1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ ግንቦት 10 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ሰኞ፣ ግንቦት 10 2007

ሽቴፋን ጄራርድ ለሊቨርፑል ከ700 በላይ ጊዜያት ተሰልፏል። ቡድኑን ከ 3 ለ1 ሽንፈት መታደግ ግን አልቻለም። ከእንግዲህ ለሊቨርፑል ተሰልፎ እንደማይቻወት በገለጠበት ወቅት ደጋፊዎች ልባቸው ቢነካም ድጋፋቸውን ግን ሰጥተውታል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፣ የጀርመን ቡንደስ ሊጋ እና ሌሎች የአውሮጳ ከፍተኛ ቡድኖች ውድድር ሊጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል።

https://p.dw.com/p/1FRdP
Steven Gerrard
ምስል picture-alliance/dpa/Georgi Licovski

የስፖርት ዘገባ፤ ግንቦት 10 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

በሻንጋይ እሁድ ግንቦት ግንቦት 9 ቀን ዓ.ም በተከናወነው ዲያመንድ ሊግ የ5000 ሜትር የሴቶች ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና አሸናፊ ሆናለች። አልማዝ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 14:14.32 ነው። የ23 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ወጣት ሯጭ አልማዝ በጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የቆየውን የዓለም ክብር ወሰን ለመስበር የቀራት ሦስት ሠከንድ ብቻ ነበር። የገባችበት ሠዓት በ5000 ሜትር የሩጫ ውድድር ታሪክ ሦስተኛው ፈጣን ሠዓት ተብሎም ተመዝግቦላታል።

ኬኒያዊቷ ቪዮላ ጄሌጋት ኪቢዎት ከአልማዝ 36 ሠከንድ ዘግይታ ሁለተኛ ስትወጣ፤ ኢትዮጵያውያቱ ሠንበሬ ተፈሪ እና ዓለሚቱ ሔሮዬ ሦስተኛ እና አራተኛ በመሆን ተከታትለው ለመግባት ችለዋል። በትናንትናው የሻንጋይ ዲያመንድ ሊግ የሩጫ ውድድር 40,000 ሰው መካፈሉ ተዘግቧል።

ቅዳሜ ዕለት በኳታር በተከናወነው የዳይመንድ ሊግ የ3,000 ሜትር የ ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው ሐጎስ ታዋቂውን ሞ ፋራሕን በማሸነፍ አንደኛ መውጣቱ ይታወሳል። ከጥቂት ቀናት በፊት 21ኛ የልደት በዓሉን ያከበረው ሐጎስ ገብረ ሕይወት ውድድሩን በአንደኛነት ያጠናቀቀው በ7 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ ከ08 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ነበር።

በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ፍልሚያ ቅዳሜ ዕለት ሽቱትጋርት ከዜሮ ተነስቶ ሐምቡርግን 2 ለ1 አሸንፏል። በዚህም መሠረት በደረጃ ሠንጠረዡ ከታች ወደ 16ኛ ከፍ ለማለት ችሏል። በሻልከ 1 ለምንም የተረታው ፓዴርቦርን በደረጃ ሠንጠረዡ ወደ መጨረሻው ጠርዝ ተገፍትሯል። ፓዴርቦርን ከሐምቡርግ ዝቅ ብሎ የመጨረሻው 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሐምቡርግ እና ፓዴርቦርን ቀሪውን አንድ የቡንደስ ሊጋ ጨዋታ ከተሸነፉ በቀጥታ ተሰናባች ይሆናሉ። ሆኖም ዕድላቸው ሙሉ ለሙሉ መከነ ማለት አይደለም። በተለይ ሐምቡርግ ቀጣዩን ጨዋታ አሸንፎ ሽቱትጋርት እና ሐኖቨር ቢሸነፉ በቡንደስሊጋው መቆየት ይችላል። የመጨረሻ ጠርዝ ላይ የሚገኘው ፓዴርቦርን ግን በቡንደስ ሊጋው ለመቆየት ቀጣዩን ጨዋታ የግድ አሸንፎ የሐምቡርግ እና የሽቱትጋርትን ሽንፈት መናፈቅ ብቻ አይደለም መማፀን ይኖርበታል። በእርግጥ ዕድል ወሳኝ ሚና ብትጫወትም ናፍቆት እና ተማፅኖ ብቻ ግን ዋጋ የለውም። ሽቱትጋርት እና ሐምቡርግ ላይሸነፉ ይችሉ ይኾናል። ያኔ ፓዴርቦርን ከቡንደስሊጋው የመሰናበትን መራራ ጽዋ ባይወድም በግድ ከመጎንጨት ውጪ አማራጭ የለውም።

