1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 22 2002

ካናዳ-ቫንኩቨር ላይ ሲካሄድ የሰነበተው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታ በአስተናጋጇ አገር ቁንጮነትና በደመቀ ትርዒት ባለፈው ምሽት ተጠናቋል።

https://p.dw.com/p/MG8o
ምስል AP

የቫን’ኩቨር የክረምት ኦሎምፒክ

“ድንቅና የወዳጅነት መንፈስ የተመላበት ጨዋታ ነበር። ካናዳ፤ እናመሰግናለን” የዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ዣክ ሮግ!
ካናዳ-ቫንኩቨር ላይ የተካሄደው 21ኛው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታ ትናንት ከ 17 ቀናት ውድድር በኋላ አስደናቂ በሆነ ትርዒትና ፌስታ በደመቀ ሁኔታ ተፈጽሟል። ውድድሩ ምንም እንኳ የጆርጂያ ወጣት ተወዳዳሪ አሳዛኝና አስደንጋጭ ሞት ጋርዶት ቢከፈትም መጨረሻው በዕውነትም ያማረበት ነበር። በ 60 ሺህ ተመልካቾች ጢም ብሎ በተመላው በቢሢ-ፕሌስ ስታዲዮም የታየው የሙዚቃና የዳንኪራ ትርዒት ከካናዳ ባሻገር ዓለምን በሰፊው ሊማርክ በቅቷል። ትርዒቱን ካደመቁት ከዋክብት መካከል ታዋቂው ካናዳዊ የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኒል ያንግና አቭሪል ላቪንግ፤ እንዲሁም የሆሊውዱ የፊልም ተዋንያን ዊሊያም ሻትነርና ማይክል ፎክስ ይገኙበታል። ምጊያውን ትርዒት አንድ ቢሊዮን ገደማ የሚጠጋ ሕዝብ በዓለም ዙሪያ በቴሌቪዥን ሲከታተል ዕለቱ በተለይም ለአስተናጋጇ አገር ለካናዳ ታሪካዊ ነበር።

ካናዳ 14 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሽነፍ ውድድሩን በቀደምትነት ስታጠናቅቅ በክረምቱ ኦሎምፒክ ታሪክ ውስጥ አብዛኛውን ወርቅ በመውሰድም አዲስ ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ በቅታለች። የአስተናጋጇን አገር ሕዝብ ያስፈነደቀው ይህ ብቻም አልነበረም። ትናንት ከመዝጊያው ስነ-ስርዓት ቀደም ሲል ከአሜሪካ ጋር በተደረገው ልብ የሚሰውር የበሮዶ ሆኬይ ፍጻሜ ግጥሚያ የአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ለድል፤ እንዲያም ሲል ለወርቅ ሜዳሊያ መብቃቱም ታሪካዊ ክብደት ነው የተሰጠው። በዚሁ ነርቭ በሚጨርስ ግጥሚያ የአሜሪካ ቡድን 2-1 ከተመራ በኋላ ጨዋታው ሊያበቃ 24 ሤኮንዶች ሲቀሩት ውጤቱን 2-2 ሲያደርግ የካናዳው የመጨረሻ ቀን ፌስታ ሊደበዝዝ አስግቶት ነበር። ይሁንና ሢድኒይ ኮስቢይ ባስቆጠራት የመጨረሻ ግብ ካናዳ 3-2 ለማሽነፍ ችላለች። ድሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ካናዳውያንን ከመጠን በላይ ነው ያስፈነደቀው።

የዓለምዓቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ዣክ ሮግ የካናዳን ሕዝብ ለእንግዳ ተቀባይነቱና ድንቅ የኦሎምፒክ መንፈሱ ከልብ ነው ያመሰገኑት። ሮግ የጨዋታውን በይፋ ማብቃት የገለጹት በጆርጂያው ወጣት የቦብ ስፖርተኛ በናዳር ኩማሪታሽቪሊ ሞት ያደረባቸውን ሃዘን እንደገና በመግለጽም ነው። የ 21 ዓመቱ ወጣት የቦብ ስፖርተኛ በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ዕለት በልምምድ ላይ እንዳለ ተንሸራቶ ከተሸካሚ ብረት ጋር ከተላተመ በኋላ በደረሰበት ጉዳይ ሕይወቱን ማጣቱ አይዘነጋም። ዣክ ሮግ የናዳር ኩማሪታሽቪሊ ትውስት ለሁልጊዜ አብሮን ይኖራል ብለዋል።

