1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 10 2006

በሁለት ሣምንታት ጊዜያት ውስጥ ብቻ በአስደናቂ ፍጥነቷ ሶስት ክብረወሰኖችን ሰባብራለች፤ ሀገሯንም በዓለም ሕዝብ ፊት ደጋግማ አስጠርታለች። አትሌት ገንዘቤ ዲባባ። ሶስተኛ ተከታታይ ድሏን ከትናንት በስትያ በብሪታንያው የቢርሚንግሐም ግራንድ ፕሪክስ የስታዲየም ውስጥ ውድድር ነው ያስመዘገበችው።

https://p.dw.com/p/1BAbk
800 Meter Lauf Männer Goldmedaille Mohammed Aman Leichtathletik Weltmeisterschaft 2013 Moskau
ምስል Getty Images

በእዚሁ ውድድር በወንዶች የ800 ሜትር ፉክክር ሌላኛው የሀገሯ ልጅ መሐመድ አማን ተጨማሪ ክብር ወሰን ሰብሯል። አትሌቶቹ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሲሆን፤ ደውለን ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል። የእግር ኳስ ውድድር ውጤቶችንም አካተናል።

ስታዲየም ውስጥ ለብቻዋ ስትፈተለክ ተወዳዳሪ ያለባትም አትመስል፣ አጣጣሏ የአቦሸማኔ፣ ቆራጥነቷ የአንበሣ ነው። አትሌት ገንዘቤ ዲባባ። ልክ እንደ እህቶቿ ሁሉ እሷም በድል ጎዳና መንጎማለል ጀምራለች። በብሪታንያው የቢርሚንግሐም ግራንድ ፕሪክስ የስታዲየም ውስጥ ውድድር ገንዘቤ ዲባባ ፍጥነት ጨማሪ አሯሯጩዋ ከወጣችበት ቅፅበት ጀምሮ ስምንት ዙር ለብቻዋ ማንም ሳይቀድማት ሮጣ ነው ያሸነፈችው።

ገንዘቤ ዲባባ የትናንት በስተያውን የዓለም 3000 ሜትር የስታዲየም ውስጥ ሩጫ ውድድር ያሸነፈችው በ9 ደቂቃ ከ0,48 ሠከንድ ሲሆን፤ ከኋላ የምትከተላት ተፎካካሪዋን በ20 ሠከንድ ርቀት ጥላ ነው አሸናፊ ለመሆን የበቃችው። 20 ሠከንድ በአጭር ርቀት የሩጫ ውድድር እጅግ በጣም ብዙ የሚባል ነው። ገንዘቤ ዲባባ ከሁለት ሣምንታት በፊት ጀርመን ካርልስሩኸ ውስጥ የ1500 ሜትር የስታዲየም ውስጥ የሩጫ ውድድርንም ከ3 ሠከንድ በላይ በማሻሻል ክብርወሰን አስመዝግባለች። ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ ትናንት ያሸነፈችበትን የ3000 ሜትር ውድድር ስዊድን ስቶኮልም ውስጥ በ7 ሠከንድ ማሻሻሏ ይታወሳል።

Tirunesh Dibaba Äthiopien Stade de France
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

በቢርሚንግሐሙ የስታዲየም ውስጥ ሩጫ ውድድር በወንዶች ፉክክር ከትናንት በስትያ ሌላኛው የአጭር ርቀት ሩጫ ጀግና መሀመድ አማን ተጨማሪ ክብር ወሰን ለማስመዝገብ ችሏል። መሐመድ አማን ርቀቱን በ1 ደቂቃ ከ44.53ሠከንድ በማጠናቀቅ ነው ክብር ወሰኑን የሰበረው። መሐመድን ስደውልለት ከአየር ማረፊያ ገብቶ ረፍት ለማድረግ ጋደም ብሎ ነበር። እረፍቱን ላለመሻማት አጭር ጥያቄ ነበር ያቀረብኩለት።

አትሌት መሐመድ አማን ከሁለት ሣምንታት በኋላ አውሮጳ ውስጥ በሚደረገው የሩጫ ውድድር ባለድል በመሆን የሀገሩን ስም ለማስጠራት እንደሚፈልግ አክሎ ገልጾልናል። እንዲሳካለት ምኞታችን ነው።

አሁን ወደ ቀሪዎቹ የስፖርት ዘገባዎች እንሸጋገር። በአትሌቲክስ ጀምረናልና ወደ ሩስያው የሶቺ የክረምት ኦሎምፒክ እንለፍ። የአውሮጳ ታላላቅ የእግር ኳስ ቡድኖች የውድድር ውጤቶችንና አጫጭር ዜናዎችንም አካተናል፤ ወደ በኋላ ላይ እንመለስበታለን።

