1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስዊድን የፍልሰት ጉዳይ ሕጎች እና ተጽእኖአቸው

ሐሙስ፣ ኅዳር 1 2009

በስዊድን ቀደም ሲል የተገን ጠያቂዎቹ ቁጥር በሳምንት ጊዜ ዉስጥ እስከ 9000 ይደርስ የነበረው አሁን ወደ 700 ውርዶአል። በያዝነው ዓመት በአጠቃላይ ወደ ሲዊድን የፈለሱት የተገን ጠያቂዎች ቁጥር ከአምናው ጋር ሲወዳደር ከ 163 000 ወደ 24 000 ማሽቆልቆሉ ታዉቋል።

https://p.dw.com/p/2SWEH
Dänisch-Schwedischer Grenzübergang Kontrolle
ምስል picture-alliance/dpa/A. Ladefoged

Eritrean Immigrant in Sweeden - MP3-Stereo

እጨመረ የመጣዉን የስደተኞች ቁጥር ለመቀነስ ስዊድን  ካለፈው ዓመት ጀምሮ አዳዲስ ሕግጋትን  ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች። ከወጡት ሕጎች መካከል ዋና ዋናዎቹ በድንበር ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግና ለአዳዲስ ስደተኞች ቀድሞ ይሰጥ የነበረው ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አስቀርቶ ጊዚያዊ ፈቃድ መስጠት ናቸው። እነኝህ አዳዲስ ሕግጋት ከአንድ ዓመት ጎላ ያሉ ለውጦችን  አሳይትዋል እየተባለ ነዉ።  ስዊድን ፤ የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ተግባራዊ ያደረገቻቸው ህግጋቶች በተገን ጠያቂዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ሜሮን እስጢፋኖስ እንዲህ ያብራራሉ። 
«በጣም አስቸጋሪና የሚያስጨንቅ ሁኔታ ነው የተፈጠረው። በየጊዜው የሚደውሉልኝ ኤርትራውያኖች አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ነው የሚገልጹት። ወደ ማንኛውም አገር ወደ ኖርወይም ቢሆን ለመጓዝ ቪዛ ያስፈልጋቸዋል። የተሰጣቸው የመኖርያ ፍቃድ ለ 13 ወራቶች የሚቆይ ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ቤተሰቦቻቸውን ማስምጣት አይችሉም ቋሚ ስራ ካላገኙ። በተጨማሪ 13 ወራቶች ካለፈ በኋላ ሁኔታቸው እንዴት እንደሚሆን አይታወቅም። እንደ አዲስ የተገን ጥያቄ ነው መቅረብ ያለባቸው ወይስ ይባረራሉ የሚያውቁት ነገር የለም። በዚህ የተነሳ ብዙዎች የተረጋጉ አይደሉም።»
ተገን ጠያቂዎች የሚገኙበትን አስቸጋሪ ሁኔታና የሚሰማቸውን ስሜት ለማሳወቅ በቅርብ ጊዜ በሦስት የስዊድን ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ነበር። በተጨማሪ ኤርትራውያኖች ለብቻቸው ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር። የተገን ጠያቂዎችን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉት ሜሮን ኢስጢፋኖስ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ምን ምን ጥያቄዎች እንደተነሱ ሲያብራሩ 
«ተገን ጠያቂዎች ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የፖለቲካ ተገን ጠያቂዎች በመሆናችን የሚገባን ጌዚያዊ መኖርያ ሳይሆን ቋሚ መኖርያ ፍቃድ ነው የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን ማምጣት ባለመቻላቸው ይሄ መብታቻው እንዲከበርላቸው ነው።»
ሜሮን እስጢፋኖስ እንደሚሉት ከሆነ የተገን ጠያቂ ቤተሰቦች አብዛኛቹ ኢትዮጵያ ነው የሚገኙት።  ኢትዮጵያ ውስጥ ፓስፖርት የሚሰጣቸው ኤምባሲ ባለመኖሩም ወደ ሱዳን መሄድ አለባችሁ እየተባሉ ነው።  
«መጀመርያ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሱዳን መግባት ይኖርባቸዋል። ከዚያም በኤርትራ ኤምባሲ ተገኝተው ይቅርታ ከጠየቁና የ 2% ግብር ካሟሉ በኋላ ነው የሚፈልጉትን ፓስፖርት ማግኝት ይሚችሉት። አንድ የፖለቲካ ጥገኝነት ለጠየቀ ወገን ይቅርታ ጠይቅ፤ 2% ግብር አሟላ ማለት ተቀባይነትና ህጋዊነት የሌለው ነው።»
በስዊድን ቀደም ሲል የተገን ጠያቂዎቹ ቁጥር በሳምንት ጊዜ ዉስጥ እስከ 9000 ይደርስ የነበረው አሁን ወደ 700 ውርዶአል። በያዝነው ዓመት በአጠቃላይ ወደ ሲዊድን የፈለሱት የተገን ጠያቂዎች ቁጥር ከአምናው ጋር ሲወዳደር ከ 163 000 ወደ 24 000 ማሽቆልቆሉ ታዉቋል።ወደ ስዊድን ከፈለሱት ተገን ጠያቂዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር ከያዙት አገሮች መካከል ኤርትራ አንዷ ስትሆን የፍልሰቱ መጠን በ85% እንደቀነሰ የስዊድን ስደተኞች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። 

Grenzkontrolle vor dem EU-Gipfel in Kopenhagen
ምስል AP


ቴድሮስ ምህረቱ 


አዜብ ታደሰ