1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2003

የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና በክረምቱ ወራት የተነሣ በከፊል አረፍ እንዳለ ቢሆንም ቀደምቱን የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግና የስፓኙን ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በመሳሰሉት ውስጥ ውድድሩ በአዲሱ ዓመት መግቢያ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/QmAc
ምስል AP

በዘመን መለወጫው በዓል ዋዜማ በያመቱ የተለመደው የሲልቬስትሬ የሩጫ ውድድር ዘንድሮም በየቦታው በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል። በዚህ በጀርመን በታሪካዊቱ ከተማ በትሪየር በተካሄደው ውድድር በወንዶች በስምንት ኪሎሜትር ሩጫ ኬንያዊው ሚካህ ኮጎ አሸናፊ በመሆን ባለፈው ዓመት ባለድል በሃይሌ ገ/ሥላሴ እግር ተተክቷል። በሴቶች ደግሞ ጀርመናዊቱ ዛቢነ ሞከንሃውፕት በአምሥት ሺህ ሜትር ለሶሥተኛ ጊዜ አሸናፊ በመሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቿን አስደስታለች።

ከዘመን መለወጫው የሩጫ ውድድሮች ሁሉ እርግጥ ታላቁ የሣኦ ፓውሎው ነበር። በዚሁ የ 15 ኪሎሜትር ሩጫ ውድድር የቀድሞው ብራዚላዊ የኒውዮርክ ማራቶን ባለድል ዶሽ ሣንቶሽ ከ 2003 እና 2005 ወዲህ ለሶሥተኛ ጊዜ አሸናፊ በመሆን የአገሪቱን ፌስታ ይበልጥ የደመቀ አድርጎታል። በሴቶች ደግሞ ኬንያዊቱ ቲሚሊ በአዲስ ክብረ-ወሰን ከ 2007 ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ አሽንፋለች።

በኢጣሊያ-ደቡብ ቲሮል በቦዘንም የበላይነቱን የያዙት የአፍሪቃ አትሌቶች ነበሩ። በወንዶች አሥር ሺህ ሜትር ሩጫ የዳያመንድ ሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያዊ ኢማኔ መርጋ ባለድል ሆኗል። በሴቶች አምሥት ሺህ ሜትር ደግሞ ኬንያዊቱ የዓለም ሻምፒዮን ቪቪየን ቼሩዮት ባለፈው ዓመት አሸናፊ የነበረችውን ኢትዮጵያዊት ጌዶ ሱሌን በማስከተል ሩጫዋን በአንደኝነት ፈጽማለች።
ከዚሁ ሌላ በስፓኝ ርዕሰ-ከተማ በማድሪድ የአሥር ኪሎሜትር ሩጫ ውድድር በወንዶች ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰና በሴቶችም የፖርቱጋሏ ተወላጅ ጄሢካ አውጉስቶ አሸንፈዎች ሆነዋል። በማድሪዱ የዘመን መለወጫ ሩጫ “ሣን ሲልቬስትሬ ቫሌካኖ” ላይ 35 ሺህ ሯጮች በመሳተፍ ትዕይንቱን በአውሮፓ ታላቁ አድርገውታል። የዘመን መለወጫው ሩጫ በርከት ባሉ ተጨማሪ የጀርመን ከተሞችም በዓሉን ካደመቁት ትዕይንቶች አንዱ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ቻይና-ሢያሜን ላይ ትናንት በተካሄደ የማራቶን ሩጫ ደግሞ ኬንያና ኢትዮጵያ እንደገና ልዕልና አሳይተዋል። በወንዶች ኬንያዊው ሮበርት ኪፕቹምባ ሲያሸንፍ የኢትዮጵያ ተፎካካሪዎቹ ሃይሉ ለማና አለማየሁ ሹምዬ ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በሴቶች ግን ድሉ የኢትዮጵያዊቱ የአማኔ ገመዳ ነበር።

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ላይ እናተኩርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ባርሤሎና ትናንት በከባድ የአየር ሁኔታ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን የወጣውን ሌቫንቴን 2-1 በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን አመራሩን ወደ አምሥት ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ለባርሣ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው የብሄራዊው ቡድን አጥቂ ፔድሮ ነበር። ከሁለት ሣምንት የክረምት ዕረፍት የተመለሰው ክለብ ለድል የበቃው ለዚያውም ካርልስ ፑጆልን፣ ዤራርዲ ፒኬንና ሊዮኔል ሜሢን የመሳሰሉትን ታዋቂ ተጫዋቾቹን ሳያሰልፍ ነው።

