1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች መርጃ ደንብ 60ኛ ዓመት፦ምራብና ምሥራቅ አፍሪቃ

ዓርብ፣ ሐምሌ 22 2003

በሌላዉ የአፍሪቃ ጠርዝ-ምሥራቅ አፍሪቃ አንፃራዊ ሠላም የሠፈነባት ኬንያ የደቡብ ሱዳን፥ የኢትዮጵያ፥ የሶማሊያ ስደተኞች መጠለያ እንደሆነች ዓመታት አስቆጥራለች

https://p.dw.com/p/Rd8z
የኮት ዲቩዋር ስደተኞችምስል Amnesty International

28 07 11

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ደንብ የፀደቀበት ሥልሳኛ ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነዉ።በደንቡ መሠረት የተቋቋመዉ የዓለም የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር UNHCR ስደተኞችን ለመርዳት አበክሮ ቢጥርም ዓለም ዛሬም ከመቼዉም ጊዜ የበለጠ ሕዝብ ተሰደቧታል።በቅርቡ በምሥራቅ አፍሪቃ የተከሰተዉ ድርቅና ረሐብ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ተጨማሪ ሕዝብ እያሰደደ ነዉ።ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ የላይቤሪያና የኮትዲቫር ጦርነት ቢቆምም ጦርነቱን ሽሽት ወደ ጋና የተሰደዱት የሁለቱ ሐገራት ዜጎች ወደየሐገራቸዉ አልተመለሱም።ቀጣዩ ዘገባ የስደተኞች ደንብ የፀደቀበትን ስልሳኛ አመትና የአፍሪቃ ስደተኞችን ሁኔታ ባጭሩ ይቃኛል።

የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ከየሐገሩ ያሰደደዉን ሕዝብ እንዲረዳ የተሠየመዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢሮ ባዲስ ስምና መልክ የተቋቋመዉ በ1951 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነበር።ብዙ ሚሊዮን ስደተኞችን ረድቷል።ላከናወነዉ ምግባር በጎነት መግለጫም የዓለም ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤልን ሁለቴ ተሸልሟል።1994 እና 1981።

ብዙ የሠራ፥ ብዙ የተመሠገነዉ፥ ታላቅ ሽልማት የተሸለመዉ ታላቅ ድርጅት ሕዝብን ከመሰደድ፥ ለማዳን፥ የተሰደደዉን፥ ከችግር ለመከላከል፥ ወይም ወደ ሐገሩ ለመለስ ብዙም አለመተከሩ ነዉ ግራ-አጋቢ ተቃርኖዉ።የላይ ቤሪያዉ የርስ በርስ ጦርነት ከቆመ አስራ አንድ አመቱ ተቆጠረ።የዶቸ ቬለ የሐዉሳ ክፍል ዘገቢ ራሕመቱ አቡበከር መሐመድ እንደዘገበችዉ በ1980ዎቹ ወደ ጋና የተሰደዱ ብዙ ሺሕ ላቤሪያዉያን ዛሬም እዚያዉ ጋና ናቸዉ።

ቡዱምቡራም በተሰኘዉ መጠለያ ጣቢያ የሠፈሩት ስደተኞች ተወካይ ፒተር ሶቢያሕ ስደተኞቹ ወደ ሐገራቸዉ የሚመለሱበት ምክንያት፥ አቅም፣ ፍላጎትም የላቸዉም።

«አንዳዶቹ ሐገራቸዉ ዉስጥ ምንም ዘመድ-አዝማድ የላቸዉም።እና የሚመለሱበት ምክንያት የለም።ሌሎቹ ደግሞ በጦርነቱ ወቅት የደረሰባቸዉን ዘግናኝ ገጠመኝ እያስታወሱ ወደ ሐገራቸዉ መመለስን ይፈራሉ።ከዚሕ በተጨማሪ እዚሕ ገና ዉስጥ የተሸለ የዉሐና የመብራት አገልግሎት አለ።የተወሰኑት ደግሞ የተሻለ የሥራ እድል ያገኛሉ።»

