1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ብዛት በአውሮጳ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 19 2007

በሳምንቱ ማብቂያ ላይ እና ሰኞ ነሐሴ 18 ቀን፣2007 ዓ.ም.አውሮጳውያን በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከባሕር ሲታደጉ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ መከራ እያዩ ነው። ከተለያዩ የምሥራቅ አውሮጳ ሃገራት ወደ ጀርመን እና ሰሜን አውሮጳ በመትመም ላይ ናቸው። ስደተኞቹ ከባሕር እና ሌሎች አደጋዎች ቢተርፉ የቀኝ አክራሪዎች ተቃውሞ እና ጥቃት ይጠብቃቸዋል።

https://p.dw.com/p/1GLQV
Frankreich Flüchtlinge Eurotunnel Calais
ምስል Getty Images/AFP/P. Huguen

[No title]

በዓለማችን 59 ሚሊዮን ሰዎች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል። «ቢልድ» (Bild) የተሰኘው በጀርመንኛ የሚታተም ጋዜጣ ይኽ ፍልሰት ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛው ነው ሲል አስነብቧል። ብዙዎቹ ፈላሲያን ጎናቸውን የሚያሳርፉበት መጠለያ፣ ንብረት፣ ሥራ እና ቤተሰብ ነበራቸው፤ በሀገራቸው። ዛሬ ግን ተገን ጥየቃ ለመፍለስ ተገደዋል። የብዙዎቹ ሀገር በበለፀገው ዓለም ረቂቅ እና ዘመናዊ ጦር መሣሪያዎች እንደማይሆን የሆነ ነው። የስደተኞቹን ሰቆቃ የበለጠ የሚያከፋው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በምዕራቡ ዓለም የፈረሱ ቀዬዎቻቸውን ጣጥለው ወደ በለፀገው ዓለም ሰላም እና ተገን ፍለጋ ሲያቀኑ የሚጠብቃቸው ሌላ መከራ እና ጥላቻ መሆኑ ነው። የሜድትራኒያን ባሕር አቋርጠው የሚመጡ አፍሪቃውያንን የሚታደግ ግብረ-ሠናይ ድርጅት በመመስረት ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት አንስቶ ርዳታ በማድረግ ላይ ያሉት

ሰሞኑን ይኽ ምስቅልቅል እጅግ ተባብሷል። የቀድሞ ዩጎዝላቪያ አካል ወደነበረችው እና ግሪክን ወደምትጎራበተው ሜቄዶኒያ የሚተመው ስደተኛ ቁጥር ጨምሯል። በተለይ የግሪክ ድንበር ላይ የምትገኘው ጌቭጌሊያ በሺህዎች በሚቆጠሩ ስደተኞች ተጨናንቃለች። አብዛኞቹ ስደተኞች ከሶሪያ ጦርነት ሸሽተው ግሪክ የገቡ ናቸው ተብሏል። ባለፈው ሐምሌ ብቻ በጎረቤት ግሪክ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ 50.00 ሰዎች እንደነበሩ ተመዝግቧል። ይኽ ቁጥር ካለፈው የጎርጎሪዮስ ዓመት አንፃር ከፍተኛው ነው ተብሏል።

ስደተኛ አባት ከልጁ ጋር ድንበር ለመሻገር ሲያቀና
ስደተኛ አባት ከልጁ ጋር ድንበር ለመሻገር ሲያቀናምስል Reuters/L. Balogh

በሺህዎች የሚቆጠሩት ስደተኞች ከተቻለ በተሽከርካሪ ካልተቻለም በእግር በሜቄዶኒያ አሳብረው ወደ ሰሜን አውሮጳ ማቅናት ነው የሚፈልጉት። መጀመሪያ አካባቢ የሜቄዶኒያ የድንበር ጠባቂ ፖሊስ በአስለቃሽ ጢስ እና ከፍተኛ ድምጽ በሚፈጥሩ ፍንዳታዎች ስደተኞቹን ወደ መጡበት ወደ ግሪክ ለመመለስ ሙከራ አድርጎ ነበር። በወቅቱ የተወሰኑ ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል። ቆየት ብሎ የሜቄዶኒያ መንግሥት ስደተኞቹ ድንበሩን እያቋረጡ እንዲያልፉ ፈቅዷል። ኹኔታው ምስቅልቅል የተሞላበት ከመሆኑም ባሻገር አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ብቻ 7 ሺህ ስደተኞች ከሜቄዶኒያ ወደ ሠርቢያ መግባታቸውን በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) ይፋ አድርጓል። ሜቄዶኒያ ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ ማንኛውም ስደተኛ ሀገሯ ውስጥ ለ72 ሰአታት መንቀሳቀስ እንዲችል የመጓጓዣ አገልግሎትም በነፃ እንዲያገኝ የሚያስችል ሕግ ደንግጋለች። ሰሞኑን በርካታ አውቶቡሶች በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ሜቄዶኒያ ውስጥ ሲያመላልሱ ታይተዋል።

