1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 28 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከመንፈቅ በኋላ ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የስምንቱ ምድቦች ዕጣ ባለፈው አርብ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት መውጣቱ ይታወቃል። ታዲያ እንደተለመደው ከባድም ሆነ ቀለል ያለ ዕድል በገጠማቸው ተሳታፊ አገሮች ዕጣው ትልቁ መወያያ ርዕስ ሆኖ ነው ሰንበቱን ያሳለፈው።

https://p.dw.com/p/Ks2n

የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ዕጣ

ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ኬፕ-ታውን ላይ የተካሄደው ባሕላዊ ትርዒት ያጀበው የደመቀ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት የአፍሪቃን በጎ ገጽታ ለዓለም ለመሣየት ምናልባትም ከስንት አንዴ የተገኘው ዕድል ነበር። ደቡብ አፍሪቃ በክፍለ-ዓለሚቱ የመጀመሪያው የሚሆነውን አኩሪና ታሪካዊ የሆነ ውድድር ለማስተናገድ ብቁ መሆኗን በዝግጅቱ አስመስክራለች። እንደ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ከሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪቃ የምትጓዘው ዋንጫም ክፍለ-ዓለሚቱን ለቃ አትወጣም። ከስድሥቱ የአፍሪቃ ታሳታፊ አገሮች አንዱ ባለቤቷ ነው። ቢሳካ ከታሪክም ታሪክ በሆነ! እርግጥ የአፍሪቃ እግር ኳስ ዛሬ ከደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ አንጻር የዙማ ምኞትም ሆነ ትንበያ ብዙም የተጋነነ አይሆንም።

Flash - Galerie Südafrika Nationalmannschaft FiFA 2010 Weltmeisterschaft Südafrika
ምስል AP

ወደ ምድቦቹ ይዞታ እንሻገርና በምድብ-አንድ ውድድሩን ጆሃንስበርግ ላይ ከሜክሲኮ ጋር የምትከፍተው አስተናጋጇ አገር ደቡብ አፍሪቃ ቀላል ዕጣ አልገጠማትም። ፈረንሣይና ኡሩጉዋይ የተቀሩት ተጋጣሚዎቿ ሲሆኑ ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፉ ከባድ ፈተና የሚሆንባት ነው የሚመስለው። በሌላ በኩል በአገሩ ሕዝብ ፊት የሚጫወተው ብሄራዊ ቡድን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየጠነከረ የምድብ ግጥሚያዎቹን በስኬት ሊወጣም ይችላል። የአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን የመሃል ሜዳ ተጫዋች ስቲቨን ፒናር ከዕጣው በኋላ እንደተናገረው የተመልካቹ ድጋፍ ራሱ አውር-በመቶ ተጨማሪ ሃያል ሊሆን የሚችል ነው። በአጠቃላይ አስተናጋጇ አገር በውድድሩ ሂደት መክረሟ በተለይም ለድምቀቱ በጣሙን ለማስፈለጉ አንድና ሁለት የለውም።

ምድብ-ሁለት አርጄንቲናን፣ ደቡብ ኮሪያን፣ ናይጄሪያንና ግሪክን የሚጠቀልል ሲሆን አርጄንቲና ምንም እንኳ የደቡብ አሜሪካን ማጣሪያ ተንገዳግዳ ብታልፍም የጎላ ዕድል ያላት ነው የሚመስለው። ናይጄሪያና ደቡብ ኮሪያም እንዲሁ ቀላል ተጋጣሚዎች አይሆኑም። የሩብ ፍጻሜው ሽግግር በነዚሁ በሶሥቱ አገሮች መካከል የሚለይለት ነው የሚመስለው። በአንጻሩ አራተኛዋ ግሪክ ከአውሮፓ ሻምፒዮንነቷ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባሳየችው ድክመት ከቀጠለች ቀድማ ስንብት ማድረጓ የማይቀር ነው። በምድብ-ሶሥትም እንግሊዝ ቢቀር በወረቀት መልካም ዕጣ የገጠማት ይመስላል። ቀሪዎቹ ተጋጣሚዎቿ አልጄሪያ፣ ስሎቬኒያና ዩ-ኤስ-አሜሪካ ይሆናሉ። ግን ጉዞው ለእንግሊዝ ቀላል ሽርሽር መሆኑም ያጠያይቃል።