ወና ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ አንድ ጨዋታ ጎሎት በ 41 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን ዛሬ ማምሻውን ከጌታፌ ጋር ይጋጠማል። ሬያል ግጥሚያውን በድል ከተወጣ ከባርሤሎና ጋር ያለውን የነጥቦች ልዩነት መልሶ ወደ ሶሥት የማጥበብ ዕድል አለው። ቪላርሬያል አንድ ግጥሚያ ጎሎት በወቅቱ ሶሥተኛ ሲሆን ቫሌንሢያ ደግሞ ኤስፓኞልን 2-1 በመርታት በአራተኛው ቦታ ተቆናጧል። ለቡድኑ በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ የድል ጎሏን በአናቱ ያስቆጠረው ሁዋን ማታ ነበር።
በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን አምሥተኝነቱን የያዘው ኤፍ-ሢ-ሤቪያ ሲሆን በጎል አግቢነት ሁለቱ የባርሣና የሬያል ከዋክብት ሜሢና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እያንዳንዳቸው እኩል 17 ጎሎች አስቆጥረው ይመራሉ። በ 17 ግጥሚያዎች 17 ጎሎችን ማስቆጠር በተለይም ለመሃል ሜዳ ተጫዋች እጅጉን የሚደነቅ ነው። የስፓኝ ሻምፒዮና የሁለቱ ከዋክብት ፉክክር የሰመረበት ሆኖ እንደሚቀጥል አንድና ሁለት የለውም።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከሁሉም ይልቅ እስትንፋስ የሚያሳጣ ሆኖ ያለፈው ግጥሚያ ትናንት በቼልሢይና በኤስተን ቪላ መካከል የተካሄደው ነበር። ግጥሚያው በመጨረሻ 3-3 ሲያበቃ በተለይም በሜዳው በኦልድ-ትሬፎርድ ስታዲዮም ለተጫወተው ለቼልሢይ የቀና አልነበረም። የጨዋታውን ውጤት የወሰኑት በተለይም የመጨረሻዎቹ ስድሥት ደቂቃዎች ነበሩ። ኤስተን ቪላ እስከዚያው ድረስ 2-1 ሲመራ ከቆየ በኋላ ቼልሢይ በአጥቂው በዲዲየር ድሮግባ አማካይነት እኩል ለእኩል 2-2 ያደርጋል። ቼልሢይ በዚህ ብቻም አልተወሰነም። ጨዋታው ሊያበቃ አንዲት ደቂቃ ስትቀር እንዲያውም በተከላካዩ በጆን ቴሪይ አማካይነት 3-2 ይመራል። ሆኖም የቡድኑ ደጋፊዎች ደስታ ብዙ የሚቆይ አልሆነም። ቪላ በመጨረሻዋ ሤኮንድ ጎል አስቆጥሮ ግጥሚያው 3-3 ይፈጸማል።

ከሰንበቱ ግጥሚዮች ወዲህ ሊጋውን በ 41 ነጥቦች በአንደኝነት የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ ነው። ማንቼስተር ሢቲይ ደግሞ በሁለት ጨዋታ ብልጫ ለጊዜው በነጥብ እኩል ሆኖ ይከተለዋል። አርሰናል ሶሥተኛ ሲሆን ቶተንሃም ሆትስፐር አራተኛ፤ ቼልሢይ ደግሞ አምሥተኛ ነው። ቼልሢይ ባለፉት አሥር ግጥሚያዎች ሲሶውን ነጥቮች ብቻ ማግኘቱ ሲሆንለት ዘንድሮ ሻምፒዮን የመሆን ዕድሉ እየመነመነ የሚሄድ ነው የሚመስለው። በአንጻሩ የሻምፒዮናው አጀማመር ከባድ ሆኖበት የነበረው ሊቨርፑል ዎንደረርስን 2-1 በማሸነፍ ነፍስ እየዘራበት መሆኑን አስመስክሯል። በወቅቱ ዘጠነኛ ነው።
በጎል አግቢነት ቡልጋሪያዊው የማንቼስተር ዩናይትድ ኮከብ ዲሚታር ቤርባቶቭ 14 አስቆጥሮ ይመራል፤ በ 12 ጎሎች ሁለተኛው የማንቼስተር ሢቲው አርጄንቲናዊ ካርሎስ ቴቬዝ ነው። በስኮትላንድ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ በሰንበቱ ግጥሚያዎች ቀደምቱ የግላስጎው ክለቦች ሤልቲክና ሬንጀርስ 2-0 በሆነ ውጤት ሲለያዩ ሤልቲክ አመራሩን ወደ አራት ነጥቦች ሊያሰፋ ችሏል። ሬንጀርስ በ 41 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን ኸርትስ ደግሞ ሁለት ነጥቦች ወረድ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል።

