1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴቶች መብት ምን ያህል ይከበራል?

ሐሙስ፣ የካቲት 10 2008

« የሴቶች መብት ተብሎ ወረቀቱ ላይ የተፃፈዉ እዳለ ሆኖ፤ ከወንዱ እኩል ቡና ቤት ከመሄዱ፤ ለሊት ሲጨፍሩ ከማደሩ በዘለለ፤ በትክክል ሴት ልጅ የሚገባትን መብት አግኝታለች ተብዬ ብጠየቅ፤ የሚታየኝ ምንም ነገር የለም። ዛሬም ዩንቨርስቲ የሚገኙ ተማሪዎች ለአስተማሪዎቻቸዉ ራሳቸዉን ሸጠዉ ዉጤት የሚቀበሉ አሉ።

https://p.dw.com/p/1HxaY
Feuerholz zum Heizen Äthiopien
ምስል DW/L. Rahnert

የሴቶች መብት ምን ያህል ይከበራል?

በተለያየ ሞያ ዉስጥ ገብተዉ መዉጣት አቅቶአቸዉ፤ ለቀጠርዋቸዉ ሰዎች ወይም ደግሞ ለአሰልጠኑዋቸዉ ሰዎች ወይም አለቃዎቻቸዉ ለሆኑ ወንዶች ራሳቸዉን አስገዝተዉ የሚወጡ ሴቶችም አሉ። ታድያ እነዚህ ሴቶች መብታቸዉ ተከብሮላቸዋል?» ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ።

Mesob Traditioneller Esstisch Äthiopien
ምስል DW/L. Rahnert


በፍቅረኛሞች ዘንድ ታስቦ የዋለዉን «ቫለንታይን ዴይ » የፍቅረኛሞች ቀንን አስታከን ለጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ በኢትዮጵያ ስላለዉ የሴቶች መብት ጉዳይ ላቀረብንለት ጥያቄ ያካፈለን ኃሳብ ነበር። በምዕራባዉያኑ ዘንድ በቀይ ጽጌረዳና ልብስ ደምቆ የሚታሰበዉ ቀን በሃገራችን በተለይ በከተሜዉ ወጣቶች ዘንድ እየተዘወተረ መጥቶአል። በከተሞች አካባቢ ሽያጮችን ያካተተቱ እለቱን የሚዘክሩ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች መካሄድ ጀምረዋል። በርግጥ የፍቅረኛሞች ቀን መታሰቡን የማይቃወሙ እንዳሉ ሁሉ ባህላችን ስላልሆነ እለቱ መዘከሩ አያስፈልግም የሚሉም አሉ። ይህ ቀን ምን ያህል እንደማፈቅር ለሰዉ እዩልኝ ለማለት ካልሆነ በስተቀር፤ እዉነተኛ ፍቅርን ከመግለፅ ጋር ምንም ግንኙነት የለዉም የሚሉ ኢትዮጵያዉያን ጥቂት አይደሉም። በዓለማችን የፍቅረኞችም ቀን ሆነ የሴቶች ቀን ብሎም የእናቶች ቀን፤ ይከበራል። ነገርን ነገር ያነሳል ነዉና በእለቱ ዝግጅታችን፤ በሀገራችን የሴቶች መብት ምን ያህል ይከበራል? ጎታች የሆነዉ ሴትን ልጅን ወደ ጓዳ የሚለዉ ልማድ ምን ያህል እያስቀረነዉ ነዉ? የእለቱ መሰናዶአችን ርዕስ አድርገን ይዘናል።


