1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስዊስ የባንክ ሚስጥርና ችግሩ

ሰኞ፣ ሰኔ 22 2001

ኩባንያዎች ወይም የግል ባለሃብቶች በባንኮች የሚስጥር ጥበቃ ከለላ በሽፍንፍን ከአገር ገንዘብ በማሾለክ በሚፈጽሙት ሕገ-ወጥ ድርጊት መንግሥታት በያመቱ የሚያጡት የግብር ገቢ በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ነው።

https://p.dw.com/p/IaTo
ምስል dpa/DW

ከነዚሁ ብዙዎቹም በነገሩ ውስብስብነት የተነሣ ሳይጋለጡ የምዝበራው ተጠቃሚ ሲሆኑ ቆይተዋል። በአንጻሩ ተራው ሠርቶ-አደር ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ ግን መንግሥታት ቁልጭ ያለ ተፈጻሚ ሕግ አላቸው። ገንዘባቸውን በሕገ-ወጥ መንገድ ለሚያሾልኩና ለሚያጸዱ ባለሃብቶች የግብር ሽሽተኞች ገነት ከሆኑት አገሮች መካከል ዋነኛዋ በባንክ ሚስጥር አያያዝ ዘይቤዋ የታወቀችው ስዊትዘርላንድ ናት። የታዳጊው ዓለም አምባገነኖች ሳይቀር እየዘረፉ ያከማቹትን ሃብትም በማስቀመጥ ለዛሬው ድህነት መስፋፋት በተዘዋዋሪም ቢሆን ድርሻ አላት።
የበለጸጉት መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት የ OECD ዓባል ሃገራት የፊናንስ ተጠሪዎች ትናንት በርሊን ላይ ተሰብስበው የግብር አሾላኪዎች ገነት እየተባሉ ወደሚጠሩት አገሮች ገንዘብ መፍሰሱን መግታት በሚቻልበት ሁኔታ ተነጋግረው ነበር። ሃብት ያለው ሁሉ በመሠረቱ ገንዘቡን ሳያስነካ ይዞ ማቆየቱንና ማበራከቱን መምረጡ ያለ ነገር ነው። ግብር መክፈሉን በሕግ እስካልተወጠረ ድረስ ብዙም አይፈቅደውም። ታዲያ ግብር ላለመክፈል ገንዘብን ወደ ውጭ ማሾለኩ በባለሃብቶች ዘንድ የተወደደው ዘዴ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል። ይህንኑ ለማሳካት ደግሞ የግብር ገነት የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አገሮች ሁኔታውን ማመቻቸታቸው አልቀረም።
በዚህ መንገድ በመንግሥታት ላይ የሚደርሰው የገንዘብ ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው። ጀርመንን እንደ ምሳሌ ብንወስድ አገሪቱ በሕገ-ወጡ አሠራር የተነሣ በያመቱ የምታጣው የግብር ገቢ አንድ ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ይጠጋል። ይህ ግዙፍ ገንዘብ በተለይ በዛሬው የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ሰዓት በመንግሥቱ ካዝና ላይ ስንቱን ቀዳዳ ሊሽፍን በቻለ ነበር። እርግጥ ሁኔታውን ለመለወጥ በየጊዜው ጥረት መደረጉ አልቀረም። ችግሩ ሕገ-ወጡን የገንዘብ ፍሰት የሚገታ ጭብጥ መፍትሄ እስካሁን አለመገኘቱ ነው። ሆኖም በሌላ በኩል ጥረቱ እየተጠናከረ መምጣቱ ደግሞ አልቀረም።
ከጥቂት ወራት በፊት ለንደን ላይ በተካሄደው የዓለም የፊናንስ ጉባዔ የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች ዓለምአቀፉን የፊናንስ መዋቅር በአዲስ መልክ ለመቅረጽ በሚያደርጉት ሂደት ሕገ-ወጥ ገንዘብ የሚፈስባቸውን የግብር ገነት ተብዬ አገሮች ቧምቧ ለመዝጋት ተስማምተው ነበር። እነዚህ አገሮች በ OECD አማካይነት በየደረጃቸው በክትትል ዝርዝር ውስጥ እንዲሰፍሩም ተደርጓል። የግብር ገነት ተብለው የሚጠሩት፤ የግብር ገንዘብ አሾላኪዎች ገነት ቢባሉ ይሻላል፤ በተለይ ኩባንያዎችንና የግል ባለሃብቶችን ምንም ወይም በጣም ዝቅተኛ ግብር የሚጠይቁና የሚስቡ ትናንሽ አገሮች ናቸው።
አብዛኛውን ጊዜ በዝቅተኛ ግብር፣ የባንክ ሚስጥር ጥበቃና የረባ የፊናንስ ቁጥጥር ባለማድረጋቸው ባለሃብቶች እየሄዱ የሚሰፍሩባቸውም ናቸው። ከስያሜ አልፈው ያሌሉ የይስሙላ ኩባንያዎችም በአድራሻ ወይም በፖስታ ሣጥን ደረጃ በዚያው እየተከፈቱም የግብር ገንዘብ ማሸኪያ ድልድዮች’ ሆነው ያገለግላሉ። እነዚሁ አካባቢዎች በትውልድ አገራቸው ገንዘባቸውን ከግብር ለመሰወር ለሚሹ ለብዙ የዓለም ባለጸጋዎች ለአያሌ ዓመታት አስተማማኝ ቦታዎች ሆነው ኖረዋል።
የግብር ስርዓታቸው ተስማሚ በመሆኑ ሃብታሞቹ ከገቢያቸው አምሥት በመቶዋን ያህል ቢከፍሉ ነው። ለንጽጽር ያህል በበለጸጉት አገሮች አንድ አማካይ ገቢ ያለው ሠራተኛ ቢያንስ ሃያ በመቶ ግብር ይከፍላል። ፍትህ ሲጓደል እንዲህ ነው! ግን በዚህ ሊቀጥል አይችልም። የትናንቱ የበርሊን ጉባዔም ያመላከተው የግብር ገነት በተባሉት አገሮች ላይ ግፊቱ መጠናከሩን ነበር። በዚህ ላይ እንመለስበታለን፤ በቅድሚያ በስዊስ የባንክ ሚስጥር አያያዝ ዘይቤ ላይ እናተኩርና የደምበኞችን ገመና ሸፍኖ የመያዙ አሠራር ምንም እንኳ የቆየ ልምድ ቢኖረውም የባንኩ ሕግ የጸናው እ.ጎ.አ. በ 1935 ከ 74 ዓመታት ገደማ በፊት ነው።