በዚህ በጀርመን የቡንደስሊጋው ክለቦች ከገና እረፍት በኋላ በመሰባበብ ለተከታዩ ዙር መዘጋጀት እየጀመሩ ሲሆን አንዳንዶቹ በአዳዲስ ተጫዋቾች ራሳቸውን ለማጠናከር መሞከራቸው አልቀረም። ባየርን ሙንሺን የሆፈንሃይሙን ኮከብ ሉዊስ ጉስታቮን ሲገዛ አቆልቁለው የሚገኙት ኮሎኝና ግላድባህም በአዳዲስ ተጫዋቾች ራሳቸውን ለማጠናከር ዕርምጃ ወስደዋል። ወደ ሁፈንሃይም እንመለስና የብራዚላዊው መሃል ሜዳ ተጫዋች የሉዊስ ጉስታቮ ወደ ባየርን ሙንሺን መሄድ አሠልጣኙ ራልፍ ራንግኒክም በቅሬታ ስንብት እንዲያደርግ ምክንያት ነው የሆነው። የክለቡ አመራር አሠልጣኙን ሳያማክር ኮከብ ተጫዋቹን መሸጡ ለራንግኒክ የሚዋጥለት ነገር አልሆነም።

“እኔ በአንደኛና ሁለተኛ ሊጋ ውስጥ አሠልጣኝ በነበርኩባቸው ባለፉት ዓመታት ዕውነቱን ልናገር እንዲህ ዓይነት ነገር የደረሰበትን ጊዜ አላስታውስም። አንድ ተጫዋች፤ ለዚያውም ሉዊስ ጉስታቮን የመሰለ በማንም ይሁን ለሠልጣኙ ቀጥተኛ መረጃ ሳይሰጥ መሸጡን ማለቴ ነው። ለዚህ ውሣኔ ያበቃኝም ይሄው ነው”

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ውስጥ የመጀመሪያው ዙር ባልተጠበቀ ሁኔታ ሲያልፍ ቁንጮ ሆኖ የተገኘው ማንም ያላሰበው ሊል ነው። ሊል በማጥቃት አጨዋወቱ ብዙ ተወዳጅነትን ቢያተርፍም እርግጥ አሁን በሚቀጥለው በሁለተኛው ዙር ኦላምፒክ ሊዮንንና ማርሤይን የመሳሰሉት ቀደምት ክለቦች እየጠነከሩ መሄዳቸው የሚቀር አይመስልም። በነገራችን ላይ ሊል ለመጨረሻ ጊዜ የፈረንሣይ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ከ 55 ዓመታት በፊት ነበር። ለማንኛውም ሁሉንም በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ሂደት እንደርስበታለን።

የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተር በማሕበራቸው አመራር አካል ላይ ብዙ ትችት ከተሰነዘረ በኋላ አንድ ጸረ-ሙስና ኮሚቴ ለማቋቋም መነሣታቸውን ትናንት ስዊትዘርላንድ-በርን ላይ አስታውቀዋል። ሁለት ከፍተኛ የፊፋ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከፍተኛ ዓባላት ራይኖልድ ቴማኒና አሞስ አዳሙ ለ 2018 እና 2022 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት በሚደረገው ውድድር ድምጸውን በገንዘብ ለመሽጥ ሞክረዋል በመባል መታገዳቸው የሚታወስ ነው።

ብላተር ኮሚቴው ፊፋን ከሙስና እንደሚያጸዳ ተሥፋ ቢጥሉም ችግሩ እንደማይገፋ የሚያምኑት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። ለነገሩ ፊፋ ከወዲሁ የስነ ምግባር ኮሚቴ አቋቁሞ የሌሎች የአራት የታገዱ ባለሥልጣናትን ሁኔታ እንደሚከታተል ይታወቃል። ሆኖም በጉዳዩ የታየ ጭብጥ ውጤት ግን አለ ለማለት አይቻልም። ብላተር ምናልባት በፊታችን ሰኔ ወር እንደገና የፊፋ ፕሬዚደንት ሆኖ ለመመረጥ ባላቸው ውጥን ዕድላቸውን ለማጠናከር መላ መምታታቸው ይሆን? ይህ እርግጥ ለጊዜው እርግጠኛ ባይሆንም ጥርጣሬን መቀስቀሱ አልቀረም።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