ስለ ሴቶች መብት ሲጠቀስ በዋነኛነት የምናነሳው መሠረታዊ ስለሆነው የሰው ልጆች መብት ነዉ። ይህ ደግሞ ስለ እናቶቻችን፤ እህቶቻችን ሴት ልጆቻችንና ሴት አያቶቻችን፤ መብት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም መሠረታዊ በሆነው የሴቶች መብትና በሌሎች ሰዎች መብት መካከል የምንፈጥረው ምንም ዓይነት ድንበርም ሆነ መለያ ክልል ሊኖር አይችልም፡፡ የሴቶችን መብት በተመለከተ መንግሥት ብዙ ሥራ ቢያከናዉንም ሕግጋትን ቢያወጣም የሴት እኩልነትን ማኅበረሰቡ ተግባራዊ እስኪያደርገዉ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ የገለፁልን በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉን ጥቃት ለደረሰባቸዉ ሴቶች ቤት ያቋቋሙት ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር፤
«እንደ መንግሥት ሕግ ነዉ የሚወጣዉ፤ በሕገ-መንግሥቱ የወጣ ሕግ አለ። ግን ሕጉ መኖሩ የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ ይቀይረዋል ማለት አይደለም። ሕጉ ለአጠፋ ሰዉ መቅጫ ወደ ሕግ ፊት ሲቀርብ መብት ማስከበርያ ነዉ የሚሆነዉ። ነገር ግን በባህል ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቦቻችን ጋር ስናድግም ሆነ ልጆችን ስናሳድግ ቤተስብም ልጆችን ሲያሳድግ ወንድና ሴት ልጅ መካከል ልዮነት የሚፈጥረዉን ለሴት የሚሰጠዉ ቦታ ቀደም ሲል ጊዜ ጀምሮ ዝቅ ያለ ስለሆነ አሁን መሰራት ያለበት የሰዉን አዕምሮ በመቀየር ላይ ነዉ ብዙ መሰራት ያለበት። አሁንም የሚታየዉን ሁላችንም የምናዉቀዉ ነዉ። በየቦታዉ ለሴቶች የሚሰጠዉ ክብር አንዳንድ ቦታ ጥሩ ሲሆን፤ በብዛት የሚታየዉ ግን አሁንም እንዳልተቀየረ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ክብር እንዳለ ነዉ። ተቀይሮአል ክብር እየተሰጠ ነዉ በሚባልበት ቦታም ቢሆን ለዉጡ ገና አዝጋሚ እንደሆነም ይታያል። ስለዚህም የሴት መብት ተከብሮአል ፤ ሴቶች ከወንዶች እኩል እየታዩ ያለበት ሁኔታ ነዉ ማለት አይቻልም።»

በተለይ በምዕራቡ ዓለም የጎርጎረሳዉያኑ የካቲት ወር በገባ በሁለተኛዉ ሳምንት የሚከበረዉ ቫለንታይንስ ዴይ ማለት «የፍቅረኛሞች ቀን» ባሳለፍነዉ እሁድ ታስቦ ዉሎአል። በምንኖርበት የግሎባላይዜሽን ማለትም በአፅናፋዊዉ የኤኮኖሚ ትስስር ዘመን ዓለም ከሌላዉ ማኅበረሰብ የምንወስደዉን ተለምዶ ማየቱ እንደማይከፋ የሚገልፀዉ ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ ቀኑ ይላል፤
« የኔ እይታ ብዙዉን ጊዜ ከባህል አንፃር ነዉ። ከራሳችን ባህል ጋር የሚጣጣም ነዉ፤ ወይስ አይደለም? ምን መዉሰድ አለብን፣ የትኛዉን ማስቀረት አለብን የሚለዉን እመለከታለሁ። የፍቅር ቀን « ቫለንታይንስ ዴ » የሚባለዉን ቃሉን ስንመለከት ማንም ሰዉ ሊያደርገዉ የሚገባ፤ ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸዉ ፍቅራቸዉን እንዲገልፁ ቢሆን፤ ፍቅረኛ ለፍቅረኛዉ ቢያደርገዉ መልካም ነዉ። ግን ሌሎች አብረዉ ተያይዘዉ የሚመጡ ባህላዊ የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ ከራሳችን ነገር ጋር ማያያዝ ያለብን ይመስለኛል። »

