1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 28 2003

የዘንድሮው የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ቀስ በቀስ ወደ መገባደጃው እየተቃረበ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ክለቦች ከማንቼስተር ዩናይትድ በስተቀር ሰንበቱን ያሳለፉት በድል ነበር።

https://p.dw.com/p/R6w5
ምስል picture-alliance/empics

በሻምፒዮናው ሊጋ ውድድርም ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚያልፉት ክለቦች በከፊልም ቢሆን ማንነት ነገና ከነገ በስቲያ በሚካሄዱ የመልስ ግጥሚያዎች ይለይለታል። በአትሌቲክሱ መድረክ ፓሪስ ላይ በተካሄደው የአውሮፓ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ሩሢያና ፈረንሣይ አይለው ሲታዩ ሰንበቱ የቴኒስ ዴቪስ-ካፕ ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር።

በእግር ኳስ እንጀምርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና ሬያል ሣራጎሣን በሜዳው በኖው-ካምፕ ስታዲዮም 1-0 በማሸነፍ በሰባት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። የቡድኑ ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ በ 43ኛዋ ደቂቃ ላይ ያቀበላትን ኳስ ለጎል ያበቃው ሰይዱ ኬይታ ነበር። የማሊው ተወላጅ በዚህ የውድድር ወቅት ለባርሤሎና ተሰልፎ ሲጫወት ገና ለአሥረኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ባርሣ ከ 27 ግጥሚያዎች በኋላ በወቅቱ በ 74 ነጥቦች ፕሪሜራ ዲቪዚዮኑን ይመራል።
የቅርብና ምናልባትም ብቸኛ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድም ምንም እንኳ ኮከቡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በአካል ጉዳት ባይሰለፍም ሣንታንዴርን 3-1 ሲረታ ሰባት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሁለቱን ካሪም ቤንዜማና የቀረችውን አንዷን ደግሞ ኤማኑዌል አዴባዮር ነበሩ። ከባርሤሎና በሃያ ነጥቦች ዝቅ ብሎ የሚገኘው ቫሌንሢያ ደግሞ ለሻምፒዮንነት ዕድል ባይኖረውም ማዮርካን 2-1 በማሸነፍ ሶሥተኝነቱን አጠናክሯል። ቪላርሬያል በአንጻሩ በአትሌቲኮ ማድሪድ 3-1 ሲሸነፍ አራተኛ ነው። በጎል አግቢነት የባርሣና የሬያል ከዋክብት ሜሢና ሮናልዶ እያንዳንዳችው 27 በማስቆጠር አቻ ለአቻ ሆነዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ በሊቨርፑል 3-1 ሲሸነፍ የሻምፒዮንነት ፉክክሩ እየጠነከረበት በመሄድ ላይ ነው። ለቀደምቱ ክለብ በሣምንቱ በቼልሢይ 2-1 ከተረታ ወዲህ ሁለተኛ ሽንፈቱ ሲሆን ባለፉት በአምሥት ግጥሚያዎችም ሶሥተኛው ይሆናል። በነገራችን ላይ ለሊቨርፑል ሶሥቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ሆላንዳዊው አጥቂ ዲርክ ኩይት ነበር። የማኒዩ አመራር በወቅቱ በሶሥት ነጥቦች ሲወሰን ይህም የሚሆነው ለዚያውም ሁለተኛው አርሰናል አንድ ጨዋታ ጎሎት ነው።
ማንቼስተር ሢቲይ በበኩሉ ዊጋን አትሌቲክን 1-0 ሲረታ ከአንደኛው ቦታ በሰባት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በሶሥተኝነት መከተሉን ቀጥሏል። አራተኛው ቼልሢይ ሁለት ጨዋታዎች የሚጎሉት ሲሆን አንዱን ግጥሚያ የሚያካሂደው ከብላክፑል ገና በዛሬው ምሽት ነው። በተቀረ ቶተንሃም ሆትስፐር አምሥተኛ ሲሆን ሊቨርፑልም በስድሥተኝነቱ ቀጥሏል። ዝነኛው ክለብ ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር መጥፎ አጀማመር ማድረጉ ሲታሰብ መልሶ ማገገም መቻሉ በጣሙን የሚያስደንቅ ነው።

Fußball Bundesliga 25. Spieltag SC Freiburg SV Werder Bremen Sonntag 06.03.2011
ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን የባየርን ሙንሺን ዕጣ ይብሱን ሲጨልም አሁንም መወደሱን የቀጠለው ሊጋውን በ 12 ነጥቦች የሚመራው ድንቅ ክለብ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ነው። ባየርን ሙንሺን በሶሥተኛው በሃኖቨር 3-1 ተቀጥቶ ወደ አምሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል የሆላንዳዊ አሠልጣኙ የሉዊስ-ፋን-ኸል የቆይታ ዕድሜ ረጅም መሆኑ አጠያያቂ ሆኗል። ባየርን ሙንሺን በሶሥት ግጥሚያዎች ለሶሥተኛ ጊዜ መሸነፉ ሲሆን ከቡንደስሊጋው ሻምፒዮናም ሆነ ከፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ቀድሞ መሰናበቱ ለክለቡ መሪዎች መሪር ነው የሆነው። ግን የክለቡ ማኔጀር ካርል-ሃይንስ-ሩመኒገ ፋን-ኸል ሚዩኒክ ውስጥ ይቆዩ አይቆዩ ከመናገር ለጊዜው መቆጠቡን ነው የመረጠው።

