1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2005

የአውሮፓ ቀደምት እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ለሻምፒዮንነት በሚደረገው ፉክክር ረገድ ከወዲሁ እየለየለት በመሄድ ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/17v9O
ምስል picture-alliance/AP

በጀርመን ባየርን ሙንሺን አመራሩን ወደ ሃያ ሲያሰፋ በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና በ 13፤ እንዲሁም በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ በ 12 ነጥቦች የበላይነቱን ይዘው ቀጥለዋል። ሣምንቱ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ቀሪዎቹ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበትም ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውድድር እንጀምርና ኤፍ ሲ ባርሤሎና ዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛን 2-0 በመርታት አመራሩን ወደ 13 ከፍ ማድረጉ ተሳክቶለታል። ለባርሣ ጎሎቹን አሌክሢስ ሣንቼዝና ሊዮኔል ሜሢ ሲያስቆጥሩ የአርጄንቲናው ኮከብ ለ 17ኛ ጊዜ በሊጋ ግጥሚያ በተከታታይ ለስኬት መብቃቱ ነው። ቡድኑ የነጥብ ልዩነቱን ሊያሰፋ የቻለው በሁለተኝነት የሚከተለው አትሌቲኮ ማድሪድ ትናንት በገዛ ሜዳው በሪያል ሶሢየዳድ 1-0 በመሸነፉ ነበር።

የአትሌቲኮ መሸነፍ ለከተማ ተፎካካሪው ለሬያል ማድሪድም ሲበጅ ሬያል በበኩሉ ግጥሚያ ሤልታ ቪጎን 2-1 በመርታት ሁለተኛውን ቦታ ሊነጥቅ በቅቷል። በነገራችን ላይ ለሬያል ሁለቱንም ጎሎች በማስቆጠር የድል ዋስትና የሆነው የፖርቱጋሉ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበር። የስፓኝ ሻምፒዮና ሊጠቃለል 11 ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ አሁን ባርሤሎና በ 71 ነጥቦች ተዝናንቶ ይመራል፤ ሬያል ማድሪድ በ 58 ነጥቦች ሁለተኛ፤ እንዲሁም አትሌቲኮ በ 57 ሶሥተኛ በመሆን ይከተላሉ።

Manchester City VS. QPR
ምስል picture-alliance/dpa

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ የፌደሬሺኑ ዋንጫና የሊጋው ሻምፒዮና ውድድር ተጣምረው የተካሄዱበት ነበር። በፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ትናንት ማንቼስተር ዩናይትድ በገዛ ሜዳው ከቼልሢይ ባደረገው ግጥሚያ በእኩል ለእኩል 2-2 ውጤት መወሰን ግድ ሆኖበታል። ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ቼልሢይ ውጤቱን ያስተካከለው 2-0 ከተመራ በኋላ የበኩሉን ጎሎች በማስቆጠር ነበር። ማንቼስተር ዩናይትድ ለፖርቱጋላዊ አጥቂው ለናኒ በተሰጠ አከራካሪ ቀይ ካርድ ሳቢያ ባለፈው ማክሰኞ በሬያል ማድሪድ ተሸንፎ ከአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር በሩብ ፍጻሜው ከስንብት አደጋ ላይ መውደቁ አይዘነጋም።

ለማንኛውም የማኒዩና የቼልሢይ አሸናፊ በዌምብሌይ ስታዲዮም በሚካሄደው ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ባርንስሊይን 5-0 ከረታው ከማንቼስተር ሢቲይ ይገናኛል። በተቀሩት ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ዊጋን አትሌቲክ ኤቨርተንን 3-0 በመሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋንጫው ግማሽ ፍጻሜ ሲደርስ ሚልዎልና ብላክበርን ሮቨርስ ደግሞ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል። በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ማንቼስተር ዩናይትድ በ 71 ነጥቦች በአስተማማኝ ሁኔታ መምራቱን ሲቀጥል ማንቼስተር ሢቲይ 12 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። ቶተንሃም ሆትስፐር በአንድ ጨዋታ ብልጫ በ 29 ግጥሚያዎች 54 ነጥቦች ይዞ ሶሥተኛ ሲሆን ቼልሢይ በ28 ግጥሚዎች 52 ነጥቦችን በመሰብሰብ በአራተኝነት በቅርብ ይከተላል።

Bundesliga Bayern München Fortuna Düsseldorf
ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ሻምፒዮናው ሊጠቃለል ዘጠኝ ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ባየርን ሙንሺን የማይደረስበት እየሆነ መራመዱን እንደቀጠለ ነው። ከወቅቱ አሰላለፍ ስሌት ባየርን ውድድሩ አራት ወይም ሶሥት ጨዋታዎች ቀርተውት ቀድሞ ሻምፒዮን ሊሆን ይችላል። የበላይነት ማለት እንግዲህ እንዲህ ነው። የአገሪቱ ሬኮርድ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ባለፈው ሰንበትም ፎርቱና ዱስልዶርፍን 3-2 በመርታት የበላይነቱን ሲያስመሰክር አመራሩን ወደ 20 ማስፋቱ ሆኖለታል።