Valentinstag in Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa


ቀኑ እንዳየነዉ ፍቅረኛ ለፍቅረኛዉ አበባ የሚሰጥበት ፍቅሩን የሚያሳይበት ሆኖዉ ነዉ?
« በእዉነቱ አገላለፁ በጣም ጥሩ ነዉ፤ ግን ፤ አንደኛ ቀኑ ከንግድ ጋር የሚያያዝ ነዉ። ስለዚህ ቀን ምንነት የሚነገረዉ አብዛኛዉን ጊዜ ከአንድ ወገን ብቻ ነዉ። በዚህ ቀን ሰዎች አላስፈላጊ ወጭ እንዲያወጡ ይገደዳሉ። የሚሰሙት ማስታወቅያዎች ወጣቱን ባልሆነ መንገድ የሚያማልሉ ናቸዉ ። እንደሚታወቀዉ ወጣቱ ለእንደዚህ ዓይነት ነገሮች በቀላሉ የሚሰነፍ ነዉና ካሉብን ሃገራዊ በአላት ላይ ተጨማሪ አንድ ወጭ የሚያስወጣ በዓል እጨምራለን ማለት ነዉ። በዚህ ቀን የሚወጣዉ ወጭ ብዙ ነዉ። ፍቅረኛሞቹ የሚለብሱት ተመሳሳይ መሆን አለበት። ቀይ ኮፍያ፤ ቀይ ሸሚዝ ፤ቀይ ቀሚስ የመሳሰሉ ነገሮች ይኖራሉ። ስለዚህ ቀኑ እንደ በዓል ታስቦ፤ ሰዉ እቁብ ሊገባ፤ ሊበደር ነዉ ማለት ነዉ። ስለዚህም እኔ ይህ የፍቅረኛሞች ቀን ለአንድ ቀን ብቻ መሆን የለበትም ከሚሉት ወገን ነኝ። ፍቅር የሕይወታችን አንድ አካል ስለሆነ በየቀኑ ልንተሳሰብ፤ እናደርግ ካልን ደግሞ በራሳችን የራሳችን የምንለዉ ቀን ሊኖር ይገባል እንጂ፤ ይህ የፍቅር ቀን ተብሎ ተወስኖ፤ በዚህ ቀን አላደረክልኝም የሚል ወቀሳም ሊመጣብን ሁሉ ይችላል። ስለዚህ ሰዎች ቀኑን ሳይወስኑ ማታም ሆነ ጠዋት ነገም ሆነ ዛሬ ፍቅራቸዉን ሊገላለፁ ከፈለጉ አንድ የራሳቸዉ የተለየ ቀን ሊኖራቸዉ ይችላል። ከዝያ በተረፈ የግዴታ « ፊብርዋሪ 14 ነዉ» የሚለዉ ወደ አለመግባባት ሊያመጣ ይችላል የሚል ኃሳብ አለኝ»


ይልቁንም የሴቶች መብት ቢከበር ለሴት የሚገባትን ክብር ብንሰጥ ያሉን በሴቶች መብት ጉዳይ ላይ የሚሰሩት ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር፤ ሴትን ወደ ጓዳ የሚለዉን ልምዳችን ለማስቀረት መሥራት ይጠበቅብናል።
« እኔ መቼም አስተዳደጋችን መሠለኝ። አስተዳደጋችን አሁንም ሆነ ቀደም ሲልም የነበረዉ፤ አባት ሚስቱን እንዴት ይይዛት እንደነበረ የሚያይ ልጅ፤ እሱም ራሱ ሚስቱን እንደዝያ ነዉ የሚይዘዉ። እቤት ዉስጥ አባት ሴት ልጁን በትክክል የማያይ ከሆነ ሴት ልጁም እንደ አልቃሻ የምትታይ ከሆነ፤ ወንዱ ልጅም ደብዳቢ፤ ጉልበተኛ ሆኖ በሚታይበት ኅብረተሰብ ዉስጥ ያንን ይዞ ነዉና የሚሄደዉ፤ ያንን አስተዳደግ ላይ መቀየር ካልቻልን፤ ከሕፃንነት መቀየር ካልቻልን ፤ ይህ ፀባይ እየቀጠለ ነዉ የሚሄደዉ። በሴቶች ጉዳይ ላይ ከ 20 ዓመታት በላይ ሰርቻለሁ። ቀደም ሲልም እንደምናየዉ ትንሽ የባል ለዉጦች ይታያሉ ፤ ይህ ለዉጥ ደግሞ በአዲሱ ትዉልድ ላይ እየታየ ነዉ ማለት እችላለሁ። እቤት ዉስጥ መረዳዳቱም ወጣት ባለትዳሮች ላይ ይታያል። ይህ ደግሞ ሁለቱ ሰርተዉ ስለሚገቡ ኑሮም ሊሆን ይችላል። ምናልባት በጣም በቁጥር በተወሰነ፤ ቤተሰብ አካባቢ ለዉጥ ይታያል። በጣም ዉስነነት አለዉ ቢሆንም ሊበረታታ የሚገባዉ ነዉ። ችግሩ ወንዶች ብቻ ላይ አይደለም የሚታየዉ። አሳዳጊዎቹ ሴቶችም ነን፤ እኛ ሴቶች ራሳችን ልጆቻችን ላይ ልዩነት ፈጥረን እናሳድጋለን። እናቶች ሴትዋ ልጃችን ከትምህርት ቤት ስትመጣ ቶሎ ብለን የምንሰጣት የማዕድ ቤት ሥራን ነዉ። ወንዱ ልጅን ደግሞ ወጥቶ ኳስ እንዲጫወት እንፈቅድለታለን። እናም ይህን አይነት ተፅኖ እንዲመጣ የምናደርገዉ እኛ ራሳችን አሳዳጊ እናቶችም ነን። ይህን ፀባይ ደግሞ እኛ እንዳደግንበት ከጥንት ይዘን እንደመጣነዉ መሆኑ ነዉ። ወንዶች እቤት ዉስጥ ሲሰሩ «ይሄማ ሴታ ሴት ነዉ» እያልን እንወርፋለን።