በውድድሩ አጠቃላይ ውጤት ካናዳ በ 14 ወርቅ፣ ሰባት ብርና አራት የነሐስ ሜዳሊያዎች አንደኛ ስትሆን ጀርመን ሁለተኛ፤ ኖርዌይ ሶሥተኛ፤ አሜሪካ አራተኛ፤ እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ አምሥተኛ ሆናለች። ጀርመን አስተናጋጇን አገር ተከትላ ሁለተኛ መውጣቷ ለተወዳዳሪዎቿ ታላቅ ውዳሴን ነው ያተረፈው። የአገሪቱ የኦሎምፒያ ተልዕኮ መሪ በርናርድ ሽቫንክ በውድድሩ ፍጻሜ በቦታው ከነበረው ጠንካራ ፉክክር አንጻር ተወዳዳሪዎቹ ያስመዘገቡትን ውጤት ድንቅ ነው ብለውታል።

“በኛ አመለካከት ቡድናችን ግሩም የውድድር ጥንካሬ ነው ያሳየው። ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ጽናት ሲያሳይ በየቀኑ ቢያንስ አንድ ሜዳሊያ እያገኘ ነው እስከዛሬ የደረሰው። እና አድናቆቴ ታላቅ ነው። ለዚሁ ባርኔጣዬን አወልቃለሁ” ብለዋል።

የጀርመን ቡድን 10 ወርቅ፣ 13 ብርና ሰባት የነሐስ ሜዳሊያዎች ሲያገኝ በተለይም ሴት ተወዳዳሪዎቹ ከጠቅላላው ሰላሣ ሜዳሊያዎች 19ኙን በመውሰድ ከወንዶቹ አይለው ታይተዋል። ከሁሉም ድንቋ ጀርመናዊት በመጀመሪያ የኦሎምፒክ ተሳትፎዋ ሁለት የወርቅና አንድ የብር ሜዳሊያ ያገኘችው የቢያትሎን ተወዳዳሪ የ 23 ዓመቷ ወጣት ማግዳሌና ኖይነር ነበረች።
የቫንኩቨር ኦሎምፒክ ጨዋታ መዝጊያ ስነ-ስርዓት የተጠቃለለው ሁሌም እንደተለመደው የኦሎምፒኩ ሰንደቅ ዓላማ ለመጪው አዘጋጅ ከተረከበ በኋላ ነበር። ውድድሩን ከአራት ዓመታት በኋላ የምታስተናግደው የሩሢያ ከተማ የሶቺ ከንቲባ አናቶሊይ ፓኮኖቭ ሰንደቅ ዓላማውን በደመቀ ሁኔታ ተቀብለዋል። በጥቅሉ የቫንኩቨሩ የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታ በጆርጂያው ወጣት ስፖርተኛ ሞት ያሳዝን እንጂ በርከት ላሉ ተወዳዳሪዎች ሕልማችውን ዕውን ሊያደርጉ የቻሉበት ሆኖ ነው ያለፈው።