ለዚህም ምክንያቱ ሁለተኛና ሶሥተኛው ዶርትሙንድና ሌቨርኩዝን በየበኩላቸው ግጥሚያ መሸነፋቸው ነው። ያለፉት ሁለት ውድድር ወቅቶች ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድ በአካባቢ ተቀናቃኙ በሻልከ 2-1 ሲረታ ሌቨርኩዝንም አከራካሪ በሆነች ፍጹም ቅጣት ምት በማይንስ 1-0 ተሸንፎ ከሜዳ መውጣቱ ግድ ሆኖበታል። ሻልከ ፍራንክፉርትን አልፎ አራተኛውን ቦታ ሲይዝ ፍራንክፉርት አሁን አምሥተኛ ነው፤ ሃምቡርግ ደግሞ በስድሥተኝነት ይከተላል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አም ቀደምቱ ጁቬንቱስ አመራሩን ወደ ዘጠኝ ሲያሰፋ ሁለተኛው ናፖሊ ደግሞ ከአራት እኩል ለእኩል ውጤቶች በኋላ በቺየቮ 2-0 ተሸንፏል። ይህም በበኩሉ ግጥሚያ ጀኖዋን 2-0 የረታው ኤ ሲ ሚላን ናፖሊን እስከ ሁለት ነጥብ ልዩነት እንዲቃረብ ነው ያደረገው። ፊዮሬንቲና አራተኛ፤ ኢንተር ሚላን አምሥተኛ፤ ላሢዮ ስድሥተኛ! በፈረንሣይ ሻምፒዮና ቀደምቱ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ናንሢይን 2-1 በመርታት አመራሩን ወደ አራት ከፍ ሊያደርግ በቅቷል።

ይህም የሆነው ሁለተኛው ኦላምፒክ ሊዮን ከማርሤይ ባካሄደው ግጥሚያ ባዶ-ለባዶ በሆነ ውጤት በመወሰኑ ነው። በነገራችን ላይ ስዊድናዊው ዝላታን ኢብራሂሞቪች ለፓሪሱ ክለብ 23ኛና 24ኛ ጎሎቹን ማስቆጠሩ ተሳክቶለታል። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን አይንድሆፈን በመሸነፉ አያክስ አምስተርዳም አመራሩን ሲይዝ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ቤንፊካ ሊዝበን ፖርቶን በሁለት ነጥቦች ርቀት አስከትሎ መምራቱን እንደቀጠለ ነው። በተቀረ ኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ለ 40ኛ ጊዜ የግሪክ ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። ፒሬውስ የሊጋው ሻምፒዮን የሆነው ትናንት ኤኢኬ አቴንን 3-0 ከረታ በኋላ ነው።

በትናንትናው ዕለት ጃፓን-ናጎያ ላይ ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ የሴቶች ማራቶን ሩጫ ውድድር የአገሩ ተወላጅ ሩዮኮ ኪዛኪ ብርሃኔ ዲባባን ቀድማ ለማሸነፍ በቅታለች። ኪዛኪ ለድል የበቃችው በመጨረሻዎቹ ሁለት ኪሎሜትሮች ከብርሃኔ ጋር ከባድ ትግል በማድረግ ነበር። የአቴን ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የነበረችው ሌላ ጃፓናዊት ሚዙኪ ኖጉቺ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥታለች።

Schweden Brunnsparken in Göteborg um Mitternacht
ምስል picture-alliance/dpa

አትሌቲክን ካነሣን በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው ከተሳተፉት ቀደምት አትሌቶች መካከል አንዷ አበባ አረጋዊ ነበረች። አትሌቷ ምንም እንኳ ለሜዳሊያ ባትበቃም በ 1,500 ሜትር ሩጫ ለፍጻሜ ደርሣ አምሥተኛ በመሆን በዚህ ርቀት በዓለም ላይ ጠንካሮች ከሚባሉት አንዷ እንደሆነች ማስመስከሯ የሚታወስ ነው። ወጣቷ አትሌት አሁን የስዊድን ዜጋ ስትሆን በቅርቡ በዚያው ጎተቦርግ ላይ ተካሂዶ በነበረው የአውሮፓ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመሳተፍም በተለመደ ርቀቷ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅታ ነበር።

አትሌቷ ባለፉት ሶሥትና አራት ዓመታት ስዊድን ውስጥ መኖሯ ቢታወቅም ዜግነት ለመለወጥ ምን እንዳነሳሳትና በአውሮፓው ሻምፒዮና ላይ ስላስመዘገበችው ውጤት ጭምር ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በመሆኑም በጉዳዩ ገለጻ እንዲሰጠኝ ኔዘርላንዳዊ ማኔጀሯን ጆስ ሄርመንስን ዛሬ በስልክ ጠይቄ ነበር። ሄርማንስ እንዳረጋገጠልኝ አትሌቷ ለኢትዮጵያ በመሮጥ ፈንታ ለስዊድን መወዳደር የመረጠችበት የተለየ ነገር የለም።

