1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳዑዲ ተመላሾች እና ተግዳሮቶቻቸው

ረቡዕ፣ ሰኔ 14 2009

ሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ የውጭ ዜጎች ያለ ብዙ እንግልት እንዲወጡ የሰጠችው ቀነ ገደብ በዚሁ በያዝነው ሳምንት ማብቂያ ላይ ይጠናቀቃል። ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ከዓመት በፊት ጀምሮ የተጋረጠባቸው የፋይናንስ ችግር በአሁኑ ወቅት መባባሱ ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/2f7Qr
Saudi-Arabien Abschiebung illegaler äthiopischer Arbeitsmigranten
ምስል DW/S. Shibru

የሳዑዲ ተመላሾች እና ተግዳሮቶቻቸው

በሳዑዲ ዓረቢያ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ 400,000 እንደሚጠጋ የአፍሪቃ ዜና አገልግሎት (APA) ዘገባ ያትታል። ሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ የውጭ ዜጎች ያለ ብዙ እንግልት እንዲወጡ የሰጠችው ቀነ ገደብ በዚሁ በያዝነው ሳምንት ማብቂያ ላይ ይጠናቀቃል። ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ከዓመት በፊት ጀምሮ የተጋረጠባቸው የፋይናንስ ችግር በአሁኑ ወቅት መባባሱ ተገልጧል። 

እስካሁን ከሳዑዲ ዓረቢያ  ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ስደተኞች ቁጥር እጅግ ዝቅ ያለ ነው። ከሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ አካባቢ የድምፅ መልእክቱን በዋትስአፕ የላከልን አድማጫችን ተማም ኑሪ ይባላል። ተማም ካለፉት አምስት ዓመታት አንስቶ  ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚኖረው ያለፈቃድ ነው። እሱና በርካታ ጓደኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ላለመመለስ መወሰናቸውን ገልጦልናል። እንደተማም ከሆነ ምክንያታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ነው። «በጣም ብዙ ጓደኞቼ አሉ እዚህ አካባቢ። ከጓደኞቼ መካከል አንድም ሰው ወደ ኢትዮጵያ እሄዳለሁ ብሎ ያሰበ የለም» ያለው ተማም «ሁሉም የሚመጣውን እንቀበላለን እያለ ነው ያለው» ብሏል።

ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ያለሕጋዊ ፈቃድ ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመተው  400,000 ግድም ኢትዮጵያውያን መካከል ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ከ30,000 እንደማይበልጡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሰሞኑ ዘገባ ይጠቁማል። 

Illegale aus Äthiopien in Saudi-Arabien
ምስል DW/Sileshi Sibiru

ወጣት አወል ሰዒድ እንደ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያቀናው የዛሬ ሦስት ዓመት ሐምሌ ወር መገባደጃ ላይ ነበር። አሁን ከሳዑዲ ተመልሶ ኢትዮጵያ ነው የሚገኘው።  እሱ በሚኖርበት አካባቢ ደቡብ ወሎ ከሳዑዲ ዓረቢያየተመለሱ ስደተኞች ወደ እየ ቤተሰቦቻቸው መበተናቸውን ገልጧል። «…በየቀበሌ ብቻ ትንሽ ተመላሾች ተብሎ የጎጥ አመራሮች ሲመዘግቡ አስታውሳለሁ»  ያለው አወል «ከዚያ ወዲህ ምንም የተደረገ ነገር የለም። ድፍን ያለ ነው» ሲል በሚመለከተው አካል በኩል እስካሁን ምንም እንዳልተደረገላቸው ተናግሯል።

አወል የወደፊት ዕቅዱ ራሱን  የሚያስተዳድርበት ተሽከርካሪ መግዛት ነበር። ያን ለማድረግም በወር ከሚያገኘው 1500 ዶላር እየቆጠበ ለታናሽ ወንድሙ መማሪያ እና ለተሽከርካሪው መግዢያ ይልክ ነበር። አሁን ይላል አወል «ቤተሰብ ላይ ጥገኛ ሆነናል።» ለቁጠባ ይልከው የነበረው ገንዘብ ለቤተሰብ ማሳከሚያ እና አንዳንድ ድንገተኛ ወጪዎች «በግማሽ ያኽል» መቀነሱን ተናግሯል።  «የእኛ እድሜ የእኛ ገንዘብ መስዋዕት ቢሆንም፤ ቤተሰቦቼ በአሁኑ ወቅት ኑሮዋቸው ደህና ነው» ያለው አወል ከሳዑዲ ዓረቢያ ድንገት «እንደምወጣ አስቤውም አላውቅም» ብሏል። በድንገት ውጡ ሲባሉ ግን «የያዝነውን ኩርቱ ፌስታል ይዘን ኺደን ያንኑ ይዘን የመጣንበት አጋጣሚ አለ፤ ያንንም ያላገኘንበትም አጋጣሚ አለ።» 

Illegale aus Äthiopien in Saudi-Arabien
ምስል DW/Sileshi Sibiru

የፋይናንስ ባለሞያው አቶ አብደላ ሬዱዋን ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በአንድ ባንክ ውስጥ በመድኅን ዋስትና ክፍል ሠራተኛ ናቸው። በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ የተሠማሩባቸው የሥራ መስኮች ከገቢ አንጻር ዝቅተኛ የሚባሉ ናቸው ይላሉ። ኢትዮጵያውያኑ በአብዛኛው አማካይ ገቢያቸውም በወር ከ1000 ዶላር የዘለለ እንዳልሆነ አቶ አብደላ ይገልጣሉ። የኢትዮጵያውያኑ ገቢ ከሌሎች የውጭ ዜጎች ገቢ ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ የሚባለው ነው። «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉ ከእለት ገቢ ባልዘለለ እና እምብዛም ጥሪት ባላካበቱበት ሁኔታ በርካቶች ውጡ መባላቸው ችግሩን ማባባሱን ይናገራሉ። ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ በሳዑዲ ዓረቢያ በግንባታ እና የአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ላይ የተሰማራ በመሆኑ «ውጡልን አዋጁ ሳይመጣ በፊት ራሱ የእኛ ማኅበረሰብ» በገቢ እና ፋይናንስ ቀድሞውኑም እንደተጎዳ ተናግረዋል።

ከሌሎች ሃገራት ስደተኞች ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውያን አንድም በግንባታ ሥራ አለያም በችርቻሮ ንግድ እና አገልግሎት ሰጪ መስኮች ላይ እንደሚያተኩሩ አቶ አብደላ ገልጠዋል። ሴቶቹ ደግሞ በዋናነት በቤት ውስጥ ሠራተኛነት። ወትሮም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዓረቢያ በወጣው አዲስ ሕግ ካለፈው ዓመት አንስቶ ተጽዕኖው እንዳረፈባቸው ተናግረዋል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሳዑዲ ዓረቢያ ሞያዊ ሥራዎች ላይ «አናሳ ነው» ያሉት አቶ አብደላ  2030 የተባለው የሳዑዲ መንግሥት አዲስ የኢኮኖሚ ራእይ የኢትዮጵያውያኑን ገቢ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲቀንስ አድርጎታል ብለዋል። ያም ብቻ አይደለም፦ «ወደ ሀገር የሚላክ የነበረውን  የሐዋላ መጠንም ቀንሶታል» ብለዋል። «ምናልባት እዚህ አካባቢ ዜጎቻችን በሕጋዊ መሥመር አይደለም አብዛኛው ሳንቲማቸውን ዝውውር የሚያደርጉት» ያሉት አቶ አብደላ የሐዋላ ዝውውሩም መቀነሱን ጠቁመዋል። 

Saudi-Arabien Abschiebung illegaler äthiopischer Arbeitsmigranten
ምስል DW/S. Shibru

ሌላው የሳዑዲ ዓረቢያ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ  ሀገር ውስጥ የሚረዷቸው ሁለት ልጆቻቸው፣ ባለቤታቸው እና አባታቸው ይገኛሉ። እኚህ አባወራ ላለፉት አራት ዓመታት በሳዑዲ ዓረቢያ ያለሕጋዊ ፈቃድ ይኖራሉ። ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የመጡት በስደት በባሕር ላይ ጉዞ ነው። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት «ጭካኔ የለውም» በሚል ተስፋ ግን እዛው ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ መቆየቱን መርጠዋል። ለዚህ ምክንያታቸው  ደግሞ የዛሬ አራት ዓመት ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ውጡ ሲባሉ በፍቃዳቸው የወጡት ተጎድተው ሳዑዲ ዓረቢያ የቀሩት «እንደአጋጣሚ ምን ችግር የደረሰባቸው የለም፤ እንደውም የሥራ ዕድል ተከፍቶላቸዋል» ብለዋል። ምናልባት ግን ዘንድሮ የሚመጣው አይታወቅም ሲሉም በሳዑዲ ዓረቢያ ያላቸውን ጥሪት ለቃቅመው ከጥቂት ገንዘብ በስተቀር ወደ ሀገር ቤት ልከዋል። 

ከአራት ቀን በፊት ለንባብ የበቃው (The Ethiopian Herald) ድረ-ገጽ የእንግሊዝኛ ዘገባ ሳዑዲ ዓረቢያ ያለፈቃድ የሚኖሩ 83,000 ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሠነድ እንደተሰጣቸው ጠቅሷል። የጊዜ ገደቡ ሊገባደድ በቀረው ጥቂት ጊዜ ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ የሚመለስበት መንገድ ግልጽ አይደለም። 
 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