ከ1989 ጀምሮ ካጭር ጊዜ ፋታ በስተቀር እስከ 2003 በቀጠለዉ የርስ በርስ ጦርነት ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አልቋል።አሁን ላይቤሪያ ሠላም ናት።የመሠረተ ልማት አዉታሮቿ፥ ትምሕርት ቤቶቿ፥ ሐኪም ቤቶቿ ተጠግነዋል።የዉሐ አገልግሎቷም ተሻሽሏል።የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ኤለን ጆንሰን ሰርሌፍ የታየዉ ለዉጥ የሚደነቅ ነዉ ባይ ናቸዉ።ለዉጡ ጋና የሰፈሩ ስደተኞችን ግን አልሳበም።

እንዳዶቹ እንዲያዉም እዚያዉ ጋና ወልደዉ ከብደዋል።ከጋና ዉጪ ሌላ ሐገር የማያዉቁ ልጆችም ብዙ ናቸዉ።ፓፒ ሼኩ ቱሬይ አንዱ ነዉ።

«ጋና ዉስጥ በመኖሬ ደስተኛ ነኝ።አንድ ሰዉ በዚሕ ምድር ላይ ሊኮራበት የሚችለዉን ነገር በሙሉ አጥቻለሁ።ወላጆቼን አጥቻለሁ።የቀረኝ ነገር የለም።ሥለዚሕ ጋና የኔም ሐገር ነች ብዬ አምናለሁ።ምክንያቱም እዚሁ ዩኒቨርስቲ እያጠናሁ ነዉ።ለወደፊቱ ጥሩ አለም አቀፍ የሕግ ሰዉ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ።»

የግጭት-ጦርነት በሚያብጠዉ አካባቢ የሠላም፥ የዲሞክራሲና የዕድገት አብነት የሆነችዉ ጋና የላይቤሪያ ስደተኛ ቁጥር ሲቀንስላት ከኮትዲቯ ር ሌላ ስደተኛ ተጨመረላት።ርዕሠ-ከተማ አክራ አጠገብ ብቻ ከአስራ-አንድ ሺሕ በላይ ስደተኞች ሠፍረዋል።

Flash-Galerie Dürre ohne Ende Somalische Flüchtlinge strömen wegen Dürre nach Äthiopien
የሶማሊያ ስደተኞችምስል picture alliance/dpa/WFP/Judith Schuler

በሌላዉ የአፍሪቃ ጠርዝ-ምሥራቅ አፍሪቃ አንፃራዊ ሠላም የሠፈነባት ኬንያ የደቡብ ሱዳን፥ የኢትዮጵያ፥ የሶማሊያ ስደተኞች መጠለያ እንደሆነች ዓመታት አስቆጥራለች። የኢትዮጵያ ዜጎች ወደ ኬንያና የመን በብዛት ሲሰደዱ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰፍረዋል።የሶማሊያና የኤርትራ ዜጎችም ወደ ኢትዮጵያ ይሰደዳሉ።

የሊቢያዉ ጦርነት ሊቢያ ከተጠለሉ የአፍሪቃ ስደተኞች የታደሉትን ለዳግም ስደት፥ የተረገሙትን ለባሕር ሲሳይ መዳረጉ ጉድ አሰኝቶ ሳበቃ፥ ድርቅና ረሐብ ያሰደደዉ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር የሶማሊያ ሕዝብ የኢትዮጵያና የኬንያ መጠለያ ጣቢያዎች ያጥለቀልቅ ገባ።ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት የ60 ዓመት አዛዉንትነቱ ሲረጋገጥ የስደተኛዉም ቁጥር ስልሳ አምስት አሻቅቦ ከአርባ-ሰወስት ሚሊዮን በለጠ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