1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 21 2003

እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቴኒስ!

https://p.dw.com/p/R4zM
ዶርትሙንድ፤ የጀርመን ቡንደስሊጋ ውበት!ምስል dapd

የቶኪዮ ማራቶን ድል የኢትዮጵያ ሆነ

በትናንትናው ሰንበት ጃፓን ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የቶኪዮ ማራቶን ሩጫ የኢትዮጵያው አትሌት ሃይሉ መኮንን ግሩም ለሆነ ድል በቅቷል። የሰላሣ ዓመቱ አትሌት ኬንያዊ ተፎካካሪውን ፓውል ቢዎትን በ 35ኛው ኪሎሜትር ላይ ከኋላው አስቀርቶ ሲያመልጥ ያሸነፈው በሁለት ሰዓት ከሰባት ደቂቃ 35 ሤኮንድ ጊዜ ነው። ሃይሉ መኮንን ሩጫውን እንደፈጸመ ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሣ በውድድሩ ሳይሳተፍ ለቀረው ለሃይሌ ገ/ሥላሴ የተለየ አድናቆቱን ገልጿል።                    
የዓለም የማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤት የሆነው ሃይሌ በፊታችን ሚያዚያ ወር ቪየና ላይ በሚካሄደው ግማሽ ማራቶን ሩጫ መካፈሉም በወቅቱ እያጠራጠረ ነው። በውድድሩ በወንዶች ቢዎት ሁለተኛ ሲወጣ የአስተናጋጇ አገር ተወዳዳሪ ዩኪ ካዋኡቺ ደግሞ ስሥተኛ ሆኗል። የማነ ጸጋዬ ሰባተኛ! በሴቶች ሩሢያዊቱ ታቲያና አርያሶቫ ስታሸንፍ ጃፓናዊቱ ኖሪኮ ሂጉቺ ሁለተኛ እንዲሁም ሌላዋ ሩሢያዊት ታቲያና ፔትሮቫ ሶሥተኛ ወጥታለች።

በዚያው በጃፓን አንድ ቀን ቀደም ሲል ተካሂዶ በነበረ የፎኩኦካ አገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር ደግሞ በወንዶች ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል አይለው ታይተዋል። አሸናፊው ቤዳን ካሮኪ ሲሆን ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡት ደግሞ ኒኮላስ ማካኡና ዋጁኪ ያኮብ ነበሩ። በሴቶች የጃፓን አትሌቶች ከአንድ እስከ አምሥት ቀደምቱን ቦታ ለመያዝ ችለዋል።

ኒው ሜክሢኮ ላይ በተካሄደ የአዳራሽ ውስጥ አትሌኤቲክስ ውድድር የአሜሪካ አትሌቶች አይለው ሲታዩ በምርኩዝ ዝላይ የኦሎምፒክ ሁለተኛዋ ጄን ሱር በ 4,86 ሜትር ብሄራዊውን ክብረ-ወሰን ለማሻሻል በቅታለች። ሱር በምርኩዝ ዝላይ ከሩሢያዊቱ የዓለም ሻምፒዮን ከየለና ኢዚምባየባ ቀጥላ ሁለተኛዋ ጠንካራ አትሌት እንደሆነች ይታወቃል። ሌላዋ የአሜሪካ አትሌት ካማሬና ዊሊያምስም አሎሎዋን 19,87  ሜትር በመወርወር ተመልካቾችን አስደንቃለች። በተቀረ የሰንበቱ ተጨማሪ  ታላቅ ዜና ሩሢያዊቱ ቬራ ሶኮሎቫ በመሄድ ሃያ ኪሎሜትር ውድድር ሶቺ ላይ አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ማስመዝገቧ ነው። 
     