እግር ኳስ፤ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች

Fußball Bundesliga Bayern München Hamburger SV
የባየርን ፍራንክ ሪቤሪይምስል AP

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቀደምቱ ክለብ ቼልሢይ በሜዳው 36 ጊዜ ሳይደፈር ከቆየ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ በማንቼስተር ሢቲይ ተገትቷል። ቼልሢይ 4-2 በሆነ ውጤት ሲሽነፍ ግጥሚያውን የፈጸመው ሁለት ተጫዋቾቹ ከሜዳ ወጥተውበት ነው። የቼልሢይ መንገዳገድ ማንቼስተር ዩናይትድ አመራሩን በአንዲት ነጥብ ልዩነት እንዲቃረብ ሲያደርግ ስቶክ-ሢቲይን 3-1 ለረታው ለሶሥተኛው ለአርሰናልም በጅቷል። አርሰናል አሁን ከቼልሢይ የሚለየው በሶሥት ነጥቦች ብቻ ነው። በጎል አግቢነት የማንቼስተር ዩናይትድ ዌይን ሩኒይ 23 አስቆጥሮ በበላይነት የሚመራ ሲሆን የፕሬሚየር ሊጉ ሻምፒዮና በሚቀጥሉት ሣምንታት የጦፈ ፉክክር የሚታይበት ነው የሚመስለው። ማንቼስተር ዩናይትድን ካነሣን ቀደምቱ ክለብ ትናንት በሊጋው ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ኤስተን-ቪላን 2-1 በማሸነፍ ለያዝነው የውድድር ወቅት የመጀመሪያ ድል በቅቷል። የድሉ ዋስትና አጥቂው ዌይን ሩኒይ ነበር።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ኡዲኔሰን 3-2 ሲያሸንፍ በአራት ነጥቦች ልዩነት ኤሢ.ሚላንን አስከትሎ መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ኤ.ሢ.ሚላን አታላንታ-በርጋሞን 3-1 ሲረታ ሶሥተኛው ሮማ በአንጻሩ ከናፖሊ 2-2 በመለያየት በሻምፒዮናው ፉክክር ሁለት ጠቃሚ ነጥቦችን አጥቷል። በስፓኝ ላ-ሊጋ ሁለቱም ቀደምት ክለቦች ባርሤሎናና ሬያል ማድሪድ የየበኩላቸውን ተጋጣሚዎች ሲያሽንፉ ባርሣ በሁለት ነጥቦች ልዩነት ቀደምት እንደሆነ ቀጥሏል። ባርሤሎና ማላጋን 2-1 ሲረታ በ 84ኛዋ ደቂቃ ላይ ለቡድኑ ወሣኟን የድል ጎል ያስቆጠረው አርጄንቲናዊ ኮከቡ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። በነገራችን ላይ ሊዮኔል ሜሢ በጎል አግቢነትም 17 በማስቆጠር የሊጋው ቁንጮ ነው። ሬያል ማድሪድ ደግሞ ቴነሪፋን 5-1 ሲያሸንፍ እዚህም ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ድንቅ ሆኖ የታየው የአርጄንቲናው ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ጎንዛሎ ሂጉዌይን ነበር።

የሶሥት ክለቦች ጠባብ ፉክክር ሰፍኖ በቀጠለበት በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር በዚህ ሰንበት የአመራር ለውጥ ተደርጓል። ለዚሁም ምክንያት የሆነው ሊጋውን ለረጅም ጊዜ ሲመራ የቆየው ሌቨርኩዝን ከኮሎኝ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ባዶ-ለባዶ በሆነ ውጤት መወሰኑ ነው። ሌቨርኩዝን በዚሁ ጠቃሚ ነጥቦችን ሲያጣ የቅርብ ተፎካካሪው ባየርን ሙንሺን ዕድሜ ለፈረንሣዊ ድንቅ ተጫዋቹ ለፍራንክ ሪቤሪይ ሃምቡርግን 1-0 በመሸኘት በዘንድሮው ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ አመራሩን ለመያዝ ችሏል። ባየርን በሁለት ነጥብ ብልጫ የሚመራ ሲሆን ሻልከ አራት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ነው። በውድድሩ ሂደት እስካሁን ድንቅ ጨዋታ ሲያሳይ የቆየው ሌቨርኩዝን የማታ ማታ ከመቼውም ጊዜ የቀረበ መስሎ የታየውን የዘንድሮ ድሉን እንዳያጣ በጣሙን ያሰጋዋል። ሆኖም የቡድኑ አሰልጣኝ ዩፕ ሃይንከስ ሽንፈቱን ብዙም ክብደት አልሰጠውም።