የግብር ሽሽተኞች ገነት እየተባሉ ወደሚጠሩት አካባቢዎች ከሚሻገረው ገንዘብ ሲሦው በስዊስ ባንኮች ውስጥ ተከማችቶ እንደሚገኝ ይገመታል። ከዚሁም ከሰባ እስከ ዘጠና በመቶው ግብር ያላየው ነው። በነገራችን ላይ የሶሥተኛው ዓለም ገዢዎች እየመዘበሩ የሚያሸሹት ገንዘብም በዚሁ ይጠቃለላል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እነዚሁ ታዳጊ አገሮች ራሳቸው ግብር ሳይከፈልበት በሚሄደው ገንዘብ በያመቱ 15 ሚሊያርድ ዶላር ያጣሉ። ለዚህም ነው የስዊስ ባንኮች የሚስጥር አያይዝ ፖሊሲ በተዘዋዋሪም ቢሆን በታዳጊው ዓለም ድህነት መስፋፋት ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚባለው። በአጠቃላይ የስዊስ ባንኮች በነዚህ ደምበኞቻቸው ላይ አንዳች መረጃ የማይሰጡ መሆናቸው አገሪቱን የሕገ-ወጦች ገነት ያደርጋታል።

ስዊትዘርላንድ የኢጣሊያ ማፊያ ከሕገ-ወጥ ንግድና መሰል ተግባሩ የሚያገኘውን ገንዘቡን ሲያጸዳባት ኖሯል። ከባለጸጋዎች እስከ አምባገበኖች ብዙዎች ግብር ሳይከፍሉ የባንኩ ስርዓት ተጠቃሚዎች ናቸው። እርግጥ በዚህ ፍትህ አልባ በሆነ የአሠራር ዘይቤ ቁጣ የሚያድርባቸው የአገሪቱ ዜጎችም አይታጡም። የውጭ ባለሃብቶች ነጻ ሆነው ሲስተናገዱ አገሬው ዓመታዊ ግብሩን ሳያዛንፍ እንዲከፍል መደረጉ የማይዋጥላቸው ብዙዎች ናቸው። በሌላ በኩል የስዊስ መንግሥት የባንኩን ስርዓት ለመጠገን ብዙ ጥረት አለማድረጉ ያለ ምክንያት አይደለም።
ይሄው የፊናንሱ ዘርፍ ለአገሪቱ ብሄራዊ ኤኮኖሚ ታላቅ ጠቀሜታ አለው። ከአገሪቱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ከአሥር በመቶ በላይ የሚሆነው የሚገኘው ከባንኩ ዘርፍ ነው። ከዚሁ በተጨማሪ በዘርፉ ለ 100 ሺህ ያህል ሰዎች የሥራ ዕድልም ከፍቷል። የስዊስ ባንኮች በግምት 6,900 ሚሊያርድ ፍራንክ የሚሆን ገንዘብ እንደሚያስተዳድሩ ነው የሚገመተው። ከዚሁ 58 በመቶ የሚሆነው ሃብት ደግሞ ከውጭ የመነጨ ነው። አገሪቱን ለውጭ ባለሃብቶች ማራኪ ከሚያደርጓት ምክንያቶች መካከል ከባንኩ ምስጢርና ከግብር ነጻነት ባሻገር ሌሎች ሁኔታዎችም አሉ።