የአውሮፓ ቀደምት ክለቦች ውድድር

የሁለች ክለቦች የባላይነት ፉክክር በሰመረበት በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና አመራሩን ወደ ሳባት ነጥቦች ልዩነት እንዲያሰፋ ሣምንቱ መልካም አጋጣሚ ሆኗል። ባርሣ ማዮርካን 3-0 አሸንፎ ሲመለስ አመራሩን ሊያሰፋ የቻለው የቅርብ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ ከዴፖርቲቮ ኮሩኛ ጋር ባዶ-ለባዶ በመለያየቱ ነው። ባርሤሎና ከ 25  ግጥሚያዎች በኋላ 68 ነጥቦች ሲኖሩት ሬያል በ 61 ይከተላል፤ አሥር ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛው ቢልባዎን 2-1  ያሽነፈው ቫሌንሢያ ነው። በጎል አግቢነቱ ፉክክር የባርሣው ሊዮኔል ሜሢ 26 አስቆጥሮ ይመራል፤ ሁለተኛው 24  ያስገባው የሬያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የመጀመሪያው የዘንድሮው የውድድር ወቅት የሊጋ ዋንጫ ትናንት ባለቤት አግኝቷል። በርሚንግሃም ሢቲይ አርሰናልን ባልተጠበቀ ሁኔታ 2-1በማሸነፍ ዋንጫውን ሲወስድ ክለቡ ለዚህ የበቃው ከ 48 ዓመታት ቆይታ በኋላ መሆኑ ነው። በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ወደታች እንዳይወርድ ለሚያሰጋው ክለብ  ሁለተኛዋን የድል ጎል በ 89ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ኦባፌሚ ማርቲንስ ነበር። አርሰናል በዌምብሊይ ስታዲዮም ክስረት ሲደርስበት ማንቼስተር ዩናይትድ በአንጻሩ ዊጋን አትሌቲክን 4-0 በማሸነፍ የፕሬሚየር ሊግ አመራሩን ወደ አራት ነጥቦች ሊያሳድግ ችሏል።, ማኒዩ ከ 27 ግጥሚያች በኋላ 60 ነጥቦች ሲኖሩት አርሰናል በ 56 ሁለተኛ ነው፤ ማንቼስተር ሢቲይ ደግሞ ከአንድ ጨዋታ ብልጫ ጋር በ 50 ነጥቦች ይከተላል። ቶተንሃም ሆትስፐር አራተኛ ሲሆን ቼልሢይ አምሥተኛ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ የዘንድሮው አስደናቂ ክለብ ዶርትሙንድ ባየርንን ለዚያውም  ሙንሺን ላይ በገዛ ሜዳው አሸንፎ ከተመለሰ ካለፈው ቅዳሜ ወዲህ የሻምፒዮናው ነገር ከወዲሁ የለየለት ነው የሚመስለው። ዶርትሙንድ በቀለጠፈ አጨዋወት 3-1 ሲያሸንፍ አመራሩም ተከታዩ ሌቨርኩዝን እኩል ለእኩል በመውጣቱ ወደ 12 ነጥቦች ከፍ ብሏል። ወደ አራተኛው ቦታ ማቆልቆል ግድ ከሆነበት ከባየርን ሙንሺን ጋር የሚለዩት እንዲያውም 16 ነጥቦች ናቸው።

ሁለተኛው ሌቨርኩዝን በብሬመን ሜዳ ባደረገው ጨዋታ 2-0 ከመራ በኋላ በመጨረሻ 2-2  ተለያይቷል። ታዲያ ይህ እኩል ለእኩል ውጤት ለሻምፒዮንነት እፎካከራለሁ ለሚለው ለሌቨርኩዝንም ሆነ ወደታች እንዳይወርድ ብርቱ አደጋ ተደቅኖበት ለሚገኘው ለብሬመን የበጀ አልነበረም። የሌቨርኩዝኑ አጥቂ ሢሞን ሮልፈስ እንዲያውም ውጤቱን እንደ ሽንፈት ነው የቆጠረው። 

“ጨዋታውን በመቆጣጠር በአግባብ መምራታችን ሲታሰብ ውጤቱ የሽንፈትን ያህል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚያ ወዲያ ወደኋላ ማሸግሸጉን ነው የመረጥነው። አንድም ወደፊት በመሄድ ለማጥቃት የሞከረ አልነበረም። እናም በዚሁ የተነሣ ጎሎቹ ይገባሉ። በዕውነቱ ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ ከተቆጣጠርን በኋላ ለምን ይህ እንዲሆን እንደፈቀድን ሊገባኝ አይችልም”

