የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ውዝግብ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 13 2004ማስታወቂያ
የደቡብ ሱዳን ጦር ከአንድ ሣምንት በላይ በፊት ከያዘው የሱዳን ዋነኛ የሄጅሊጅ የነዳጅ ዘይት ምድር ወይም ደቡብ ሱዳናውያኑ እንደሚጠሩት ከፓንቱ ወታደሮቹን ማስወጣት መቀጠሉን በዛሬው ዕለት አስታወቀ። ይህን የገለጹት የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስትር ባርናባ-ማሪያል-ቤንጃሚን የወታደሮቹ መውጣት ሶሥት ቀናት እንደሚፈጅም አስረድተዋል። የድቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ትናንት የደቡብ ሱዳን ጦር ከሄጅሊጅ እንዲወጣ ትዕዛዝ ያስተላለፉት ከተመድ እና ከአፍሪቃ ህብረት ጦራቸው አካባቢውን እንዲለቅ ግፊት በመጠናከሩ ብቻ ሳይሆን ከሱዳን ጋ ውዝግባቸውን በድርድር መፍታት ለሚቻልበት ዘዴ ዕድል ለመስጠት መሆኑን አስታውቀዉ ነበረ። የወታደሮቹ መውጣት የአሥር ቀኑን ወረራ እንደሚያበቃ ሲገምት የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ደግሞ የሁለቱ ተወዛጋቢ መንግሥታት መሪዎች በቁርጠኝነት ወደ ንግግሩ ጠረጴዛ እንዲመለሱ ጥሪ አድርገዋል። ይሁንና፡ ሱዳን አወዛጋቢውን ግዛት ራስዋ ነፃ ማውጣቷን ነው የገለፀችው። ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ እየተካረረ የመጣው ውጥረት ሁለቱን ሀገሮች ወደለየለት ጦርነት እንዳያመራቸው አስግቶዋል።
አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን