1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሚያዝያ 26 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2007

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ቸልሲ በ83 ነጥቡ ከወዲሁ የዋንጫው ባለቤት መሆኑ ታውቋል። የስፔኑ ባርሴሎና ኮርዶባን 8 ለምንም ጉድ አድርጎታል። ሜሲ እና ሮናልዶ ለኮከብ ግብ አግቢነት የድል ካባ አንገት ለአንገት ተያይዘዋል። ለአሸነፈም ለተሸነፈም ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተከፈለበት የቡጢ ፍልሚያ በላስ ቬጋስ ተከናውኗል።

https://p.dw.com/p/1FK2B
Floyd Mayweather Jr. celebrates the unanimous decision victory during the welterweight unification championship bout
ምስል Getty Images

ለተሸናፊው ቡጢኛ ብቻ የተከፈለው ዶላር ኢትዮጵያ ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያስገነባው ያቀደው አይነት 6ዘመናዊ ስታዲዬሞችን ማስገንባት ይችላል።

ቸልሲን የሚያቆመው አልተገኘም። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሣምንታት ብቻ ይቀራሉ። ትናንት ግን ቸልሲ በኤደን ሐዛርድ ብቸኛ ግብ ክሪስታል ፓላስን ድል ነስቶ የዋንጫው ባለቤትነቱን ከወዲሁ አስከብሯል። ከ41 ሺህ በላይ ታዳሚያን በተገኙበት የስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ሠማያዊ ለባሾቹ በጣምራ ድል ሲፈንጥዙ አምሽተዋል። ቸልሲ በሰበሰበው 83 ነጥብ ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲን በሰፊ ልዩነት ርቋል።

England Chelsea Meister Jubel
ምስል Reuters/Sibley Livepic

የለንደኑ ቸልሲ ትናንት የዋንጫው ባለቤት መሆኑን ሲያረጋግጥ በፕሬሚየር ሊጉ ታሪክ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ቸልሲ ከዚህ ቀደም እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ1955፣2005፣ 2006 እና2010 የፕሬሚየር ሊጉ አሸናፊ ለመሆን ችሎ ነበር። ለአሠልጣኙ ጆሴ ሞሪንሆ ደግሞ በ13 ዓመታት ውስጥ በስምንት የሊጋ ግጥሚያዎች ዋንጫ ያስገኙበት ተጨማሪ የስኬት ዘመን ሆኖ ተመዝግቧል።

ጆሴ ሞሪንሆ እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2004 እና 2007 መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የቸልሲ አሠልጣኝ በነበሩበት ዘመን ለኹለት ጊዜ ለቡድናቸው ዋንጫ ማስገኘት የቻሉ ጠንካራ አሠልጣኝ ናቸው። «ጠንክረህ ከሠራህ እና ድል ከተጎናፀፍክ ይገባኛል የሚል ስሜት ያድርብሀል። ይህ ስሜት ደግሞ እጅግ የተለየ ስሜት ነው።» በማለት ባገኙት ድል ሲበዛመደሰታቸውን በኩራት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ገልጠዋል።

England Chelsea Meister Jubel
ምስል picture-alliance/empics/Potts

ለ34 ዓመቱ ጎልማሳ ጆን ቴሪ ደግሞ ከቸልሲ ጋር ሆኖ የዋንጫ ባለቤት ሲሆን ለአራተኛ ጊዜው መሆኑ ነው። እናም አለ ጆን ቴሪ፦ «በቃ ልዩ የሆነ የማይታመን ስሜት ነው የሚሰማኝ። የምኖረውም ለዚያ ነው። የዋንጫ ባለቤት ሳንሆን ለአራት አምስት ዓመታት የገፋነው ጊዜ ለእኔ የኅመም ዘምን ነው። ዛሬ ግን ከምንም በላይ ደስታውን እያጣጣምኩት ነው» ሲል እጅግ በደስታ መዋጡን አስታውቋል።

ቶትንሐምን በተመሳሳይ ነጥብ ትናንት አንድ ለባዶ ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ከዋንጫ ባለቤቱ ቸልሲ በ13 ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል። ኹለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት አርሰናል በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዛሬ ከሁል ሲቲ ጋር ይጋጠማል። አርሰናል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነጥብ እኩል ይሆናል። የዛሬ ሣምንት ከስዋንሲቲ ጋር የሚያከናውነውን ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታውንም የሚያሸንፍ ከሆነ ደግሞ 73 ነጥብ ይዞ፣ በሦስት ነጥብ ልዩነት የኹለተኛነት ደረጃውን ከማንቸስተር ሲቲ ይረከባል ማለት ነው።

