1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 24 2001

ዓለምአቀፍ አትሌቲክስና የአውሮፓ እግር ኳስ

https://p.dw.com/p/I1YW
የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ዋንጫ
የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ዋንጫምስል picture-alliance / Sven Simon

ያለፈው ሣምንት ታላቅ የአትሌቲክስ ውድድር ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ኒውዮርክ ላይ የተካሄደው ነበር። በኒውዮርኩ ግራንድ-ፕሪ በአጭርና መካከለኛ ርቀት ሩጫ በተለይ የአሜሪካ አትሌቶች አይለው ሲታዩ በ 5 ሺህ ሜትር እንደተለመደው የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ጠንከር ብለው ታይተዋል። በወንዶች አንድ መቶ ሜትር ሩጫ ሁለቱ አሜሪካውያን ማይክል ሮጀርስና ትራቪስ ፓድጌት ጃማይካዊውን ስቲቭ ማሊንግስን አስከትለው ሲያሸንፉ በተለይ ድንቁ ውጤት ታይሰን ጌይ በሁለት መቶ ሜትር ያስመዘገበው ነበር።
የአንዴው የአሜሪካ የመቶና የሁለት መቶ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን በኒውዮርኩ ውድድር በዓለም ላይ ሶሥተኛውን ፈጣን ጊዜ ለመሮጥ በቅቷል። እስካሁን በዚህ ርቀት ፈጣኑ ጊዜ ጃማይካዊው ኡሤይን ቦልት በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ያስመዘገበው ክብረ-ወሰን ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ አሜሪካዊው ማይክል ጆንሰን በ 1996 ኦሎምፒክ ያገኘው ነው። ታይሰን ጌይ በአካል ጉዳት የተነሣ ባለፈው ኦሎምፒክ ሳይሳተፍ መቅረቱ አይዘነጋም። በነገራችን ላይ በኒውዮርኩ ውድድር ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡትም አሜሪካውያን ናቸው።

የአሜሪካ ወንድ አትሌቶች ከዚሁ በተጨማሪ በአራት መቶ፣ በስምንት መቶና በ 1,500 ሜትር ሩጫም ሲያሸንፉ በአራት መቶ ሜትር መሰናክልና በጦር ውርወራም ቀደምቱ ነበሩ። በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያዊው ሚካህ ኮጎ ሲያሸንፍ ከኬንያ የመነጨው አሜሪካዊ በርናርድ ላጋት ሁለተኛ፤ እንዲሁም ደጀን ገብረ መስቀል ከኢትዮጵያ ሶሥተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል።

በሴቶችም ቢሆን የአሜሪካ አትሌቶች ልዕልና ጎልቶ ሲታይ በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ የቤይጂንግ ኦሎምፒክ የሁለት ወርቅ ሜዳሊያዎች ተሸላሚ የሆነችው ጥሩነሽ ዲባባ ድሉን ለኬንያዊቱ ለሊኔት ማሣይ መተው ግድ ሆኖባታል። ጥሩነሽ ዲባባ ከቤይጂንግ ኦሎምፒክ ታላቅ ድሏ በኋላ በብዙ ውድድሮች ባለመሳተፏ ጥቂት የተለመደው ቅልጥፍና ሳይጎላት አልቀረም። ለማንኛውም ሩጫውን በሁለተኝነት ስትፈጽም ገንዘቤ ዲባባም ሶሥተኛ ሆናለች። በዛሬው ዕለት ደግሞ ኔዘርላንድ-ሄንገሎ ላይ በሚካሄድ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ሃይሌ ገ/ስላሤንና ቀነኒሣ በቀለን የመሳሰሉ ቀደምት አትሌቶች ይሳተፋሉ። የማራቶኑ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ሃይሌ በሄንገሎ እስካሁን አራት የዓለም ክብረ-ወሰኖችን ሲያስመዘግብ በዛሬው ውድድርም የሚያልመው ይህንኑ ነው።

ሃይሌን ስድሥት የኦሎምፒክ ወርቅ አሸናፊዎች፤ እንዲሁም ዘጠኝ የዓለምና የአውሮፓ ሻምፒዮኖች በተፎካካሪነት የሚጠብቁት ሲሆን ቀነኒሣ በቀለ በበኩሉ በ 1,500 ሜትር ሩጫ መወዳደሩን መርጧል። ቀነኒሣ ይህን ርቀት የመረጠው ለፊታችን ነሐሴ የበርሊን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚያደርገው ዝግጅት ፍጥነቱን ለመፈተሽ ነው። ዋና ተፎካካሪዎቹ የኬንያና የሞሮኮ አትሌቶች ናቸው።