ፍራይቡርግ ከወራጅ ቃጣናው ለመውጣት ባደረገው የሞት ሽረት ፍልሚያ የዘንድሮውን ዋንጫ አስቀድሞ የግሉ ማድረጉን ያረጋገጠውን ባየር ሙይንሽን ማሸነፍ ችሏል። በዚህም መሠረት በደረጃ ሠንጠረዡ 14ኛነት ተቆናጧል።

ፍራይቡርግ መደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ኹለት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ጆከር ፔተርሰን ከመረብ ባሳረፋት ኳስ 2 ለ1 ማሸነፍ ችሏል። ባየርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት በፍራይቡርግ ሽንፈትን የቀመሰው ከሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ የደርሶ መልስ አጠቃላይ ውጤት በባርሴሎና ከተሰናበተ ገና በአራተኛ ቀኑ ነበር።

ሐኖቨር ከአውስቡርግ ጋር ባደረገው ወሳኝ ፍልሚያ 2 ለ1 አሸንፎ 15ኛ ደረጃውን አረጋግጧል። ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርቶ የተለያየው ሔርታ ቤርሊን 13ኛ ደረጃ ላይ በመስፈር ከቡንደስ ሊጋው ከመሰናበት ስጋት ድኗል።

በደረጃ ሠንጠረዡ ቁንጮ ላይ ከሚገኙት ቡድኖች መካከል ደግሞ፦ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ቬርደር ብሬመንን 2 ለባዶ ድል በመንሳት ሦስተኛ ደረጃውን አረጋግጧል። ያም ብቻ አይደለም፤ ከሥሩ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሌቨርኩሰን ሆፈንሐይምን 2 ለ ምንም ማሸነፍ ቢሳካለትም፤ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ለሚቀጥለው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ በቀጥታ አላፊ መሆኑን አረጋግጧል።

በደረጃ ሠንጠረዡ 68 ነጥብ ይዞ፣ በሁለተኛነት የሚገኘው ቮልስፍስቡርግ ቦሩስያ ዶርትሙንድን 2 ለ1 አሸንፏል። ከመሪው ባየር ሙይንሽን ጋር ያለውን ነጥብም ወደ ስምንት አጥብቧል። በእርግጥ ባየር ሙይንሽን የዋንጫው ባለቤት መኾኑን አስቀድሞ ካረጋገጠ ሰነባብቷል። ኮሎኝ በማይትስ 2 ለ1 ሽንፈትን ቀምሷል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ቸልሲ በደረጃ ሠንጠረዡ 13ኛ ላይ ከሚገኘው ዌስት ብሮሚች አልቢኖ ጋር ዛሬ ከጥቂት ሠዓታት በኋላ ይገናኛል። ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አርሰናል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ባከናወኑት ፍልሚያ አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርተዋል። አርሰናል አንድ ተስተካካይ ጫዋታ ይቀረዋል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አንድሬ ሔሬራ ከአሽሌ ያንግ የተላከለትን ኳስ ከመረብ ለማሳረፍ የተሳካለት በ30ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ማለትም በ82ኛው ደቂቃ ላይ የማንቸስተር ዩናይትዱ ቴይለር ብላኬት አርሰናልን ከሽንፈት የታደገችውን ግብ በገዛ መረቡ ላይ አስቆጥሯል። ግቧ የተቆጠረችው ቲዮ ዋልኮት ያሻማት ኳስ አቅጣጫ በመቀየሯ ነበር።

በማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ ኦልትራፎርድ የትናንቱን ጨዋታ ለመከታተል ከ75 ሺህ በላይ ታዳሚ መገኘቱም ተዘግቧል።
ዛሬ አንድ ተስተካካይ ጨዋታውን ከሚያከናውነው ከመሪው ቸልሲ በስምንት ነጥብ ዝቅ ብሎ በኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ስምንተኛ ደረጃን የሙጥኝ ያለው ስዋንሲ ሲቲን ትናንት 4 ለ2 በሆነ አስተማማኝ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል። ስዋንሲ ሲቲ ቀደም ሲል በማንቸስተር ሲቲ 2 ለ1 መሸነፉ ይታወቃል።

ሊቨርፑል በክሪስታል ፓላስ 3 ለ1 ሽንፈት ቀምሷል። በደረጃ ሠንጠረዡ 5ኛ ነው። የመጨረሻውን ግጥሚያ የፊታችን እሁድ ከስቶክ ሲቲ ጋር የሚያከናውነው ሊቨርፑል ቢያሸንፍ እና በደረጃ ሠንጠረዡ ከበላዩ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በሑል ሲቲ ቢሸነፍ እንኳ ሊቨርፑል ባለበት አምስተኛ ደረጃ ላይ ለመፅናት መገደዱ አይቀርም። ምክንያቱም ሊቨርፑል አኹን ያለው 62 ነጥብ ሲሆን፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ግን 69 ነጥብ ላይ ደርሷል።

ሊቨርፑል ከቸልሲ ጋር ሲጫወት
ሊቨርፑል ከቸልሲ ጋር ሲጫወትምስል Getty Images
የማንቸስተር ዩናይትዱ አሽሌ ያንግ
የማንቸስተር ዩናይትዱ አሽሌ ያንግምስል dapd
የጀርመኑ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ቡድን ተጫዋች
የጀርመኑ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ቡድን ተጫዋችምስል picture-alliance/dpa/R. Weihrauch
ሻልከ ከፓዴርቦርን ጋር ሲፋለም
ሻልከ ከፓዴርቦርን ጋር ሲፋለምምስል Getty Images/Lars Baron/Bongarts
USA Eugene Oregon Symbolbild Leichtathletik WM 2021
ምስል J. Ferrey/Getty Images

ማንቸስተር ዩናይትድ ግን ቢሸነፍም አራተኛ ደረጃውን የሚነጥቀው የለም። ምክንያቱም 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሐም ሆትስፐር አኹን ባለው 61 ነጥብ ላይ ኤቨርተንን አሸንፎ 3 ነጥብ ቢደምር ከማንቸስተር ዩናይትድ በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ ማጠናቀቁ አይቀርም።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ በ25 ከመብ ያረፉ ኳሶች ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል። የቶትንሐም ሆትስፐሩ ሐሪ ኬን በሠርጂዮ በአምስት ግቦች ይበለጣል። እስካሁን 20 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ተመዝግበውለታል። የመሪው ቸልሲ ዲዬጎ ኮስታ 19 ግቦች አሉት።

በስፔን ላሊጋ የዋንጫ ባለድሉ ባርሴሎና 93 ነጥብ አለው። ሪያል ማድሪድ በ89 ይከተላል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ77 ይሰልሳል። የፊታችን ቅዳሜ ሪያል ማድሪድ ለመጨረሻው ፍልሚያ ከጌታፌ ጋር ይገናኛል። አትሌቲኮ ማድሪድ ከግራናዳ ጋር ይጋጠማል ባርሴሎና ዲፖርቲቮ ላ ኮሩናን ለደንቡ ያህል ያስተናግዳል።

