላይ የአሸናፊው የኤማኑዌል ሙታይ ጊዜ ከሃይሌ ገብረ ስላሤ ክብረ-ወሰን ለመድረስ 41 ሤኮንዶች የጎደለው ነበር። በሴቶችም ኬንያዊቱ ሜሪይ ካይታኒይ ግሩም በሆነ ጊዜ ለማሸነፍ በቅታለች። ካይታኒይ የመጀመሪያዋ በነበረው ባለፈው ዓመት የኒውዮርክ ማራቶን ሶሥተኛ መውጣቷ የሚታወስ ነው። ሩሢያዊቱ ሊሊያ ሾቡኮቫ ሁለተኛ ስትወጣ ኬንያዊቱ ኤድና ኪፕላጋትም ሶሥተኛ ሆናለች። አጸደ ባይሣ ከኢትዮጵያ አምሥተኛ!

በትናንትናው ዕለት ቤልግዴድ ላይ በተካሄደ የማራቶን ሩጫ በአንጻሩ ኢትዮጵያዊው አትሌት ገብረ ስላሤ ረዳ አሸናፊ በመሆን የኬንያውያን የአምሥት ዓመታት የበላይነት እንዲያበቃ አድርጓል። ኬንያዊው ማይክል ሩቶ ሁለተኛ ሲሆን ታደለ ሙሉጌታ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥቷል። በሴቶች ያሸነፈችው ኬንያዊቱ ፍራሺያህ ዋይታካ ነበረች። ሃይሌ ገብረ ስላሤም እንዲሁ በቪየና ግማሽ ማራቶን በማሸነፍ ወደ ዓለምአቀፉ የውድድር መድረክ በስኬት ተመልሷል።

Bundesliga 30. Spieltag Dortmund Freiburg
ምስል AP

የአውሮፓ የእግር ኳስ ሻምፒዮና

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር የስፓኙ ባርሤሎና ለሶሥተኛ ተከታታይ ሻምፒዮንነት እየተቃረበ ሲሄድ የኢጣሊያው ኤ.ሢ.ሚላንና የጀርመኑ ዶርትሙንድም ግባቸውን ለማሳካት ብዙም አልቀራቸውም። ባርሣ ከዋነኛ ተፎካካሪው ከሬያል ማድሪድ 1-1 ሲለያይ ኤ.ሢሚላን ሣምፕዶሪያን 3-0 በማሸነፍ ከሰባት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋንጫው ላይ እያለመ ነው። ዶርትሙንድም በተመሳሳይ ውጤት ፍራይቡርግን በማሸነፍ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ የድል ባለቤት ለመሆን ተቃርቧል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ማንቼስተር ዩናይትድ ቀደምቱ ቢሆንም ከፌደሬሺኑ ዋንጫ ከ FA Cup ፍጻሜ መድረሱ ግን የሚሣካለት አልሆነም። ሰንበቱን በተካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ዙር ግጥሚያ በማንቼስተር ሢቲይ 1-0 ተረትቶ ተሰናብቷል። ማንቼስተር ሢቲይ በዌምብሌይ ስታዲዮም ፍጻሜ የሚጋጠመው ቦልተን ወንደረርስን 5-0 ካሰናበተው ከስቶክ ሢቲይ ጋር ነው።

ወደ አፍሪቃ ሻገር እንበልና ለመጪው የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ ለማለፍ በሚካሄደው የሴቶች እግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ እያስመዘገበ ነው። ቀደም ሲል ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን አሰናብቶ የነበረው ቡድን ሰንበቱን እክራ ላይ በጋና 2-1 ቢሸነፍም በመጀመሪያ ግጥሚያው አዲስ አበባ ላይ 1-0 በመርታቱ በውጭ በተቆጠረች ጎል ብልጫ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፏል። የኢትዮጵያ ሴቶች በለንደን ማራቶን በመሳተፍ ወንዶቹ ያልተሳካላቸውን ዕውን ሊያደርጉ ይሆን? በዚህና በወንዶቹ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ በኢፊይ ኦኑራ ስንብት ላይ የፌደሬሺኑን የግንኙነት ሃላፊ አቶ መላኩ አየለን አነጋግረናል፤ ያድምጡ!

ለማጠቃለል ባለፈው ሌሊት ሻንግሃይ ላይ ተካሂዶ የነበረው የፍርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ የማልላረኑ ዘዋሪ የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን ሆኗል። በአንጻሩ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት እሽቅድድሞች አሸናፊ ለጀርመኑ ዜባስቲያን ፌትል በተከታታይ ለሶሥተኛ ድል መብቃቱ አልተሳካለትም። ሁለተኛ ነው የወጣው። ሆኖም በአጠቃላይ ነጥብ በአንደኝነት መምራቱን ይቀጥላል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