Feuerholz zum Heizen Äthiopien
ምስል DW/L. Rahnert

እቤት ወስጥ አንድ ወንድ ልጅ እናቱን ሊጥ እያቦካ እንጀራ እየጋገረ፤ እንዲሁም ቡና እያፈላ ከአገዘ፤ እነዚህን ልጆች ጓደኞቻቸዉም ሆነ ሌላዉም ኅብረተሰብ ይሄማ ሴታ ሴት ነዉ፤ ማዕድ ቤት ሲሰራ ነዉ የሚዉለዉ ሲሉ ይናገራሉ፤ ይወርፋሉ፤ ያንጓጥጣሉ። ይህ የሚያሳየዉ በኅብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለዉጥ አለመኖሩን ነዉ። አንዳንድ ሚስቶችም ቢሆኑ ባሎቻቸዉ ወደ ጓዳ ገባ ገባ ሲሉ «ይሄ እንደዉ ሴታ ሴት ማዕድ ቤት እየገባ» «እንደ ሴት ማዕድ ቤት እየገባ» የሚሉና ወንዶች ወደ ማዕድ ቤት ሲገባ የማይወዱ ሴቶች አሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ይልቁንም የሴቶች መብት ቢከበር ለሴት የሚገባትን ክብር ብንሰጥ ያሉን በሴቶች መብት ጉዳይ ላይ የሚሰሩት ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር፤ ሴትን ወደ ጓዳ የሚለዉን ልምዳችን ለማስቀረት መሥራት ይጠበቅብናል። እና ይህ ማኅበረሰቡን መቀየር ሥራ ከራስ ቤት ይጀምራል ነዉ።
በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ ዉስጥ የሚታየዉን አንዳንድ ጎታች አስተሳሰብ ጥቂት ኢትዮጵያ ሚዲያዎችም በጣም በጥቂቱ ይንቀሳቀሳሉ ያሉት ወ/ሮ ማሪያ እንዲያም ሆኖ በሚዲያ የሚተላለፉት አንዳንድ ነገሮችም ሴትን አሳንሰዉ የሚያሳዩ ሆነዉ የሚታዩና የሚደመጡ መኖራቸዉን ሳይገልፁ አላለፉም። ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለም የወ/ሮ ሚርያምን ኃሳብ ይጋራል። የሴት ልጅ እኩልነት የሚለካዉ ለዉጭ ዓለም እራስዋን በምታሳይበት መንገድ ሳይሆን በሚሰጣት መልካም እድል ነዉ ሲል ተናግሮአል።
ለእህት እናቶቻችን አያት አክስቶቻችን በአጠቃላይ ለሴቶች መብት መከበር በቅድምያ በትምህርቱ በሥራዉ እንዲሁም በመሪነት ደረጃ ለሴቶች እድልን በመክፈት፤ ሴቶችን የሚያሳንሱ ጎታች ልምዶችን ከማኅበረሰቡ መቅረፍ ይቻላል፤ ሚዲያዎችም ለዚህ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ በመሰናዶዉ ላይ ቃለ- ምልልስ የሰጡንን በማመስገን የእለቱን ዝግጅት የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።


አዜብ ታደሰ


ኂሩት መለሰ