1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 29 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት የቀረው ሶሥት ወር ገደማ ብቻ ነው።

https://p.dw.com/p/MN7p
የአርጄንቲናው ጎል አግቢ ሂጉዌይንምስል AP

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት የቀሩት በትክክል 94 ቀናት ብቻ ናቸው። እናም ጊዜው በተሳታፊዎቹ አገሮች ለውድድሩ የሚደረገው ዝግጅት የሚጠናከርበት ነው። ይህም በመሆኑ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ በዓለም ዙሪያ በርካታ የአቅም መለኪያ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። ከነዚህ ግጥሚያዎች ውጤት ተነስቶ በወቅቱ ደካማው ወይም ጠንካራው ይሄ ነው ብሎ ለመናገር ቢያዳግትም በተለይ ሃያል በሚባሉት አገሮች ንጽጽር አንዳንድ ግንዛቤ መገኘቱ አልቀረም።

ከግጥሚያዎቹ ሁሉ በተለይ ከበድ ያለ ትኩረት የተሰጣቸው በስፓኝና በፈረንሣይ፤ እንዲሁም በጀርመንና በአርጄንቲና መካከል የተካሄዱት ሲሆኑ የአውሮፓ ሻምፒዮን ስፓኝ ፓሪስ ላይ ፈረንሣይን በፍጹም የበላይነት 2-0 በማሸነፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥንካሬዋ እንደቀጠለች መሆኗን በሚገባ አስመስክራለች። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ዴቪድ ቪያና ሤርጆ ራሞስ ነበሩ። የፈረንሣይ ብሄራዊ ቡድን በአንጻሩ በዓለም ዋንጫው ማጣሪያና አሁንም በሣምንቱ ባሣየው ድክመት ከቀጠለ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ቢበዛ ከሩብ ፍጻሜ ባሻገር መዝለቁ በወቅቱ በጣሙን የሚያጠራጥር ነው።

በሌላ በኩል በደቡብ አሜሪካ ማጣሪያ እንደ ፈረንሣይ ሁሉ ብዙ ተንገዳግዶ ያለፈው የአርጄንቲና ብሄራዊ ቡድን በዚህ በሚዩኒክ በግሩም አጨዋወት ጀርመንን 1-0 በመርታት ወደ ቀድሞ ጥንካሬው ተመልሷል። የጀርመን ቡድን የተለመደ ትግሉ ሲጎለው አሠልጣኙ ዮአኺም ሉቭም የአርጄንቲናን ልዕልና አምኖ ከመቀበል ሌላ ምርጫ አላገኘም።

“ጠንካራ ከሆነ የአርጄንቲና ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው። እናም ብዙ ዕድል መስጠት አልነበረብንም። ጥሩ ያላደረግነው ነገር በተለይ መሃል ሜዳ ላይ ኳስ በምንይዝበት ጊዜ ወደ ጎን ወይም ወደ ኋላ በመቀባበል መወሰናችን ነው። ወደፊት ለማጥቃት በቂ ወኔ አልነበረንም። ስለዚህም ያገኘነው ዕድልም በጣም ጥቂት ነበር”

የሁለት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት የአርጄንቲና አሠልጣኝ ዲየጎ ማራዶና በበኩሉ “አለን፤ አሁንም ሕያው ነኝ” ሲል ነው እፎይታውን የገለጸው። ያለፉት 18 ወራት የአሰልጣኝነት ዘመኑ ለአንዴው ድንቅ የኳስ ጠቢብ ለማራዶና ውጣ ውረድ የሞላበት ሆኖ ነው ያለፈው። የአርጄንቲና ብሄራዊ ቡድን እንዳለፈው ረቡዕ ሰክኖ ከተጫወተ በዓለም ዋንጫው ፍጻሜ እስከመጨረሻው ሊዘልቅም ይችላል።

ከተቀሩት ቀደምት አገሮች እንግሊዝ የአፍሪቃን ዋንጫ ባለቤት ግብጽን በዌምብሌይ ስታዲዮም 3-1 ስታሸንፍ የአምሥት ጊዜዋ የዓለም ሻምፒዮን ብራዚልም አየርላንድን 2-0 ረትታለች። የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን በአንጻሩ ከካሜሩን ባዶ-ለባዶ በሆነ ውጤት ሲወሰን ከሁሉም በላይ አቅም ፍተሻው ያልሰመረላት አስተናጋጇ አገር ደቡብ አፍሪቃ ነበረች። ከናሚቢያ ጋር ባደረገችው ግጥሚያ 1-1 ነበር የተለያየችው። ደቡብ አፍሪቃ እንደ አስተናጋጅ አገር ቢቀር እስከ ሩብ ፍጻሜው ዙር እንኳ መዝለቅ እንድትችል ብዙ መጠናከር የሚኖርባት ነው የሚመስለው።

በተቀሩት የወዳጅነት ግጥሚያዎች፤ ፖርቱጋል ቻይናን 2-0፤ ኡሩጉዋይ ስዊትዘርላንድን 3-1፤ ቱርክ ሆንዱራስን 2-0፤ አውስትሪያ ዴንማርክን 2-1፤ ሰርቢያ አልጄሪያን 3-0፤ ኔዘርላንድ ዩ.ኤስ.አሜሪካን 2-1 ሲያሸንፉ፤ በተረፈ ስሎቬኒያ ካታር 4-1፤ ፖላንድ ቡልጋሪያ 2-0፤ ሁንጋሪያ ሩሢያ 1-1፤ ቦስና ጋና 2-1፤ ኖርዌይ ስሎቫኪያ 1-0፤ ቆጵሮስ አይስላንድ ባዶ-ለባዶ፤ ደቡብ ኮሪያ አይቮሪ ኮስት 2-0፤ ሤኔጋልና ግሪክም እንዲሁ 2-0 ተለያይተዋል።

አትሌቲክስ

BdT Berlin Marathon
ምስል AP

በትናንትናው ዕለት ጃፓን-ኦትሱ ላይ በተካሄደው የቢዋ-ሃይቅ ማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያዊው አትሌት የማነ ጸጋይ ጃፓናዊውን ቶሞዩኪ ሣቶን አስከትሎ ከግቡ በመድረስ አሸናፊ ሆኗል። 42ቱን ኪሎሜትር ለማቋረጥ የፈጀበት ጊዜ ሁለት ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ 34 ሤኮንድ! የኤርትራው ተወዳዳሪ አብርሃም ታደሰ ሶሥተኛ ሲወጣ ከአራት እስከ አሥር ተከታትለው ሩጫውን የፈጸሙት በሙሉ ጃፓናውያን ነበሩ።

በተቀረ ሃይሌ ገ/ሥላሴ በፊታችን ግንቦት ወር የማንቼስተር ታላቅ ሩጫ በአሥር ሺህ ሜትር ለሶሥተኛ ድል ለመብቃት እንደሚወዳደር ሲያረጋግጥ የዓለም ሻምፒዮኖቹ ቀነኒሣ በቀለና የለና ኢዚምባየቫ ደግሞ ከአሜሪካውያኑ ቀደምት አትሌቶች ከታይሰን ጌይና ከሣኒያ ሪቻርድስ በመቀላለል በመጪው ሰኔ ወር የኦሬጎን ውድድር እንደሚሳተፉ ተነግሯል።

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች/ሻምፒዮና ሊጋ

Bundesliga 1. FC Nürnberg - Bayer 04 Leverkusen
ቡንደስሊጋምስል AP

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሶሥቱም ቀደምት ክለቦች ኢንተር ሚላን፣ ኤ-ሢ,ሚላንና ሮማ የተመካከሩ ይመስል በየበኩላቸው ግጥሚያዎች ባደ-ለባዶ በሆነ ውጤት ሲወሰኑ በተለይ ኢንተር አመራሩን ከሶሥት ነጥቦች በላይ ለማስፋት የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ኢንተር ከሰንበቱ ግጥሚያ በኋላ 58 ነጥቦች ሲኖሩት ኤ.ሢ.ሚላን 55፤ እንዲሁም ሮማ 52 ይዘው በቅርብ ይከተሉታል። የኢጣሊያ ሊጋ ሻምፒዮና በነዚሁ ፉክክር የሚለይለት ነው የሚመስለው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ድንቁ ክለብ ባየር ሌቨርኩዝን በዚህ የውድድር ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በመሸነፍ ወደ ሶሥተኛው ቦታ መንሸራተቱ ግድ ሆኖበታል። ሌቨርኩዝን ለዚያውም በዝቅተኛው ቡድን በኑርንበርግ 3-2 ሲሸነፍ በትናንቱ ሰንበት ይህን ውጤት የጠበቀ አንድም ታዛቢ አልነበረም። በመሆኑም በሻምፒዮናው አቅጣጫ ቀጥተኛውን መንገድ የያዘ መስሎ የቆየው ክለብ መሰናከል በተለይም አሠልጣኙን ዩፕ ሃይንከስን ምንም እንኳ የኑርንበርግን ማሸነፍ ተገቢ ነበር ቢልም በጣሙን ሳይቆረቁረው አልቀረም።

“እርግጥ ለኛ ሽንፈቱ በጣም መሪር ነው። ይህ ሲበዛ ግልጽ ነው። በአንጻሩ ለኑርንበርግ ግን አድናቆቴን ልገልጽ እወዳለሁ። ቡድኑ ዛሬ በአጨዋወቱም ሆነ በትግሉ ግሩም ነበር። ስለዚህም ማሸነፉ የሚገባው ነው”

የሌቨርኩዝን የመጀመሪያ ሽንፈት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ለሆኑት ለባየርን ሙንሺንና ለሻልከ በጣሙን ነው የበጀው። ሌቨርኩዝንን ባለፈው ሣምንት በመደረብ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡንደስሊጋው ቁንጮ ለመሆን የበቃው ባየርን ሙንሺን ምንም እንኳ በራሱ ግጥሚያ ከኮሎኝ 1-1 በሆነ ውጤት ቢወሰንም በቀደምቱ ክለብ መሸነፍ የተነሣ አሁን በሁለት ነጥብ ልዩነት በአመራሩ ሊቀጥል በቅቷል። 53 ነጥቦች አሉት።
ከሁሉም በላይ አስደናቂ ዕርምጃ ያደረገው ደግሞ በባየርንና በሌቨርኩዝን ፉክክር በስተጀርባ እየመጠቀ አሁን በ 51 ነጥቦች ለሁለተኝነት የበቃው ሻልከ ነው። ሻልከ ፍራንክፉርትን አስደናቂ በሆነ አጨዋወት 4-1 ሲያሸንፍ ባለፉት ሣምንታት ያለማቋረጥ ያሳየው ጥንካሬ ለሻምፒዮንነት ብርቱ ተፎካካሪ ያደርገዋል። ሆኖም ባለፈው ዓመት ቮልፍስቡርግን ሻምፒዮን ያደረገው አሰልጣኙ ፌሊክስ ማጋት ከባድ ጨዋታዎች እንደሚጠብቁት በማመልከት ለጊዜው መለዘቡን ነው የመረጠው።

“አሁን የሚቀጥሉት ተጋጣሚዎቻችን ሽቱትጋርት፣ ሌቨርኩዝን፣ ሃምቡርግና ባየርን ናቸው። እነዚህ ደግሞ በዚህ የውድድር ወቅት ሊገጥሙን ከሚችሉት ቡድኖች ከባዶቹ ይሆናሉ። እና አሁን በውጭ ካሸነፍን በኋላ በሜዳችን በምናካሂደው በአንዱ ወይም በሌላው ግጥሚያ አቻ ለአቻ ብንወጣ እንኳ የምንቀበለው ውጤት ነው። እንግዲህ ከነዚህ ግጥሚያዎች በኋላ ነው በየት አቅጣጫ እንደምንራመድ ለመናገር የምንችለው”

ለማንኛውም በሶሥቱ ክለቦች መካከል ያለው ልዩነት የሶሥት ነጥቦች ብቻ ሲሆን ሁሉም ዕድላቸውን እንደጠበቁ ይቀጥላሉ። ሆኖም ግን ውድድሩን በቀደምትነት ለመፈጸም የየክለቦቹና የተጫዋቾቹ የመንፈስ ጥንካሬ በሚቀጥሉት ሣምንታት ውስጥ ሲበዛ ወሣኝ ነው የሚሆነው። በተረፈ ሃምቡርግ በርሊንን 1-0 አሸንፎ በ 43 ነጥቦች አራተኛ ሲሆን ግላድባህን 3-0 የረታው ዶርሙንድ ደግሞ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ አምሥተኛ ነው። ቬርደር ብሬመን በገዛ ሜዳው ከሽቱትጋርት 2-2 በመለያየቱ ለአውሮፓ ሊጋ የሚያበቃውን ቦታ ለመያዝ በሚያደርገው ትግል ጠቃሚ ሁለት ነጥቦችን አጥቷል። በ 39 ነጥቦች ስድሥተኛ ነው።

የስፓኝ ሻምፒዮና የሁለት ክለቦች ፉክክር የሰፈነበት እንደሆነ ሲቀጥል የባርሤሎና ከአልሜይራ እኩል-ለእኩል 2-2 መለያየት ሬያል ማድሪድ መልሶ አመራሩን እንዲይዝ አድርጓል። ሬያል መልሶ ቁንጮ የሆነው ጠንካራ ተጋጣሚውን ሤቪያን ሁለት ለባዶ ከተመራ በኋላ ግሩም በሆነ ጨዋታ በመጨረሻዋ ደቂቃ 3-2 በማሽነፍ ነው። ባርሣና ሬያል እኩል 62 ነጥቦች ሲኖሯቸው ሬያል በስድሥት ጎሎች ብልጫ ይመራል። ቫሌንሢያ አንድ ጨዋታ ጎሎት በ 46 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው፤ ሤቪያ ወደ አምሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል።

በእንግሊዝ ሻምፒዮና ማንቼስተር ዩናይትድ ፓውል ስኮልስ ባስቆጠራት መቶኛ የፕሬሚየር ሊግ ግቡ ወንደረርስን 1-0 በማሸነፍ በሁለት ነጥብ ልዩነት አመራሩን ይዟል። እርግጥ 61 ነጥቦች ያሉት ቼልሢይ ገና አንድ ጨዋታ የሚጎለው ሲሆን በሶሥተኝነት የሚከተለው እኩል ነጥብ ያለው አርሰናል ነው። እዚህም ሻምፒዮናው የሚለይለት በነዚሁ ሶሥት ክለቦች መካከል ሲሆን በተረፈ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ዢሮንዲን-ቦርዶው፤ በኔዘርላንድ ሻምፒዮና ትዌንቴ-እንሼዴ፤ እንዲሁም በፖርቱጋል ሊጋ ቤንፊካ-ሊዝበን ይመራሉ።

መጪው የሣምንቱ አጋማሽ ደግሞ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የ 16 ክለቦች ጥሎ ማለፍ ዙር አብዛኞቹ የመልስ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ነው። በነገው ምሽት አርሰናል ከፖርቶና፤ ፊዮሬንቲና ከባየርን ሙንሺን የሚጋጠሙ ሲሆን፤ በማግሥቱ ደግሞ ማንቼስተር ዩናይትድ ከኤ.ሢ.ሚላን፤ እንዲሁም ሬያል ማድሪድ ከኦላምፒክ ሊዮን ይገናኛሉ። የተቀሩት ግጥሚያዎች፤ ቼልሢይ ከኢንተር ሚላን፤ ሤቪያ ከሞስኮና ቦርዶው ከፒሬውስ የሚካሄዱት ደግሞ የነገ ሣምንት ነው።

ዘገባችንን በቴኒስ ለማጠቃለል በዓለም የዴቪስ-ካፕ ቡድን የመጀመሪያ ዙር በጥንካሬያቸው የሚታወቁት ስፓኝን፣ ሩሢያንና ሰርቢያን የመሳሰሉት አገሮች የየበኩላቸውን ግጥሚያዎች በማሸነፍ ከጨረሻዎቹ ስምንት አገሮች መካከል ሊሆኑ በቅተዋል። ስፓኝ ስዊትዘርላንድን 4-1 ስታሸንፍ፤ ፈረንሣይ ከጀርመን 4-1፤ ሩሢያ ከሕንድ 3-2፤ አርጄንቲና ከስዊድን 3-2፤ ክሮኤሺያ ከኤኩዋዶር 5-0፤ ቼክ ሬፑብሊክ ከቤልጂግ 4-1፤ እንዲሁም ቺሌ ከእሥራኤል 2-1 ተለያይተዋል።

MM/DW/AFP/RTR

ነጋሽ መሐመድ