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሻምፒዮና መጠቃለያ ወቅት ታላቁና ማራኪው ውድድር እርግጥ በሣምንቱ አጋማሽ ላይ በኤፍ.ሢ.ባርሤሎናና በማንቼስተር ዩናይትድ መካከል የተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ ነበር። ባርሣ በተለየ ልዕልና 2-0 በማሸነፍ ያለፈውን ዓመት ሻምፒዮን ከዙፋኑ አውርዷል። ወኪላችን ተክለእዝጊ ገብረየሱስ በሮማው ውብ ስታዲዮም ከተገኙት ተመልካቾች አንዱ ነበር፤ የግጥሚያውን ሂደትም ተከታትሏል።
በብሄራዊ ውድድሮች ላይ እናተኩርና በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ የዘንድሮው ውድድር በስፓኝ፣ በእንግሊዝ፣ በኢጣሊያ፣ በጀርመንና በኔዘርላንድ ቀደም ብሎ ሲለይለት በፈረንሣይ ሻምፒዮኑ የታወቀው በዚህ ሰንበት የመጨረሻ ግጥሚያ ነበር። ጂሮንዲን-ቦርዶው ኬንን 1-0 በመርታት ከአሥር ዓመታት በኋላ እንደገና የፈረንሣይ ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። በአንጻሩ ለኬን የተረፈው ከናንትና ከሌ-ሃቭር ጋር ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መከለሱ ነው። ከጥቂት ሣምንታት በፊት ይበልጡን ለሻምፒዮንነት የተቃረበ መስሎ የታየው ኦላምፒክ ማርሤይ በሁለተኝነት መወሰኑ ግድ ሲሆንበት በተከታታይ ለስምንተኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን አልሞ የነበረው ኦላምፒክ ሊዮን ደግሞ ውድድሩን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። ሁለቱን ቡድኖች የሚያጽናና ነገር ቢኖር በመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የሚሳተፉ መሆናቸው ነው።

በአንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ሆነ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ባዶ ዕጁን ቀርቶ የነበረው ቀደምት ክለብ ኤፍ.ሢ.ቼልሢይ ባለፈው ቅዳሜ በዝናኛው ዌምብሌይ ስታዲዮም በተካሄደው የእንግሊዝ እግር ኳስ ፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ኤቨርተንን 2-1 በመርታት የማታ ማታ ማካካሻውን አግኝቷል። ኤቨርተን በአጥቂው በሉዊስ ሣሃ አማካይነት በፌደሬሺኑ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ታሪክ ውስጥ ፈጣኗን ጎል ጨዋታው በተጀመረ በ 25 ሤኮንዶች ውስጥ ሲያስቆጥር የቼልሢይ ዕጣ ለጊዜውም ቢሆን የጨለመ መስሎ ታይቶ ነበር። ይሁንና ዲዲየር ድሮግባና ፍራንክ ላምፓርድ የተቀሩትን ጎሎች በማስቆጠር የቡድናቸውን ድል አረጋግጠዋል።

በዚህ በጀርመንም ሁኔታው ከሞላ-ጎደል ተመሳሳይ ነበር። የቡንደስሊጋው ውድድር ዘንድሮ ብዙም ያልቀናው ቬርደር ብሬመን የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ዋንጫን በማሽነፍ የጨዋታውን ወቅት በደስታ ለመዝጋት በቅቷል። በበርሊኑ ኦሎምፒያ ስታዲዮም ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ ብሬመንና ሌቨርኩዝን ከሞላ-ጎደል አቻ ሆነው ሲታዩ በ 73 ሺህ ተመልካች ፊት ለብሬመን ብቸኛዋን ጎል በ 58ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ቱርኩ-ጀርመናዊ ሜሱት ኡዚል ነበር። ለኢጣሊያው ክለብ ለጁቬንቱስ ቱሪን የተሸጠው የቡድኑ ብራዚላዊ ኮከብ ዲየጎ እንደገና ድንቅ ጨዋታ ሲያሳይ ከሶሥት ዓመታት ቡንደስሊጋ በኋላ ስንብት አድርጓል። ያሳዝናል የጀርመን ቡንደስሊጋ ያለ ዲየጎ ተውኔት ውበቱን እንደሚያጣ አንድና ሁለት የለውም።

በፖርቱጋል አንደኛ ዲቪዚዮን ኤፍ.ሢ.ፖርቶ ከሻምፒዮንነቱ ባሻገር ብሄራዊውን ዋንጫም ሲጠቀልል በደቡብና ምሥራቅ አውሮፓም ሻምፒዮናው በአብዛኛው ለይቶለታል። በቡልጋሪያ ሊጋ ሌቭስኪ ሶፊያ ለ 26ኛ ጊዜ ሻምፒዮንነቱን ሲያረጋግጥ በጎረቤቲቱ በሩሜኒያ ደግሞ ኡኒሬያ ኡርዚቼኒ ለመጀመሪያ ዋንጫው በቅቷል። በኡክራኒያም ፖልታቫ በተመሳሳይ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን ሲሆን የሩሢያው CSKA ሞስኮ ደግሞ አዲሱን ሻምፒዮን ሩቢን ካዛንን 1-0 በመርታት የፌደሬሺኑ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል። በተረፈ በፖላንድ ክራኮቭ ሻምፒዮንነቱን አስመልሷል።

MM/AFP/RTR