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ደግሞ በአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ ያልቀናው ኢንተር ሚላን ትናንት ዌስሊይ ስናይደርና ሣሙዔል ኤቶ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሣምፕዶሪያን 2-0  በማሸነፍ ለጊዜው በአንድ ጨዋታ ብልጫም ቢሆን ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። አንደኛው ኤ.ሢ.ሚላን ዛሬ ማምሻውን ከሶሥተኛው ከናፖሊ የሚጋጠም ሲሆን ናፖሊ ከተሽነፈ ኢንተር ሁለተኛ እንደሆነ መቀጠሉ ነው። በተቀረ በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አይንድሆፈን፣ በፈረንሣይ ሊጋ ሊል፣ በስኮትላንድ ፕሬሚየር ሊግ ሤልቲክ ግላስጎውና በፖርቱጋል ሻምፒዮናም ፖርቶ በአመራራቸው ቀጥለዋል።

የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ

ያለፈው ሣምንት የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋና የአውሮፓ ሊጋ የአግር ኳስ ውድድሮችም የተካሄዱበት ነበር። በሻምፒዮናው ሊጋ ውድድር የጥሎ ማለፍ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያ ቼልሢይ ኮፐንሃገንን 2-0፤ ባየርን ሙንሺን ኢንተር ሚላንን 1-0  ሲያሸንፉ ኦላምፒክ ሊዮን ከሬያል ማድሪድ 1-1፤ እንዲሁም ማርሤይ ከማንቼስተር ዩናይትድ 0-0 ተለያይተዋል። ቀደም ባለው ሣምንት አርሰናል ባርሤሎናን 2-1፤ የኡክራኒያው ዶኔትስክ ሮማን 3-2፤ ቶተንሃም ኤ.ሢ.ሚላንን 1-0 ሲረታ ቫሌንሢያና ሻልከ ደግሞ 1-1 ተለያይተው ነበር።                                                                 
የመልሱ ግጥሚያዎች የነገ ሣምንት የሚካሄዱ ሲሆን በተለይ በሜዳቸው ሽንፈት የደረሰባቸው ሁለቱ የኢጣሊያ ቀደምት ክለቦች ኢንተርና ኤ.ሢ.ሚላን ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፉ ፈተና ሳይሆንባቸው አይቀርም። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ኢንተር ሚላን በዘጠናኛዋ ደቂቃ ላይ በባየርን ሙንሺን አጥቂ በማሪዮ ጎሜስ በተቆጠረች ጎል በሜዳው ሲሸነፍ ሚዩኒክ ውስጥ በሚካሄደው የመልስ ግጥሚያ ውጤቱን ለመቀየር የሰከነ ጨዋታ ማድረግ ይጠበቅበታል። ምናልባት ሊሆንለትም የሚችል ነው። እንደ ማሪዮ ጎሜስ ግምት ከሆነ ባየርንም ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፉ ገና እርግጠና ሊሆን አይችልም።

“የለም፤ ነገሩ አልቆለታል ብዬ አላምንም። የኢንተር ሚላን ቡድን ብዙ የጠራ ብቃት እንዳለው አይተናል። በግለሰቦች ደረጃ ጭምር! ምንም እንኳ ተጫዋቾቻቸው ወጣቶች ባይሆኑም ጠቃሚ የሆነ ልምድ አላቸው። እንዴት መጫወት እንዳለባቸው በሚገባ የሚያውቁ ሲሆን ለእኛም ዛሬ ቀላል ተጋጣሚ አልነበሩም። እርግጥ በረኛችን ቶማስ ክራፍት ግሩም በመሆኑና ሁላችንም ከኋላም ከፊትም በመታገላችን ነው በመጨረሻ በውጤቱ ልንካስ የበቃነው”