« የለም፤ ምንም ምክንያት የለም። ለረጅም ጊዜ በሰቶክሆልም ስዊድን ውስጥ ኖራለች። እና ብዙ ቤተሰብም አላት እዚያው የሚኖር። ለረጅም ጊዜ ደግሞ የስዊድን ዜጋ ናት። እና እንዲህ ነው የሆነው። ኢትዮጵያን በመጻረር ዓይነት ምክንያት የሆነ ነገር አይደለም።እርግጥ ስዊድን ውስጥ ዜግነት እንድትቀበል መጠየቋና ግፊት መደረጉ አልቀረም። እናም ይህን ምርጫ አድርጋለች»

እርግጥ ሄርመንስ በዜግነቱ ለውጥ መፋጠን ሳይደነቅም አልቀረም።

«እኔም ለውጡ በፍጥነት በመካሄዱ ተደንቄያለሁ። በኦሎምፒክ በመሳተፏ የተነሣ በደምቡ መሠረት ምናልባት ሶሥት ወይም አራት ዓመታት ይፈጃል የሚል ግምት ነበረኝ። ግን ዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሺን በቀላሉ ፈቃድ የሰጠ ይመስለኛል። እርግጥ በሌላ በኩል እንደሚታሰበው በተቻኮል የሆነ ነገርም አይደለም። አበባ በስዊድን ብዙ ሁኔታዎችንም አሳልፋለች። የስዊድንን ቋንቋ ከአሁኑ ትናገራለች። እና እንዲያው ከዛሬ ወደነገ የሆነ ነገርም አይደለም»

በሌላ በኩል በፖለቲካም ሆነ በገንዘብ ምክንያት ለምሳሌ እንደ ኬንያ ዜግነትን የሚለውጡ አትሌቶች እየበዙ ነው የመጡት። አንዳንድ የኢትዮጵያ አትሌቶችም ቢሆን ባለፉት ዓመታት ወደ ባህሬይን፣ ካታር ወይም ቱርክ ተሻግረዋል። ይህ ሂደት ደግሞ ምናልባትም ቀጣይነት ሊኖረው የሚችል ነው።

«ሊሆን ይችላል። ወደ ብሩናይ ወይም መሰል ቦታዎች የሚሄዱት በመሠረቱ ታላላቆቹ አትሌቶች አይደሉም። አበባ አረጋዊ ደግሞ በዓለም ላይ ግሩም ከሚባሉት አንዷ ናት። ይሄው አሁን የአውሮፓ ሻምፒዮን ለመሆን በቅታለች። ከኢትዮጵያ ለመቀየሯ ምክንያቷ የተለየ ነው። ቅድም እንዳልኩት ስዊድን ውስጥ ብዙ ኖራለች፤ ዘመዶቿ እዚያ ናቸው፣ ዜግነትም አላት። የተሸጠች አይደለችም። ብሩናይ የሄዱት ግን የተሸጡ ናቸው። ገንዘብ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ሆና ብዙ ማግኘት በቻለች ነበር። የርሷን ሁኔታ ከመሸጥ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም»

አበባን ለማንኛውም ስኬት እንመኝላታለን፤ ወደፊት በቀጥታ ልናነጋግራት እንደምንበቃም ተሥፋችን ነው።

Cristiano Ronaldo Real Madrid
ምስል Getty Images

በእግር ኳስ ለማጠቃለል ነገና ከነገ በስቲያ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ሩብ ፍጻሜ መልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት የጀርመኑ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ የመጀመሪያ 3-0 ድሉን ይዞ ዶኔትስክን በሜዳው የሚያስተናግድ ሲሆን የኡክራኒያው ክለብ ውጤቱን መለወጡ ብዙ ያጠራጥራል። ማንቼስተር ዩናይትድም በመጀመሪያው ግጥሚያ 2-1 በመሸነፉ ከሬያል ማድሪድ ጋር የሚያደርገው ትግል ቀላል አይሆንም።

በማግሥቱ ረቡዕ ሚዩኒክ ውስጥ ከባየርን ሙንሺን የሚጋጠመው አርሰናልም ወደፊት ለመዝለቅ ተዓምር ሳያስፈልገው አይቀርም። የእንግሊዙ ክለብ በመጀመሪያው ግጥሚያ በገዛ ሜዳው 3-1 መረታቱ ይታወሳል። ባርሤሎናም በኦ ሲ ሚላን የደረሰበትን 2-0 ሽንፈት ለመቀልበስ ምናልባት የታላቁን ጠቢብ የሊዮኔል ሜሢን ጥበብ ከመቼውም በላይ ሳይሻ አይቀርም። በተረፈ ፓሪስ ሣንት ዠርማን ከቫሌንሢያ፣ ጁቬንቱስ ከሤልቲክ ግላስጎው፤ ሻልከ ከጋላታሣራይ ኢስታምቡልና ማላጋ ከፖርቶ ቀሪዎቹ ግጥሚያዎች ይሆናሉ።

በተረፈ የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን ካሜሩናዊውን ኢሣ ሃያቱን ለሰባተኛ ጊዜ ፕሬዚደንቱ አድርጎ መርጧል። ድርጅቱ እንዳስታወቀው መጪው የአራት ዓመት ሥልጣን ለሃያቱ የመጨረሻው ነው።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