ጀርመን በዛክሰን ግዛት፣ ሃይደናው ውስጥ ደግሞ ካለፈው ዓርብ አንስቶ ለኹለት ተከታታይ ምሽቶች የስደተኞቹን መምጣት አጥብቀው የሚቃዋሙ ቀኝ አክራሪዎች ብጥብጥ አስነስተዋል። በእነዚህ ቀኝ አክራሪዎች እና የግራ አመለካከት ባላቸው ሰልፈኞች መካከል የአደባባይ ግጭት ተቀስቅሶ ውጥረት ነግሷል። ከዓርብ እለት ጀምሮ በቀኝ አክራሪዎች በደረሰ ጥቃት ከ30 በላይ ፖሊሶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። የዛክሰን ግዛት የስደተኞች ጉዳይ ተጠሪ ጊርት ማኬንሮስ ጥቃት አድራሾቹ ላይ ፈጣን እና ጠንካራ ቅጣት እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል። የጀርመን ምክትል መራሔ-መንግሥት ሲግማር ጋብሪዬል በበኩላቸው ተገን ጠያቂዎች ስጋት ሳይሆኑ እንደውም ለጀርመን የሚጠቅሙ መሆናቸውን አሳስበዋል።

ጀርመናዊው ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዲህ ይበሉ እንጂ «ተገን ጠያቂዎች በመኖሪያ አካባቢያችን አይድረሱብን» የሚለው ተቃውሞ በሌሎች ከተሞችም ቀጥሏል። በበርሊን ከተማ ተገን ጠያቂዎች እንዲያርፉበት የተሰናዳ የስፖርት አዳራሽ በእሳት ተለኩሶ ትናንት ሌሊት መቀጣጠሉ ተዘግቧል። ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። የጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአውሮጳ አባል ሃገራት ስደተኞችን ፍትኃዊ በሆነ መንገድ ተከፋፍለው በየሀገራቸው እንዲያኖሩ ዛሬ በድጋሚ ተማጽነዋል።

የጀርመን ምክትል መራሔ-መንግሥት ሲግማር ጋብሪዬል ሃይደናው ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ
የጀርመን ምክትል መራሔ-መንግሥት ሲግማር ጋብሪዬል ሃይደናው ውስጥ ጉብኝት እያደረጉምስል Reuters/Bundesministerium für Wirtschaft und Energie/M. Weiss

«ደር ሽፒግል» (Der Spiegel) እንደተሰኘው በጀርመንኛ የሚታተም መጽሔት ከሆነ በዓለማችን ጦርነት ካመሳቀላት ሶሪያ ብቻ 4 ሚሊዮን ሰዎች ተሰደዋል። ከነዚህ አራት ሚሊዮን ስደተኞች ዩናይትድ ስቴትስ 10ሺህውን እቀበላለሁ ብላለች።
ለመሆኑ አውሮጳ ውስጥ ይኽ የስደተኞች መትመም በድንገት ቁጥሩ ለምን ከፍ አለ? በርካቶች የተለያዩ ትንታኔዎችን አስነብበዋል። በሶሪያ እና በኢራቅ የአሳድ ታማኝ ወታደሮች በደል፤ ራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራው ቡድን ከሚያደርሰው መከራ ጋር ተደምሮ ነዋሪዎች ሃገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷል። በአፍጋኒስታንም ታሊባን ለነዋሪዎች ሌላኛው ስጋት መሆኑ አላከተመም። ሶማሊያ ለዓመታት ከተዘፈቀችበት የእርስ በእርስ ጦርነት ብትወጣም ሽምቅ ውጊያ ውስጥ የገባው አክራሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን የበርካታ ሶማሌዎችን ሕይወት እያመሳቀለ ነው። ኤርትራ ውስጥ ሕዝቡን እንደፈለገ የሚያደርግ ፕሬዚዳንት መግዛቱ ለስደቱ መባባስ ምክንያት ነው ሲሉ ተንታኞች አስነብበዋል።