የጣሊያን ሴሪኣም ሊጠናቀቅ አንድ ዙር ግጥሚያ ብቻ ይቀረዋል። ጁቬንቱስ በ83 ነጥቡ የዋንጫ ባለቤት መኾኑ ቀድሞ ታውቋል። ሮማ 67 ነጥብ አለው። ላትሲዮ ሮም በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ነው።

የሜዳ ቴኒስ

ከጁቬንቱስ ወሳኝ ተጨዋችች አንዱ አንድሬ ፒርሎ
ከጁቬንቱስ ወሳኝ ተጨዋችች አንዱ አንድሬ ፒርሎምስል Reuters/Juan Medina

የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች የዘመናት ተቀናቃኙ ስዊትዘርላንዳዊው ሮጀር ፌዴሬርን ትናንት ሮም ከተማ ውስጥ በማሸነፍ የበላይነቱን አስጠብቋል። የኖቫክ ጆኮቪች የትናንትናው ድል ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ካስመዘገባቸው ድሎች 5ኛው መኾኑ ተገልጧል።

ኖቫክ ጆኮቪች ከሮጀር ፌዴሬር ጋር እሁድ ዕለት ያከናወነው ግጥሚያ ለ39ኛ ጊዜያት መኾኑ ነው። ከትናንትናው ድል በፊትም ሕንድ ውስጥ ከኹለት ወራት በፊት በተከናወነው የዌልስ ፍፃሜ ኖቫክ ጆኮቪች እና ሮጀር ፌዴሬር ተገናኝተው ድል የቀናው ለኖቫክ ነበር።

ፈረንሣይ የሚከናወነው የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ሊጀምር አንድ ሣምንት ብቻ በቀረበት በዚህ የውድድር ዘመን፤ ኖቫክ ጆኮቪች የአውስትራሊያ፣ የሕንድ ዌልስ፣ የሚያሚ እና የሞንት ካርሎ ድሎች ተደማምረው ለ22 ጊዜያት በተከታታይ ሳይሸነፍ ድል የተቀዳጀ ጠንካራ ስፖርተኛ መሆኑን አስመስክሯል።

አጫጭር ዜናዎች

የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች
የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪችምስል picture-alliance/dpa

የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል ወደ ሪያል ማድሪድ ሊያቀና የጠበቀ ግንኙነት ፈጥሯል የተባለለትን ግብ ጠባቂያቸው ዴቪድ ዴ ጊያን በቡድናቸው ለማቆየት እየታገሉ መሆናቸውን ትናንት ገልጠዋል።

አርሰናል ከፍተኛ ተስፋ የጣለችበት የአማካይ ተጫዋች ጌዲዮን ዘላለም ለዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰልፎ ለመጫወት መወሰኑ ሰሞኑን ይፋ ኾኗል። ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ከሆኑ ቤተሰቦቹ ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ የተወለደው የ18 ዓመቱ ጌዲዮን ዘላለም ቀደም ሲል ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኾኑ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የእግር ኳስ ግጥሚያ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን መሰለፉ ይታወቃል።

ለሊቨርፑል 17 ዓመታት ተሰልፎ የተጫወተው አምበሉ ሽቴፋን ጄራርድ ትናንት ከክሪስታል ፓላሱ ሽንፈት በኋላ ለቡድኑ ተሰልፎ ከእንግዲህ እንደማይጫወት በሐዘን ተውጦ ገልጧል። የ34 ዓመቱ እንግሊዛዊ አምበል ሽቴፋን ጄራርድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንቶ ለሎስ አንጀለስ ጋላክሲ ቡድን ይሰለፋል ተብሏል። ሽቴፋን ጄራርድ ለሊቨርፑል ከእንግዲህ እንደማይጫወት ባሳወቀበት ወቅት የደጋፊዎቹ ስሜት ልብ የሚነካ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