ምድብ-አራት ውስጥ ጀርመን፣ አውስትራሊያ፣ ሰርቢያና ጋና በአንድ ተደልድለዋል። ብዙዎች ታዛቢዎች ጀርመን የበላይ ትሆናለች ማለታቸው አይቅር እንጂ ተጋጣሚዎቿ በቀላሉ የሚታዩ አይሆኑም። ጋና በቅርቡ ብራዚልን ግሩም በሆነ ጨዋታ በማሸነፍ ከሃያ ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ባለቤት መሆኗ ሲታወስ በተለይ በግል ችሎታ የተካኑ ተጫዋቾች ያሏት ሰርቢያም ዋዛ አይደለችም። በማጣሪያው ፈረንሣይን ያህል ቡድን ከኋላዋ ጥላ በቀላሉ በመገስገስ ነበር ለፍጻሜው ያለፈችው። ጋናም ቢሆን በአፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አራት ጨዋታዎችን፤ ለዚያውም አንድም ጎል ሳይገባባት በማሸነፍ በቀደምትነት ያለፈችው አገር ነበረች። በጀርመኑ አሠልጣኝ በዮአሂም ሉቭ ግምት ከሆነ ጋና በወቅቱ አፍሪቃ ውስጥ ጠንካራ ከሚባሉት ቀደምት ቡድኖች አንዷ ናት።

“ጋና ለኔ ከአልጄሪያ ጋር፤ ማለትም ከአይቮሪ ኮስት ቀጥሎ አፍሪቃ ውስጥ ጠንካራዋ አገር ናት። ግሩም ተጫዋቾችም አሏት። ጀርመን ውስጥ በተካሄደው ባለፈው የዓለም ዋንጫ ውድድርም ድንቅ ጨዋታ ነበር ያሳየችው። ማይክል ኤሢየን ለምሳሌ፤ አምበላችን ሚሻኤል ባላክ በሚገባ ያውቀዋል፤ እርሱና መሰሎቹ በከፍተኛ ደረጃ የሚጫወቱ ናቸው”

ጋና እንግዲህ ከፍተኛ ግምት ሲሰጣት አራተኛዋ አውስትራሊያም በትጉ አጨዋወቷ ለአንዱ ወይም ለሌላው መሰናክል በመሆን የሩብ ፍጻሜውን አየር ለመተንፈስ ልትበቃ የምትችል ናት። ከጀርመን ጋር መመደቧም በሃላፊዎቿ ዘንድ ያን ያህል ድንጋጤን አላስከተለም። አሠልጣኟ ፒም ፌርቤክ እንዲያውም ከአሁኑ ለግጥሚያው መጓጓቱን ነው የገለጸው።

“አዎን፤ ሆላንዳዊ ነኝ። መገናኘታችን ግሩም ነው። እርግጥ ምድቡ ቀላል ነው ብዬ አላስብም። ግን ለኔ በግሌ ይህ በመጀመሪያ ከጀርመን የምናካሂደው ግጥሚያ በጣም የሚያስደስተኝ ነው የሚሆነው”
ጀርመንም ወደ ሩብ ፍጻሜው ለመዝለቅ ከባድ ሥራ ሳይጠብቃት አይቀርም። የምድብ-አምሥት ተጋጣሚዎች ደግሞ ኔዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ጃፓንና ካሜሩን ሲሆኑ በመካከላቸው ጠባብ ፉክክር መስፈኑ የማይቀር ነው የሚመስለው። እርግጥ የአውሮፓ ማጣሪያውን በሽርሽር ያለፈው የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን ትልቁ ክብደት የሚሰጠው ሲሆን የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ተወካይ ካሜሩን ቢቀር ከጃፓንና ከዴንማርክ ልቆ ለመገኘት በሚገባ መታገሏ ግድ ነው። በተቀረ ሁሉም ወደ ሩብ ፍጻሜው የመሻገር ዕድል አላቸው። በደቡብ አፍሪቃው ዕጣ አወጣጥ ገዳም አገር ታይቷል ከተባለ ምናልባትም ኢጣሊያ ነበረች። ኢጣሊያ በምድብ-ስድሥት ከፓራጉዋይ፣ ከኒውዚላንድና ከስሎቫኪያ ጋር ስትደለደል ተዓምር ካልተፈጠረ ወደ ሩብ ፍጻሜው ለመዝለቅ በሩ ከወዲሁ ተከፍቶላታል። በዚህ ምድብ ውስጥ ጥያቄው ማን በሁለተኝነት ያልፋል የሚል ነው የሚሆነው።