ስዊስ በአውሮፓ ያላት አማካይ አቀማመጥ አንዱ ነው። ገለልተኛና ነጻ ስርዓቷም በውጭ ባለሃብቶች ዘንድ አስተማማኝ ያደርጋታል። ከዚሁ ሌላ የተረጋጋ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ይዞታዋ፤ እንዲሁም ምንዛሪዋ ስዊስ-ፍራንክ ከሌሎች ምንዛሪዎች አንጻር ያለው ጽናት ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። የሆነው ሆኖ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ የተነሣ ሁኔታው በነበረበት ሊቀጥል ከማይችልበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል። ዛሬ የግብር ኪሣራውን ለመግታት የግድ ግልጽ አሠራርና የተሻለ የመረጃ ልውውጥ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ የባንኩ ዘርፍ አዋቂ የሆኑት የስዊሱ ባለሙያ ማኑዌል አማን እንደሚሉት አገራቸው የባንክ ሚስጥርን በተመለከተ ውስጧን ማሳየቷ የሚያጠራጥር ነው።

“የባንኩ ምስጢር የሚከፈተው አንድ ጭብጥ ጥርጣሬ መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ለዚያውም የተጠርጣሪውና የባንኩ ስም ተጠቅሶ! እንግዲህ በዕውነቱ አንድ ጭብጥ ነገር ሲኖር ይሆናል። ልምድ እንደሚያሳየው ከሆነ ግን ይህን መሰሉ ጭብጥ ሁኔታ ከስንት አንዴ ቢከሰት ነው”

ከግብር የሚያመልጡ ባለሃብቶችን በማጋለጡ በኩል ከስዊስ አስፈላጊውን የመረጃ ዕርዳታ ለማግኘት የድርብ፤ ማለት የሁለት ወገን ማስገበሪያ ውሎች መደረግ ይኖርባቸዋል። እንግዲህ ስዊስ ከአውሮፓ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት የክትትል ዝርዝር እንድትወጣ 12 አዳዲስ ስምምነቶች ገና መፈረም አለባቸው ማለት ነው። በነገራችን ላይ እስካሁን 70 ከሚሆኑ የድርብ ግብር አከፋፈል ውሎች ስድሥቱ ብቻ ናቸው የተፈረሙት። እናም ግፊቱ መቀጠሉ የማይቀር ነው።

“ስዊስ ከውጭ በሚደረገው ግፊት የአውሮፓን የኤኮኖሚ ትብብና የልማት ድርጅት መስፈርት በመቀበል በብዙ ነጥቦች የድርጅቱና የአውሮፓን ሕብረት ፍላጎት ተከትላለች። እና ግፊቱ ባለበት ከቀጠለ አገሪቱ በዚሁ አቅጣጫ ተጨማሪ ዕርምጃ ማድረጓ የማይቀር ነው። ተጨማሪ ግፊት መጠበቅም ይኖርባታል”

ትናንት በርሊን ላይ ተሰብስበው የተነጋገሩት ሃያ የ OECD ዓባል መንግሥታት ተጠሪዎች በተወሰኑ ጭብጥ በተባሉ ውጤቶች ተስማምተዋል። ስዊስም በድርጅቱ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሳተፍ ወደፊት ገንቢ በሆነ መንገድ ለመተባበር ዝግጁነት ማሣየቷ ነው የተነገረው። የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ፔር ሽታይንብሩክ በስዊስ ላይ ሃይለ-ቃል ሲሰነዝሩ ቢቆዩም የጉባዔውን የጋራ መግለጫ በማወደስ የአገሪቱንና የሌሎቹንም ስም ጠቅሰው ነው ያመሰገኑት።

“እነዚህ ሃገራት የ OECD-ን መስፈርት በመቀበሉ ረገድ ከዚህ ቀደም የአሁኑን ያህል ዝግጁነት አልነበራቸውም። እንግዲህ አሁን የምንጠብቀው ተገቢው የእጥፍ ግብር ውል ለውጥ እንደሚመጣ ነው። ግን በዚህ አጋጣሚ እነዚህ አገሮች በጉባዔው ዝግጅትና እንደዛሬው በንግግሩ ላይ ላሣዩት ትብብር ሊወደሱ ይገባቸዋል። ስለዚህም ስም በመጥቀስ አውስትሪያን፣ ሉክሰምቡርግንና ስዊስን አመሰግናለሁ”

ከትናንቱ ጉባዔ ስምምነት ወዲህ ስዊስና መሰል አገሮች የወደፊት ዕርምጃ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። አለበለዚያ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅቱን የዳታ ልውውጥና ትብብር መስፈርት በፍጥነት ገቢር ላላደረገ የሚከተለው ማዕቀብ ነው። የጉባዔው የጋራ መግለጫ የፊናንስ መቀጮ እንደሚከተል አመልክቷል።

MM/DW

HM