Champions League Schalke vs Real Madrid
ምስል P. Stollarz/AFP/Getty Images

በደረጃ ሠንጠረዡ አራተኛ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ 65 ነጥብ አለው። ሊቨርፑል በ4 ነጥብ ዝቅ ብሎ በአጠቃላይ 61 ነጥቡ 5ኛ ደረጃን ተቆናጧል። የፊታችን ቅዳሜ ከክሪስታል ፓላስ ጋር የሚገጥመው ማንቸስተር ዩናይትድ በበነጋታው እሁድ ከቸልሲ ጋር ከሚፋለመው ሊቨርፑል የተሻለ የማሸነፍ እድል አለው።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ ደግሞ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በባየር ሌቨርኩሰን 2 ለምንም ሽንፈት ቀምሷል። ሆኖም መሪው ባየር ሙይንሽን በ76 ነጥቡ አስቀድሞ የዋንጫ ባለቤት መሆኑን ማረጋገጡ ይታወቃል። ከነገ በስትያ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ከስፔኑ ባርሴሎና ጋር ይገናኛል። ነገ የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ከሌላኛው የስፔን ኃያል ሪያል ማድሪድ ጋር የሚያከናውኑት ግጥሚያ በእግር ኳስ ጨዋታ አድናቂዎች ዘንድ እጅግ በጉጉት ይጠበቃል። ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ነው የሚፋለሙት። የነገ እና የከነገ ወዲያ አሸናፊዎች ግንቦት 29 ቀን፣ 2007 ዓም ለፍፃሜ ጀርመን በርሊን ከተማ ይገናኛሉ። አሸናፊው በእለቱ ግዙፉን ዋንቻ ያነሳል። 73.5ሴንቲ ሜትር ይረዝማል፣ 8.5 ኪሎ ግራም ይመዝናል፤ ዋንጫው።

ዝነኛውን ግብ ጠባቂ ቡፎን እንዲሁም ቴቬዝ፣ ኤቭራ እና ቪዳልን የመሳሰሉ ድንቅ ተጨዋቾችን ያሰባሰበው ጁቬንቱስ በጣሊያን ሴሪያ ኣ ከወዲሁ የዋንጫው ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል። የነገውን ጨዋታ የሚያከናውነው ቱሪን ውስጥ በሜዳው ጁቬንቱስ አሬና እና በደጋፊው ፊት ነው። ሆኖም እንግዳው ሪያል ማድሪድ እነ ሮናልዶ እና ቤልን ከፊት አስቀድሞ፣ በእነ ማርሴሎ እየታገዘ እነ ፔፔን የብረት አጥር አድርጎ የሚገባ በመሆኑ ለጁቬንቱስ ፈተና መሆኑ አይቀርም።

Champions League Barcelona vs Manchester City Messi
ምስል Getty Images/M.Regan

ቮልፍስቡርግ ከባየር ሙይንሽን በ14 ነጥብ ልዩነት 62 ነጥብ ይዞ በኹለተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛል። ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ 60 ነጥብ አለው ደረጃው ሦስተኛ ነው። ባየር ሌቨርኩሰን ከትናንት በስትያ ባየር ሙይንሽንን ድል ነስቶ ያገኘው ሦስት ነጥብ ተደምሮለት በአጠቃላይ 58 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ከሆፈንሐይም ጋር አንድ እኩል አቻ ተለያይቷል፤ አኹንም 9ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። 40 ነጥብ አለው።

ሐኖቨር እና ሽቱትጋርት በ30 እና 27 ነጥብ ወራጅ ቃጣናው ላይ ነው የሚገኙት። ፍራይቡርግን ከትናንት በስትያ 2 ለ1 ማሸነፍ የቻለው ፓዳርቦርን በ31 ነጥቡ ፍራይቡርግን ወደ ወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ገፍትሮ ለጊዜውም ቢሆን ከስጋት ድኗል። ፍራይቡርግ በ30 ነጥብ ወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ላይ በስጋት ተውጦ ይገኛል። እስከ ውድድር ዘመኑ በዚሁ ከቀጠለ በቡንደስ ሊጋው ለመቆየት በኹለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሆኖ ካጠናቀቀ ቡድን ጋር ተጋጥሞ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

በስፔን ላሊጋ ቅዳሜ ዕለት ኮርዶባን 8 ለምንም ያንኮታኮተው ባርሴሎና በ87 ነጥብ ላሊጋውን እየመራ ይገኛል። ሪያል ማድሪድ 85 ነጥብ አለው በኹለተኛነት ይከተላል። 76 ነጥብ ያለው አትሌቲኮ ማድሪድ ሦስተኛ ነው። 20 ነጥብ ብቻ ማግኘት የቻለውግራናዳ ወራጅ ቃጣናው ግርጌ ላይ ይገኛል።

