1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 25 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር እየተቃረበ በመሄድ ላይ ነው። በትክክል ሊከፈት የቀሩት 38 ቀናት ብቻ ናቸው።

https://p.dw.com/p/NDP2
የደርባን የዓለም ዋንጫ ስታዲዮምምስል DW/Arnulf Boettcher

የደቡብ አፍሪቃው’ የዓለም ዋንጫ

Südafrika Nationalmannschaft FiFA 2010 Weltmeisterschaft Südafrika
የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድንምስል AP

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ መካሄዱ የአገሪቱን ሕዝብ ብቻ ሣይሆን መላ ክፍለ-ዓለሚቱን የሚያኮራ ነው። ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ቀረብ ብሎ የሚካሄደው ፌስታ በተለይም የወጣቱን አፍሪቃዊ የእግር ኳስ ፍቅር ይበልጥ እንደሚያጠነክር አንድና ሁለት የለውም። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ከስድሥትና ሰባት ዓመታት በፊት አፍሪቃ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ መስተንግዶ መድረክ ትሆናለች ብሎ ያሰበ ቀርቶ ያለመም አልነበረም።
ለመሆኑ የአፍሪቃ ተሳታፊዎች በክፍለ-ዓለማቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ታላቅ ውድድር ምን ያህል የመግፋት ዕድል አላቸው፤ የአፍሪቃ እግር ኳስ በምን ይዞታና ደረጃ ላይስ ነው የሚገኘው? በነዚህና መሰል ጥያቄዎች ላይ ያነጋገርነው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋችና የወጣት ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ ስዩም አባተ የዛሬ እንግዳችን ነው።

የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድር

Bundesliga Spieltag 33 Bayern München Vfl Bochum Thomas Mueller
ባየርን ሙንሺንምስል AP

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ በአንዳንዶቹ ሻምፒዮናው ለይቶለታል፤ በሌሎችም ውሣኔው ብዙ አልቀረውም። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ውድድሩ ሊጠቃለል ገና አንድ ግጥሚያ ቢቀረውም ባለፈው ሰንበት ቦሑምን 3-1 በማሸነፍ በመሠረቱ ሻምፒዮንነቱን አረጋግጧል። ሶሥቱንም ጎሎች ያስቆጠረው አጥቂው ቶማስ ሙለር ነበር።
እኩል ነጥብ የነበረው የባየርን ተፎካካሪ ሻልከ በብሬመን 2-0 ሲረታ ከእንግዲህ ሻምፒዮን ለመሆን የሚችለው በቀጣዩ ግጥሚያው ቢያንስ 18-0 ካሽነፈ ነው። ለዚያውም ባየርን ሙንሺን ከተረታ! እንደ ዕውነቱ ከሆነ የቡንደስሊጋው ሻምፒዮንነት ጉዳይ ከወዲሁ አልቆለታል። ተጫዋቾቹም እንደ ዕለቱ ጎል አግቢ እንደ ቶማስ ሙለር ሁሉ ድላቸውን እያከበሩ ነው።

“ይህ እርግጥ እያንዳንዱ ተጫዋች የሚያልመው ነው። አንዴ ተሳክቶልን የጀርመን ሻምፒዮን ለመሆን ለዓመታት የምንጥረው ብዙዎች ነን። እና ለኔም ገና በመጀመሪያው የውድድር ወቅት መሳካቱ ግሩም ነገር ነው። ሕልሜ ዕውን ሆኖልኛል። በዚሁ ለመቀጠልም ነው የምፈልገው”

ባየርን ሙንሺን በእርግጥም በሚቀጥሉት ሣምንታት ከቡንደስሊጋው ሌላ የአውሮፓን ሻምፒዮና ሊጋና የጀርመንን ፌደሬሺን ዋንጫዎችም በማግኘት ድሉን ሶሥት ዕጅ ሊያደርግ ይችላል። ባየርን በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ኦላምፒክ ሊዮንን በደርሶ መልስ ግጥሚያ 1-0 እና 0-3 በጥቅሉ አራት-ለባዶ በማሽነፍ በተለየ ጥንካሬ ለፍጻሜ ሲያልፍ ከሁለት ሣምንት በኋላ ማድሪድ ላይ የፍጻሜ ተጋጣሚው የሚሆነው ባርሤሎናን ያሰናበረው ኢንተር ሚላን ነው።
ኢንተር በኢጣሊያ ሻምፒዮናም ሮማን በሁለት ነጥብ አስከትሎ መምራቱንም ቀጥሏል። የሚቀሩቱት ሁለት ግጥሚያዎች ብቻ ናቸው። ባርሣ ምንም እንኳ ከአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ቢሰናበትም በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውድድር ግን በአንዲት ነጥብ ብልጫ መምራቱን እንደቀጠለ ነው። የስፓኝ ሻምፒዮና ሶሥት ግጥሚያዎች የሚቀሩት ሲሆን የዋንጫው ጉዳይ የሚለይለት በባርሣና በሬያል ማድሪድ መካከል ይሆናል።
ዘንድሮ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ከስድሥት ዓመታት በኋላ በሩብ ፍጻሜ ዙር ተወስነው የቀሩት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ክለቦች ደግሞ በብሄራዊው ውድድር ሲያተኩሩ የቼልሢይና የማንቼስተር ዩናይትድ የዋንጫ ፉክክር የሚለይለት በፊታችን ዕሑድ ነው። ሰንበቱን ቼልሢይ ሊቨርፑልን 2-0 ሲረታ ማኒዩ ደግሞ ሰንደርላንድን 1-0 አሸንፏል። ቼልሢይ የሚመራውም በአንዲት ነጥብ ብቻ ነው። በኔዘርላንድ ትዌንቴ-ኤንሼዴ ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሪቱ ሻምፒዮን ሲሆን በፈረንሣይ ማርሤይ፤ እንዲሁም በፖርቱጋል ደግሞ ቤንፊካ-ሊዝበን ለድል ተቃርበዋል።

መሥፍን መኮንን/ሸዋዬ ለገሠ