“ያሳዝናል ፍሬ ለማግኘት አለመቻላችን። ምክንያቱም በሁለተኛው አጋማሽ ከሞላ-ጎደል በአብዛኛው እኛ ነበርን ያጠቃነው። ግን እንዲህ ዓይነት ቀኖች ያጋጥማሉ። እናም’በቡድኔ ላይ ወቀሳ ለመሰንዘር አልፈልግም። ጥሩ አልተጫወትንም፤ ቢሆንም ሞክረናል”

ሌቨርኩዝን በፊታችን ሣምንት መልሶ እንደሚጠናከርና የሊጋው ሻምፒዮና ማራኪ ሆኖ እንደሚቀጥል ተሥፋ እናደርጋለን። በተረፈ የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሶሥት ወር ገደማ ያህል ቀርቶት ሳለ አንዳንዶቹ ታሳታፊ አገሮች ሣምንቱን የአቅም መፈተሻ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ይካሂዳሉ። ከነዚሁ አንዱም ሚዩኒክ ውስጥ ከነገ በስቲያ በጀርመንና በአርጄንቲና መካከል የሚካሄደው ነው። ከዚሁ ሌላ እንግሊዝ ከአፍሪቃ ሻምፒዮኗ ግብጽ፣ ናይጄሪያ ከዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ፣ ፈረንሣይ ከስፓኝ፤ እንዲሁም ነገ ብራዚል ከአየርላንድ ይጋጠማሉ።

አትሌቲክስ/ቴኒስ

በቼሌ የመሬት ነውጽ ሳቢያ የትሱናሚ ማስጠንቀቂያ ተላልፎ በነበረባት በጃፓን ዝናብ እየወረደ በተካሄደው የቶኮዮ ማራቶን ሩጫ የአገሪቱ ተወላጅ ማሣካዙ ፉጂዋራ አሸናፊ ሆኗል። ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡትም ጃፓናውያን ናቸው። ያለፈው ዓመት አሸናፊ ኬንያዊ ሣሊም ኪፕሣንግ በበኩሉ በቅዝቃዜ የተነሣ ሩጫውን ማቋረጡን መርጧል። 35 ሺህ ሰዎች በተሳተፉበት የከተማ ማራቶን በሴቶፕ ደግሞ ሩሢያዊቱ አሌቭቲና ቢክቲሚሮቫ አንደኛ ወጥታለች። ማራቶን ከተነሣ የሣምንቱ አስቂኝ ወይም አስገራሚ ነገር የማልታ ማራቶን ስርዓት ያጣ ሆኖ ማለፍ ነው። ሯጮቹን ከፊት ሆኖ የሚመራው አውቶሞቢል አቅጣጫውን በመሳቱ የተነሣ ፊት የነበሩት ሁለት አትሌቶች ውድድሩን እንዲያቋርጡ ሲያደርግ እነዚሁ ውጤቱ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል። በዚሁ በውል ባልለየለት ሩጫ የሞሮኮው ተወላጅ አብደል-ሃኪሚ-ኤል-ፌሂ አሽናፊ ሲባል ለተፈጸመው ስህተት ከአዘጋጆቹ በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።

በቴኒስ ለማጠቃለል በዱባይ-ኦፕን ፍጻሜ የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች የሩሢያ ተጋጣሚውን ሚካኢል ዩዥኒን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 ለማሸነፍ በቅቷል። በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ሁለተኛው የሆነው ጆኮቪች ባለፈው ዓመትም የዱባይ አሸናፊ እንደነበር አይዘነጋም። የሩሢያ ሴቶች ለፍጻሜ በደረሱበት በማሌዚያ-ኦፕን ደግሞ አሊሣ ክሌይባኖቫ ኤሌና ዴሜንቴቫን በሁለት ምድብ ጨዋታ በማሸነፍ ለመጀመሪያ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ድሏ በቅታለች።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