Bildergalerie berühmte Sportler und ihre Kinder
ምስል picture alliance/AP Photo

የባርሴሎናው ሱዋሬዝ በ45ኛው፣ 53ኛውእና 88ኛው ደቂቃ ላይ በተከታታይ ሦስት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትሪክ ሰርቷል። አርጀንቲናዊው የኳስ ጥበበኛ ሊዮኔል ሜሲ በ46ኛው እና በ80ኛው ደቂቃዎች ላይ ኹለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በላሊጋው 40 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሚበለጠው በ2 ግቦች ብቻ ነው። ሊዮኔል ሜሲ ከትናንት በስትያ በተደረገው ጨዋታ በ85ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ለኔይማር አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ራሱ ቢመታት ኖሮ ምናልባትም ከሮናልዶ ጋር ያለው የግብ ልዩነት በአንድ ሊወሰን ይችል ነበር። ቀሪዎቹን ግቦች ኔይማር በ85ኛው ደቂቃ እንዲሁም ራክቲክ በ42ኛው እንዲኹም ፒኬ በ65ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል።

ከሴቪያ ጋር ከትናንት በስትያ የተገናኘው ሪያል ማድሪድ በክርስቲያኖ ሮናልዶ ሦስት ግቦች አሸናፊ ለመሆን ችሏል። በባካ እና ኢቦራ 45ኛው እና በ79ኛው ደቂቃ ላይ ኹለት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ሴቪያ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ነበር የገባው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው የተገኘው ዕድል ባይመክን ኖሮ ሪያል ማድሪድ ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ግድ ይሆንበት ነበር። ግብ አዳኙ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቅዳሜ ዕለት ባስቆጠረው ሐትሪክ በፕሬሚየር ሊጉ 42 ግቦች አሉት።ከሊዮኔል ሜሲ በ2 በልጦ ይገኛል። ባርሴሎና በሰባት ዓመት ውስጥ በላሊጋው ለአምስተኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን መንገዱን እየጠረገ ነው።

Public Viewing beim Boxampf Mayweather vs. Pacquiao auf den Philippinen
ምስል DW/R.-I. Duerr

ቡጢ

በዓለም የቡጢ ፍልሚያ ውድድር ታሪክ ለተፋላሚዎች እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ፉክክር በዩናይትድ ስቴትስ ላስቬጋስ የተከናወነው በሣምንቱ ማሳረጊያ ላይ ነበር። በቡጢ ፍልሚያ ውድድሩ 400 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ፍሎይድ ሜይዌዘር ለውድድሩ ከ140 እስከ 180 ሚሊዮን ዶላር ሳይከፈለው አልቀረም ተብሏል። የፊሊፒኑተፋላሚ ማኒ ፓኪያው ምንም እንኳን በዳኛ ውሳኔ የተሸነፈ ቢሆንም፤ በበኩሉ ከ100 እስከ 120 ሚሊዮን ዶላር በእጁ እንዳስገባ ተዘግቧል።

ፍሎይድ ሜይዌዘር ከማኒ ፓኪያው የተሰነዘሩበትን ቡጢዎች ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ በመሸሽ ነጥብ በማስቆጠሩ ለ48ኛ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን ችሏል። ፍሎይድ ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፦ «ብዙ ቡጢ አላረፈብኝም፤ በብልጠት ነው የተጋጠምኩት» ብሏል። በርካታ ተመልካቾች ማሸነፍ የነበረበት ፓኪያው ነበር ቢሉም፤ ሦስቱም ዳኞች 118:110፣ 116:112 እና116:112በሆነ ልዩነት ነጥብ በመስጠታቸው ሜይዌዘር አሸናፊ ሊሆን ችሏል።

ተሸናፊው ማኒ ፓኪያው በበኩሉ፦ «ጥሩ ፍልሚያ ነበር። በተደጋጋሚ በቡጢ ስላገኘሁት እንዳሸነፍኩ ነው የምቆጥረው። ከዚያ የባሰ ቡጢ እንዳላሳርፍበት አንድም ጊዜ ሳይቆም በደንብ ወዲህ እና ወዲያ ሲንቀሳቀስ ነበር።» ሲል ማሸነፍ የነበረበት እሱ ራሱ እንደነሆነ ጠቅሷል።

Manny Pacquiao lands a punch against Floyd Mayweather
ምስል Reuters

በላስቬጋሱ የቡጢ ፍልሚያ ተሸናፊ የሆነው የፊሊፒኑተፋላሚ ማኒ ፓኪያው በእጁ አስገባ የተባለው ከ100 እስከ 120 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ሊያስገነባ ያቀደው አይነት ቢያንስ 6ዘመናዊ ስታዲዬሞችን ማስገንባት የሚችል ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያስገነባው ነው የተባለለት ስታዲየም 18 ሚሊዮን ዶላር ግድም እንደሚያወጣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በድረገፁ አስፍሮት ይገኛል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን « አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ሰኞ ሚያዝያ 26/ 2007» ሥራ እንደሚጀምሩ በኢሜል መልእክቱ ይፋ አድርጓል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማጫወቻ ይቻኑ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