ፈረንሳይ ካሌ ውስጥ የቆመው የድንበር አጥር
ፈረንሳይ ካሌ ውስጥ የቆመው የድንበር አጥርምስል DW/B. Riegert

በሌሎች ሃገራት ደግሞ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ አምባገነንነት፣ ጎጠኝነት፣ የሃይማኖት ጽንፈኝነት ብሎም ድህነት በተለይ ከሰሐራ በታች ላሉ ሃገራት ነዋሪዎች የስደት ሰበብ ተደርጎ ይወሰዳል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በምሥራቅ አውሮጳ የመትመማቸውን ያኽል በጣሊያን በኩልም በባሕር አደገኛ ጉዞ የሚያደርጉ አፍሪቃውያን ቁጥር እየጨመረ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ሰብአዊ መብቶች ተመልካች ልዩ መልእክተኛ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ባለሥልጣናት በተገኙበት አውሮጳን በስደተኛ እና ፈላሲያን አያያዝ ተችተዋል። የአውሮጳ ኅብረት ፈላሲያንን በተመለከተ ያልተሳካ ፖሊሲ ነው የሚከተለው ብለዋል። ልዩ መልእክተኛው ፍራንሷ ክሬፒዩ ዛሬ ከስዊዘርላንድ ጄኔቫ «የአውሮጳ ኅብረት እና አባል ሃገራቱ ድርጅቶች በእርግጥም ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ አድርገን አናስመስል።» ሲሉ የሰላ ትችት አቅርበዋል። «አጥር ማቆም፣ አስለቃሽ ጢስ መልቀቅ እና ሌሎች በደሎችን ፈላሲያን እና ተገን ጠያቂዎች ላይ መፈጸም፣ ዘብጥያ ማውረድ ፣ መጠለያ አልባ ማድረግ፣ የምግብ፣ ውኃ እና መድሐኒት መንፈግ ፣ የጥላቻ ቅስቀሳዎችን ማድረግ ፈላሲያን ወደ አውሮጳ ከመምጣት አለያም ያን ከመሞከር አያግዳቸውም። » በማለት የችግሩን አሳሳቢነት አጉልተዋል።

ጀርመን ዉስጥ ጥገኝነት እንዲሰጠዉ የሚጠይቀዉ ስደተኛ ቁጥር አለቅጥ ማሻቀቡን የሐገሪቱ መንግሥት ሰሞኑን አስታውቋል። የጎሮጎሪዮስ 2015 በመጪዉ ታኅሳስ እስከሚገባደድ ድረስ ወደ ጀርመን የሚገባዉ ስደተኛ ስደተኛ ቁጥር ከ750 ሺሕ ይበልጣል ተብሎ ይገመታል።

ከየሀገራቸው በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ወደ አውሮጳ የሚፈልሱ ስደተኞች ከባሕር ዓሣ፣ ከጨካኞች ካራ አለያም የጦርነት እሳት ተርፈው አውሮጳ ቢደርሱም እንኳን የሚጠብቃቸው ሌላ መከራ ነው። ብዙዎቹ ስደተኞች ከፈረንሣይ ካሌ በዋሻ መሸጋገሪያ በባቡሮች አለያም በከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ተንጠልጥለው ወደ ብሪታንያ ለመግባት ሲሞክሩ በተደጋጋሚ ለሞት ተዳርገዋል። ብሪታንያ ደግሞ ወደ ሃገሯ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ስደተኞችን ወደፊት የሥራ እና የመኖሪያ ፈቃድ እንደማትሰጥ፤ ስደተኞቹ ቤት መከራየት እንደማይችሉም አስጠንቅቃለች።

ዛክሰን ውስጥ ቀኝ አክራሪዎች የፈጠሩት ግችት
ዛክሰን ውስጥ ቀኝ አክራሪዎች የፈጠሩት ግችትምስል picture-alliance/dpa/A. Burgi

ጀርመን ያሉ የቀኝ አክራሪዎች «የትኛውም ስደተኛ አይድረስብን» በማለት ከረር ያሉ የጥላቻ ቅስቀሳዎችን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ማስተላለፋቸውን የሀገሪቱ መገናኛ አውታሮች ዘግበዋል።

ሆኖም አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱ ጦርነት፣ የአምባገነኖች ጭካኔ፣ የሞት ጥላ፣ የፈራረሱ መንደሮች፣ የወደሙ መሠረተ አውታሮች ነው የሚጠብቋቸው። በአውሮጳ ፈላሲያን የቀን ተቀን ሕይወታቸውን ተስፋ ቢስ በሆነ መልኩ ለመግፋት ተገደዋል። እንዳይመለሱም እንዳይቆዩም ሆነው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