“ካለፈው ጊዜ የተማርኩት ነገር ቢኖር፤ ሁላችንም ለዚህ ሥራ አዲስ አይደለንም፤ ይህን ከመሰለ ግጥሚያ በኋላ ስሜታዊ በመሆን ውሣኔ ማድረጉ ትክክል እንዳልሆነ ነው። ለጊዜው ነገሩን ተወት ማድረጉ ይመረጣል”

ሌቨርኩዝን ቮልፍስቡርግን 3-0 በማሸነፍ ሁለተኝነቱን ሲያጠናክር ባየርንን በግሩም ጨዋታ የቀጣው ሃኖቨር ሶሥተኛ ነው። ማይንስም ሃምቡርግን 4-2 በማሸነፍ አራተኛ ሆኗል። ሆኖም በሰንበቱ ግጥሚያዎች የተመልካች ዓይን ይበልጥ ያተኮረው ባለፈው ሣምንት ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ወደሚያወርደው ወደ 17ኛው ቦታ አቆልቁሎ በነበረው ያለፉት በርካታ ዓመታት ቀደምት ክለብ በብሬመን ላይ ነበር። ታዲያ የደጋፊዎቹ ተሥፋ ከንቱ ሆኖ አልቀረም። ብሬመን ትናንት ፍራይቡርግን 3-1 ሲረታ ወደ 14ኛው ቦታ ከፍ ሊልና እንደገና የሚተነፍሰው አየር ሊያገኝ በቅቷል። ሆኖም ቡድኑ ካለፉት ሣምንታት አቀራረቡ ጠንከር ብሎ ቢታይም ገና መሻሻል የሚገባቸው ድክመቶች መኖራቸውን ነው አሠልጣኙ ቶማስ ሻፍ ያመለከተው።

“ሶሥቱንም ነጥቦች ለመሰብሰብ መቻላችን አስፈላጊ ነበር። ከሁሉም በላይ ጠቃሚው ነገር ይሄው ነው። በዛሬው ግጥሚያ መልሰን የወደፊት ዕርምጃ ማድረጋችንን ሁላችንም ያየን ይመስለኛል። ሆኖም ግን ሁሉም ነገር ጥሩ እንዳልነበረና መሻሻል እንዳለብንም ጭምር ነው የታዘብነው”

ብሬመን በፊታችን ሣምንት የሚጋጠመው ከመጨረሻው ከግላድባህ ጋር ሲሆን ያንን ጨዋታ ካሸነፈ በአንደኛው ቡንደስሊጋ ውስጥ የመቆየቱን ዕድል ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርግ አንድና ሁለት የለውም።

በኢጣሊያው አንደኛ ዲቪዚዮን ሤሪያ-አ የሰንበቱን ትኩረት ይበልጡን የሳበው የቀደምቱ የኤ.ሢ.ሚላንና የጁቬንቱስ ግጥሚያ ነበር። ሚላን በተራጋጭነቱ ለሣምንታት የጋዜጦችን ትኩረት ስቦ የቆየው የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ጄናሮ ጋቱሶ ባስቆጠራት አንዲት ግብ ለድል ሲበቃ የአምሥት ነጥብ አመራሩንም ሊያስከብርም ችሏል። በነገራችን ላይ ጋቱሶ በሤሪያ-አ ሻምፒዮና ጎል ሲያገባ ባለፉት ሶሥት የውድድር ወቅቶች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።
ኤ.ሢ.ሚላን ውድድሩ ሊያበቃ አሥር ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በ 61 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ያለፈው ጊዜ ሻምፒዮን ኢንተር ሚላንም ጌኖዋን 5-2 በመርታት ሁለተኝነቱን እንዳጠናከረ ነው። ሶሥተኛው ናፖሊ ከብሬሺያ ባዶ-ለባዶ ሲለያይ ከኢንተር በሶሥት ነጥቦች መራቁ ግድ ነው የሆነበት። በተቀረ ላሢዮ አራተኛ፣ ኡዲኔሰ አምሥተኛ፣ እንዲሁም ሮማ ስድሥተኛ በመሆን ይከተላሉ።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ሊል ኦላምፒክ ማርሤይን 2-1፤ እንዲሁም ስታድ ሬንስ ሞንትፔሊዬን 1-0 በማሸነፍ በእኩል 49 ነጥቦች መምራታቸውን ሲቀጥሉ ኦላምፒክ ሊዮንም አቪኞንን በመርታት ሶሥተኝነቱን ይዟል። እርግጥ ማርሤይም ከሊዮን እኩል ነጥብ ሲኖረው ነገር ግ’ን በጎል ልዩነት በመበለጥ አራተኛ ነው። ለማንኛውም በፈረንሣይ ሊጋ አንደኛው ከአምሥተኛው የሚለየው በአምሥት ነጥቦች ብቻ ሲሆን ሻምፒዮናው በመጪዎቹ ሣምንታትም ክፍት እንደሆነ ይቀጥላል።

በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን አይንድሆፈን በሶሥት ነጥቦች ብልጫ ኤንሼዴን አስከትሎ መምራቱን ሲቀጥል በፖርቱጋልም ፖርቶ በ 11 ነጥቦች ብልጫ በሻምፒዮንነቱ አቅጣጫ እንደገሰገሰ ነው። በሌላ በኩል በግሪክ ሻምፒዮናው ሳይቆይ ቀድሞ የሚለይለት ይመስላል። ለዚሁም ምክንያቱ ኦሎምፒያኮስ ፒሬውስ አመራሩን ወደ 13 ነጥቦች ከፍ ማድረጉ ነው። ፒሬውስ ከእንግዲህ ሻምፒዮን ለመሆን ሶሥት ነጥቦች ይበቁታል።

የእግር ኳሱ ትኩረት ነገና ከነገ በስቲያ ምሽት ደግሞ በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ላይ የሚያልም ይሆናል። በነገው ምሽት በተለይም በታላቅ ጉጉት የሚጠበቀው ግጥሚያ በባርሤሎናና በአርሰናል መካከል የሚካሄደው ነው። ለንደን ላይ የተካሄደው የመጀመሪያ ግጥሚያ በአርሰናል አሸናፊነት 2-1 ሲፈጸም ባርሣን በገዛ ስታዲዮሙ ከባድ ትግል ይጠብቀዋል። ሮማም እንዲሁ ቀደም ሲል በሜዳው በሻክታር ዶኔትስክ 3-2 በመሽነፉ ፈታኝ ግጥሚያ ነው ያለበት። ከነገ በስቲያ ረቡዕ ሻልከ ከቫሌንሢያ የሚገናኝ ሲሆን የምሽቱ ዋና ግጥሚያ ግን በቶተንሃም ሆትስፐርና በኤ.ሢ.ሚላን መካከል የሚካሄደው ነው። የእንግሊዙ ክለብ የመጀመሪያውን ግጥሚያ ለዚያውም በውጭ 1-0 ማሸነፉ አይዘነጋም።

Spanien Leichtathletik Europameisterschaft Russland
ምስል picture alliance/dpa

አትሌቲክስ

ሰንበቱን ፓሪስ ላይ በተካሄደው የአውሮፓ የአዳራሽ ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሩሢያና ፈረንሣይ ውድድሩን በበላይነት ፈጽመዋል። ሩሢያ በስድሥት ወርቅ ሶሥት ብርና ስድሥት ናስ በጠቅላላው በ 15 ሜዳሊያዎች አሸናፊ ስትሆን ፈረንሣይም በአምሥት ወርቅ አራት ብርና ሁለት ናስ በጥቅሉ በ 11 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ሆናለች። ጀርመን በሶሥት ወርቅ ሶሥተኛ ስትሆን እያንዳንዳቸው በሁለት ወርቅ ከአራት እስከ ሰባት የተከታተሉት ብሪታኒያ፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሬፑብሊክና ኢጣሊያ ናቸው።
በጃፓን-ኦትሱ 66ኛ የቢዋ ሃይቅ ማራቶን ሩጫ ደግሞ ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሣንግ ሲያሸንፍ ደሪባ መርጋ ሁለተኛ ወጥቷል። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው ጃፓናዊው ሂሮዩኪ ሆሪባታ ነበር።
ዘገባችንን በቴኒስ ለማጠቃለል ትናንት ሜክሢኮ-ሞንቴሬይ ላይ በተካሄደ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ውድድር የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ ሩሢያዊቱ አናስታዚያ ፓቭሉሼንኮቫ ሰርቢያዊቱን የለና ያንኮቪችን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 አሸንፋለች። ሰንበቱን በርካታ የዴቪስ-ካፕ ግጥሚያዎችም ሲካሄዱ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ዩ.ኤስ.አሜሪካ ከቺሌ 4-1፤ ፈረንሣይ ከአውስትሪያ 3-2፤ ጀርመን ከክሮኤሺያ 3-2፤ ሰርቢያ ከሕንድ 4-1፤ ስዊድን ከሩሢያ 3-2 ተለያይተዋል።
ትናንት በወጣው ዕጣ መሠረት በፊታችን ሐምሌ ወር ሩብ ፍጻሜ እርስበርሳቸው የሚጋጠሙት ስዊድን ከሰርቢያ፤ ካዛክስታን ከአርጄንቲና፤ ዩ.ኤስ.አሜሪካ ከስፓኝ፤ እንዲሁም ጀርመን ከፈረንሣይ ይሆናሉ። በተቀረ በዛሬው ዕለት ይፋ የሆነ የዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ በወንዶች ራፋኤል ናዳልና በሴቶችም ካሮሊን ቮዝኒያችኪ በአንደኝነት መቀጠላቸውን አመልክቷል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