ሌላው ጥያቄ በመጀመሪያው ግጥሚያ ለንደን ላይ ተሸንፎ የተመለሰው ባርሤሎና ሣምንት በኖው-ካምፕ ስታዲዮሙ በሚያደርገው የመልስ ግጥሚያ አርሰናልን ለመርታት ምን መላ ይመታል ነው። የባርሣ የአዋወት ልዕልና እርግጥ ውድድሩን ለሚከታተል ለማንም የተሰወረ አይደለም። እናም በታላላቅ ከዋክብቱ በሊዮኔል ሜሢ፣ በሻቪና በኢኒዬስታ የሚመራው የስፓኝ ክለብ ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር ለማለፍ እንደሚበቃ የሚያምኑት ደጋፊዎቹ ብቻ ሣይሆኑ ብዙ የቅርብ ታዛቢዎች ጭምር ናቸው። ከዚሁ ሌላ የአውሮፓው የእግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ዩኤፋ የአውሮፓ ሊጋ ውድድርም ብዙ ትግል የታየበት ነበር።                                                                             
ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ሤቪያ ፖርቶ 1-0፤ ማንቼስተር ሢቲይ ሣሎኒኪ 3-0፤ ኤንሼዴ ሩቢን ካዛን 2-0፤ ቪላርሬያል ናፖሊ 2-1፤ ሌቨርኩዝን ቻርኮቭ 2-0፤ ዲናሞ ኪየቭ’ ኢስታምቡል 4-0፤ አምስተርዳም አንደርሌኽት 2-0፤ ሊቨርፑል ፕራግ 1-0፤ አይንድሆፈን ሊል 3-1 ተለያይተዋል። ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመዝለቅ የሚደረጉት ጨዋታዎች በፊታችን ወር መጀመሪያና በሣምንቱ የሚካሄዱ ሲሆን ጠንካራ ከሚሆኑት ግጥሚያዎች መካከል ሌቨርኩዝን ከቪላርሬያል፣ ዲናሞ ኪየቭ ከማንቼስተር ሢቲይ፤ ቤንፊካ ሊዝበን ከፓሪስ ሣን-ዠርማን፤ አያክስ አምስተርዳም ከስፓርታክ ሞስኮ ይገኙበታል።

በነገራችን ላይ የሕዝብ የለውጥ እንቅስቃሴ ዋነኛውን ትኩረት በሳበበት በሰሜን አፍሪቃና መካከለኛ ምሥራቅ አካባቢም ተወዳጁ እግር ኳስ ትናንት ወደ ግብጽ ተመልሷል። የግብጹ ዛማሌክ ተሸጋሽጎ በነበረ የአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያ የኬንያውን ኡሊንዚን 1-0 ሲረታ ተጫዋቾቹ በክንዳቸው ላይ ጥቁር ጨርቅ በማሰርና በሕሊና ጸሎት የትግሉን ሰለቦች አስበዋል። ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር በሰፈነበት በካይሮ የጦር ሃይል ስታዲዮም የተገኙት ተመልካቾች 22 ሺህ ይሆኑ ነበር። በሌላ በኩል የግብጽና የቱኒዚያ የሊጋ ውድድር ገና እንደተቋረጠ ሲሆን መጪው የአፍሪቃ ወጣቶች ሻምፒዮና ከሊቢያ ወደሌላ ቦታ በሚሸጋሸግበት ሁኔታ በቅርብ ውሣኔ እንደሚሰጥ የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በቴኒስ ለማጠቃለል ትናንት በፍሎሪዳ-ዴልሪይ ቢች በተካሄደ የኤ.ቲፒ. ፍጻሜ ግጥሚያ አርጄንቲናዊው ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮ ከ 2009 የዩ.ኤስኦፕን ድሉ በኋላ ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። ዴል-ፖትሮ ለዚህ ክብር የበቃው  የሰርቢያ ተጋጣሚውን ያንኮ ቲፕሣሬቪችን በሁለት ምድብ ጨዋታ 6-4, 6-4 በማሸነፍ ነው። በሜክሢኮ-አካፑልኮ ፍጻሜ ግጥሚያ የስፓኙ ዴቪድ ፌሬር የአገሩን ልጅ ኒኮላስ አልማግሮን 2-1 ሲረታ በሴቶች ደግሞ የአርጄንቲናዋ ጊዜላ ዱልኮ የስፓኝ ተጋጣሚዋን አራንጫ ፓራን አሸንፋለች።

መሥፍን መኮንን    ሂሩት መለሰ