የሞት የተባለው የብራዚል ምድብ

የፕሬቶሪያው ዕጣ አወጣጥ ሂደት በአንድ በኩል ለኢጣሊያ ቀና ሆኖ ሲያልፍ በአንጻሩ ለአምሥት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለብራዚል ድብ-ዕዳን ያህል ነው የሆነው። በዕጣው አወጣጥ ሂደት አሠልጣኙን ካርሎስ ዱንጋን ለተመለከተ ገጽታው ስንክሣር የሚናገር ነበር። ብራዚል ከፖርቱጋል፣ ከአይቮሪ ኮስትና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ስትደለደል ታዛቢዎች ይህን ምድብ ከወዲሁ የሞት ምድብ ብለውታል። ፖርቱጋል ከብራዚል የሚመሳሰል የአጨዋወት ስልት ስላላት ለሤሌሳኦው የምትመች አይደለችም። በቼልሢው ኮከብ በዲዲየር ድሮግባ የሚመራው የአይቮሪ ኮስት ቡድን ደግሞ ሲበዛ የሰከነ ነው። ሰሜን ኮሪያም ቢሆን በዚህ ምድብ ውስጥ ምናልባት ቀለል ያለችው ተጋጣሚ ትምሰል እንጂ እንዳትናቅ ታሪክ በጀርባዋ አለ። ሰሜን ኮሪያ እንግሊዝ ውስጥ እ.ጎ.አ. በ 1966 ዓ.ም. በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ኢጣሊያን ታህል አገር ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ 2-1 ቀጥታ ከውድድሩ ማሰናበቷ የሚታወስ ነው።
የሰሜን ኮሪያ ተጫዋቾች ታዲያ በአገራቸው የጀግና አቀባበል ሲደረግላቸው የኢጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ሮማ ላይ የጠበቀው የቲማቲም እሩምታ ነበር። የብራዚል ስጋት እንግዲህ ያለ ምክንያት አይደለም። በተረፈ በመጨረሻውና ስምንተኛው-ምድብ ስፓኝ ጥሩ ዕጣ ገጥሟታል ለማለት ይቻላል። ተጋጣሚዎቿ ስዊትዘርላንድ፣ ሆንዱራስና ቺሌ ሲሆኑ ወደ ሩብ ፍጻሜው በደህና መሸጋገሩ ያን ያህል የሚከብዳት አይሆንም። በአጠቃላይ ግን ኳስ ድቡልቡል በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫም ብዙ ተዓምር ማሳየቷ የማይቀር ነው። ሃይሌ ገ/ሥላሴን ጨምሮ በዕጣ አውጭነት ባለፈው አርብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ከዋክብት ዕጆች ገዳምነታቸው ለማን እንደሚሆን ከመንፈቅ በኋላ የምንደርስበት ይሆናል።

ድርብ የኢትዮጵያ የማራቶን ድል

ያለፈው ሰንበት የኢትዮጵያ አትሌቶች ድርብ የማራቶን ድል የተጎናጸፉበት ነበር። የቤይጂንግ ኦሎምፒክ የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ጸጋዬ ከበደ ጃፓን-ፉኩኦካ ላይ ትናንት በተካሄደ የማራቶን ሩጫ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ አሸናፊ ሆኗል። የ 22 ዓመቱ ወጣት አትሌት 42ቱን ኪሎሜትር ያቋረጠው ግሩም በሆነ ሰዓት የራሱንም ጊዜ በማሻሻል ነበር። በለንደን ማራቶን አስመዝግቦት የነበረውን 2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ 20 ሤኮንድ ጊዜ በሁለት-መቶኛ ሤኮንድ ለማሻሻል በቅቷል። ይሄው በዓለም ላይ ዘጠነኛው ፈጣን ጊዜ ሲሆን ለፉኩኦካም አዲስ ክብረ-ወሰን ነው። ሌላው ኢትዮጵያዊ ተወዳዳሪ ተከስተ ከበደም ሁለተኛ ሲሆን የኡክራኒያው ዲሚትሮ ባራኖቭስኪይ ደግሞ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። በሊባኖስ ማራቶንም ቀደምቶቹ የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቶች ነበሩ። መሐመድ ተማም በወንዶች ሚህረድ ታደሰም በሴቶች አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል።