በሶቺ የክረምት ኦሎምፒክ ጀርመን የወርቅ ሜዳይ በብዛት በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የቅርብ ተፎካካሪዋ ጎረቤት ኔዘርላንድ ናት። አዘጋጇ ሩስያ በሁለት ሀገራት ማለትም በኖርዌይና ስዊዘርላንድ ተቀድማ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የጀርመን የሀገር ውስጥ ሚንስትር ቶማስ ዴ ሜዚየር በውድድሩ ጀርመን ያስመዘገበችው ውጤት በጣም ጥሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

«የእስካሁኑ ውጤት ወርቁን በተመለከተ በጣም ጥሩ ነው፤ በአጠቃላይ የተገኘው የሜዳይ ብዛት ሲታይ ደግሞ ጥሩ ነው። ሆኖም የኦሎምፒክ ጨዋታው ገና አልተጠናቀቀም።»

አርብ ጥር 30 ቀን 2006 ዓም ሩስያ ሶቺ ውስጥ የተጀመረው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር የፊታችን እሁድ ይጠናቀቃል።

Sotschi 2014 - Eisschnelllauf
ምስል picture-alliance/dpa

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ቸልሲ በ57 ነጥብ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። አርሰናል አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል። ማንቸስተር ሲቲ በ54 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሊቨርፑል ከሲቲ አንድ ከመሪው ቸልሲ ደግሞ አራት ነጥብ ዝቅ ብሎ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ትናንት አርሰናል በኢሚሬት ስታዲየም ሊቨርፑልን 2 ለ1 በማሸነፍ ቀደም ሲል በሊቨርፑል የደረሰበትን የ5 ለ1 ድቀት በከፊልም ቢሆን ለመበቀል ችሏል። ማንቸስተር ሲቲ ቸልሲን ቅዳሜ 2 ለ0 በመርታት ወደ FA cup ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ ችሎዋል። ስቴቨን ጆቬቲክና ሳሚር ናስሪ ነበሩ ቸልሲን ጉድ ያደረጉት።

ትናንት ጀርመን ውስጥ በተደረጉ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ዎልፍስቡርግ ጠንካራው ሔርታ ቤርሊንን 2 ለ1 ረትቷል። ኑርንበርግ አውቡርግን 1 ለ ባዶ ሸኝቷል። ኃያላኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድና ባየር ሙንሸንም የተለመደ ድላቸውን አስመዝግበዋል። ዶርትሙንድ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን፤ ባየርን ሙንሽን ፍራይቡርግን በተመሳሳይ 4 ለባዶ አሸንፈዋል።

Wayne Rooney
ምስል picture-alliance/dpa

የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ ወደ ቸልሲ ሊዛወር ነው ሲሉ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡት ከመላ ምት ያለፈ አለመሆኑ ተጠቀሰ። ሩኒ ለማንቸስተር ዩናይትድ የ5 ዓመት ከመንፈቅ ውል ግፋ ቢል እስከ ፊታችን ረቡዕ ድረስ እንደሚፈርም ተጠቅሷል።

ዣቪየር ማሼራኖ በስተመጨረሻ ዝምታውን በመስበር ሊቨርፑል ድንቅ ቡድን ቢሆንም በቡድኑ ቆይታዬ ግን አስቸጋሪ ነበር አለ። ሊቨርፑል ልዩ ቡድን ነው፤ እናም ስሙ በመጥፎ ሊነሳ አይገባም ሲል ዣቪየር አክሎዋል። አያይዞም በሊቨርፑል ቆይታዬ የተገባልኝ ቃል ኪዳን አልተጠበቀም፤ እናም ከባርሴሎና በኩል ፍላጎቱ እያየለ ሲመጣ ቆይታዬ የበለጠ አስቸጋሪ ሆኖ ነበር ብሏል።

ከጥቂት ወራት በፊት ብራዚል ውስጥ በእሳት ተያይዞ የነበረው ስታዲየም ጉዳቱ ከተነገረው በላይ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቀሰ። የብራዚል መንግሥት ባለስልጣናት በቃጠሎው የደረሰው ጉዳት አነስተኛ ነው ሲሉ ለምን መሸፋፈን እንደፈለጉ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል። በብራዚል 12 ከተሞች ውስጥ ከተዘጋጁ ስታዲየሞች ገና ያልተጠናቀቀውና ኩያባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ስታዲየም ለዓለም ዋንጫ መድረሱ አጠራጣሪ መሆኑም ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