1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴኔጋል ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ውጤት

ሐሙስ፣ የካቲት 22 2004

ትናንት ከቀትር በኋላ ይፋ የተደረገው የሴኔጋል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት እንደሚያስረዳው፤ ጎምቱው መሪ ፤ አብዱላዬ ዋድ እንደፎከሩት፤ በድምፅ ብልጫ በመጀመሪያ ዙር ማሸነፍ ባለመቻላቸው ፣ የኀፍረት ሸማ ነው የተከናነቡት። ስለሆነም፤ መጋቢት 9 ቀን

https://p.dw.com/p/14Cp7
የቀድሞ ጠ/ሚንስትር ማኪ ሳል
ፕሬዚደንት አብዱላይ ዋድምስል AP

2004 ዓ ም የሚካሄደውን 2ኛ ዙር ውድድር መጠበቅ ግድ ይሆንባቸዋል። የ 85 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ዋድ፣ በመጀመሪያው ዙር 34,82 ከመቶ ድምፅ ሲያገኙ፤ ተፎካካሪአቸው በ 26,57 ከመቶ ድምፅ በሁለተኛነት ይከተላሉ። ምርጫውን በመጀመሪያ ዙር ለማሸነፍ ዋድ ቢያንስ 50 ከመቶ ውጤት ማግኘት ነበረባቸው። ስለ ሴኔጋሉ ምርጫና ሂደት---ተክሌ የኋላ---

ፕሬዚዳንት አብዱላዬ ዋድ በ 85 ዓመት ዕድሜአቸው ነው ለ 3ኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም አከራካሪ ከሆነው የምርጫ ውድድር የገቡት። በምርጫው እጩ ሆነው የቀረቡት ተወዳዳሪዎች 13 ቢሆኑም ዋድን ይበልጥ የሚፎካከራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትራቸው ማኪ ሳል ናቸው። ስለቀጣዩ ምርጫ፣ በዳካር ዩኒቨርስቲ የህገ-መንግሥት ጉዳይ ፕሮፌሰር አሜት እንዲያዬ--

«እንደሚመስለኝ ሁለተኛው ዙር ምርጫ አስገዳጅ ነው። ይህም በአንድ ጎን አወንታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው። በሴኔጋል ለነገሩ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ማካሄድ የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። ማንም በመጀመሪያ ዙር ምርጫ አሸንፋለሁ ብሎ መተማመን አይችልም።»

የመጀመሪያው ምርጫ አጠቃላይ ውጤት በዚህ ሳምንት ማለቂያ ላይ ይሆናል የሚገለጠው። ውጤቱ ያን ያህ ል እንዲዘገይ መደረጉን ታዛቢዎች በጥርጣሬ ዐይን ይመለከቱት ይዘዋል። ምርጫውን ለመታዘብ በዚያ ከተገኘው የአውሮፓው ኅብረት ቡድን አባላት መካከል ክርስቲያን ዳን ፕሬዳ የተባሉት እንዲህ ይላሉ--

«የምርጫውን ውጤት ለማሳወቅ ጊዜው መጓተቱ፣ ጥርጣሬን ነው የሚያስከትለው፣ውጥረቱንም ያባብሳል። መንግሥት እዚህ ላይ ጥሩ አይደለም ያደረገው።

ግልጽ አሠራር ሊኖረው ይገባል። በአሁኑ የኢንተርኔት ዘመን፤ ሴኔጋላውያን ይፋውን የምርጫ ውጤት ለማወቅ እስከነገ ዓርብ ድረስ መጠበቅ አይገባቸውም ነበር።»

ያም ሆነ ይህ በእስካሁኑ ውጤት ፤ አብዱላዬ ዋድ አሳፋሪ ሽንፈት እንዳጋጣማቸው ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት። 13 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈው ድምጽ በተከፋፈሉበት ሁኔታ ማሸነፍ ያልቻሉት ዋድ፤ በሁለተኛው ዙር ይቀናቸዋል ብለው የሚያስቡት ብዙዎች አይደሉም። እንዲያውም፣ በሁለተኛው ዙር የተቃውሞው ወገን ተወዳዳሪዎች ሁሉ ፣ ከቀድሞው ጠ/ሚንስትር ማኪ ሳል ጎን ይሰለፋሉ የሚል ግምት ነው ያለው።

Macky Sall Senegal Dakar
ምስል AP

ፕሬዚዳንት ዋድ፤ ከሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ተሻግረው ለ3ኛ ጊዜ ውድድር ላይ መቅረባቸውን መራጩ ህዝብ እምብዛም አልወደደላቸውም። ሴኔጋል ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች በኋላ በቀጠሉት አባዛኞቹ ዓመታት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የምታካሂደው በየ 7 ዓመት አንድ ጊዜ ነበረ። አብዱላዬ ዋድ፣ እ ጎ አ በ 2000 ዓ ም ከተመረጡ በኋላ፣ የሥልጣን ዘመኑን ወደ 5 ዓመት ዝቅ አደረጉት። ከዚያም እ ጎ አ በ 2008 ዓ ም፤ እንደገና የህገ-መንግሥቱን አንቀጽ ለውጠው ወደ 7 ዓመት እንዲመለስ አደረጉ። ህገ-መንግሥቱ በተለያዩ አንቀጾች ሳቢያ 15 ጊዜ ለውጥ ተደርጎበታል። በሥልጣን ላይ 12 ዓመታት የቆዩት አብዱላዬ ዋድ፤ ሌሎች ጎረቤቶች በኃይል ሲገዙ እርሳቸው ለዴሞክራሲ ከቆሙት ጥቂት አፍሪቃውያን መሪዎች መካከል አንደኛው መሆናቸው ይነገርላቸው ነበር። ዋድ፤ የተቃውሞው ወገን ባልረባ በመሆን የአገሪቱ ሶሺያሊስት ፓርቲ ሥልጣኑን ያለዝብ ዘንድ 25 ዓመታት መታገላቸው ይነገርላቸዋል። በአማዛኙ በበጎ ነገር ይወሱ የነበሩት ዋድ፤ ጥላቻ ማትረፍ የጀመሩት ለወንዱ ልጃቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ላቅ ያለ ሥልጣን እየሰጡ በመምጣታቸው ነው። እንዲያውም አሽሟጣጮች፤ ልጅየውን «የሰማይና ምድር ሚንስትር » ይሏቸው ነበር። ምክንያቱም የተለያዩ ሚንስትሮችን ፣ ለምሳሌም ያህል፤ የመሠረተ-ልማትና የኃይል ምንጭ ጉዳይ ሚንስትር ተብለው ተሾመው ነበረና!

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