ቴኒስ ዴቪስ-ካፕ ፍጻሜ

ስፓኝ ባርሤሎና ላይ በተካሄደው የቴኒስ ዴቪስ-ካፕ ፍጻሜ ቼክ ሬፑብሊክን በማሽነፍ ለድል መብቃቷ በአካል ጉዳት በተደጋጋሚ መሰናክል የገጠመው የአገሪቱ ኮከብ ራፋኤል ናዳል ፈታኙን ዓመት በደስታ እንዲዘጋ መልካም አጋጣሚ ሆኖለታል። ስፓኝ በናዳል፣ ዴቪድ ፌሬር፣ ፌርናንዶ ቫርዳስኮና በሎፔዝ አማካይነት ያሸነፈችው በለየለት 5-0 ውጤት ነው። የዘንድሮው ድል ለስፓኝ ከ 2000 ዓ.ም. ወዲህ አራተኛው ይሆናል። በተረፈ የአንዴዋ የዓለም ቀደምት ተጫዋች የቤልጂጓ ኮከብ ጁስቲን ሄኒን ትናንት በአገሯ ቻርሌሮይ ላይ በተካሄደ የፍጻሜ ግጥሚያ የኢጣሊያ ተፎካካሪዋን ፕላቪያ ፓኔታን በማሸነፍ ከዓመት ተኩል ቆይታ በኋላ ወደ ቴኒሱ መድረክ ለመመለስ በቅታለች። ሄኒን በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በወቅቱ 12ኛ የሆነችውን ኢጣሊያዊት ያሸነፈችው 6-4, 6-4 በሆነ ውጤት ነው።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል የዘንድሮው የብራዚል ሻምፒዮን ፍላሜንጎ ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ ሆኗል። ፍላሜንጎ ለዚህ ክብር የበቃው ትናንት ግሬሚዮን 2-1 ከረታ በኋላ ነው። ክለቡ የብራዚልን ዋንጫ ሲያገኝ ከ 17 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን አያሌ ደጋፊዎቹ ድሉን ሪዮ ውስጥ በአደባባይ ዳንኪራና በርችት ተኩስ አክብረዋል። ኢንተርናሺናል ሁለተኛ ሲሆን ሣኦ-ፓውሎ ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ክሩዜሮ አራተኛ ወጥቷል። ኬንያ ውስጥ የሚካሄደው የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ደግሞ ወደ ሩብ ፍጻሜው ሲሸጋገር እነዚሁ አራት ግጥሚያዎች ዛሬና ነገ ይካሄዳሉ። ያለፈው ሻምፒዮን ኡጋንዳ ከኬንያ፤ ዛምቢያ ደግሞ ከዛንዚባር ዛሬ የሚካሄዱት ጨዋዎች ናቸው። ሌላው የሣምንቱ ታላቅ የእግር ኳስ ዜና የአርጄንቲናው ተወላጅ የባርሤሎና ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ የዓመቱ የአውሮፓ ድንቅ ተጫዋች ተብሎ መመረጡ ነው። የሬያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ዘንድሮ ዙፋኑን አስረክቦ ሁለተኛ ሲሆን ሌላው የባርሤሎና መንኮራኩር ክሣቪ ሶሥተኛ ወጥቷል። በእጩነት ከቀረቡት አያሌ ተጫዋቾች መካከል ስድሥት የስፓኝ ክለብ ተጫዋቾች በመጀመሪያዎቹ ሰባት ቦታዎች ውስጥ መገኘታቸው ፕሪሜራ-ዲቪዚዮኑ ምን ያህል ሃያል እንደሆነ የሚመሰክር ነው።

መሥፍን መኮንን

RTR/AFP/DW

አርያም ተክሌ