1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ሰላምና የርዳታ አቅርቦቱ

ሰኞ፣ መጋቢት 25 1998

ሱዳንን በሚያዋስነዉ የቻድ ግዛት ግጭት ከተባባሰ ካለፈዉ ጥር ወዲሕ ብቻ ከአዋሳኙ ድንበር አካባቢ ሐምሳ ሺሕ ተጨማሪ ሕዝብ ተፈናቅሏል።

https://p.dw.com/p/E0is

ሱዳንን የሚያብጠዉ ግጭት ከየቤት ንብረቱ ለተፈናቀለዉ ሕዝብ ርዳታ ለማቅረብ የሚደረገዉን ጥረት ማደናቀፉን የተበባሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ ርዳታ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ጃን ኤገላንድ እንዳሉት በተቀናቃኝ ወገኖች መካካል ከሚደረገዉ ግጭት በተጨማሪ በርዳታ ሠራተኞችና ድርጅቶች ላይ የሚደርሰዉ ተደጋጋሚ ጥቃት አንዳድ አካባቢዎች የርዳታ አቅርቦቱን ጨርሶ አሰናክሎታል።ኤገላንድ ሱዳንን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ ሐገራትን በመጎብኘት ላይ ናቸዉ።

ትናንት ጁባ-ደቡባዊ ሱዳን የገቡት የአለም አቀፉ ድርጅት የርዳታ ጉዳይ የበላይ ጄን ኤገላንድ የምደብቃችሁ የለም ነዉ-ያሉት ለጋዜጠኞች።ሥራችን (ርዳታ ማቅረቡ-ማለታቸዉ ነዉ) ተሰናክሏል።»ሱዳን ደቡባዊ ግዛትዋን ያወድም በነበረዉና ምዕራባዊ ግዛትዋን በሚያብጠዉ የርስ-በርስ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝቧ ተገድሏል። ተፈናቅሏል።ወይም ተሰዷል።

የሱዳን ማዕከላዊ መንግሥትና የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ ወይም ጦር (SPLM/A) -በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ ከአመት በፊት ያፀደቁት የሠላም ዉል ሚሊዮኖች የገደለ-ያሰደደ-ያፈናቀለዉን የሃያ አንድ አመት ጦርነት ማስቆሙ እዉነት ነዉ።የሠላም ሥምምነቱ ዛሬም እንደፀና ነዉ።ትናንት ጁባን የጎበኙት ኤገላንድ እንዳሉት የሠላም ሥምምነቱ ከተፈረመ ወዲሕ በመቶ-ሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞችና ተፋናቃዮች ወደየቀያቸዉ ተመልሰዋል።ወይም እየተመለሱ ነዉ።

ወደ ቀድሞ ቀያቸዉ-የተመለሱን፣ በመመለስ ላይ የሚገኙትን ወይም እስካሁን ያልተመለሱትን ለመርዳት ግን አለም አቀፉ ድርጅት ከፍተኛ ችግር ገጥሞቷል።ዋናዉ ኤገላንድ እንዳሉት የፀጥታ ችግር ነዉ።ደቡባዊ ሱዳንን በሚያዋስነዉ የዩጋንዳ ግዛት የመሸገዉ ሎርድ ሪዝታንስ አርሚ የተሰኘዉ አማፂ ቡድን፣ የጎሳ ታጣቂዎችና ሽፍቶች በርዳታ ድርጅቶችና ሠራተኞች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እጅግ ተባብሷል።


«በደቡባዊ ሱዳን ሁኔታዉ እጅግ ተባብሷል።»

የምዕራባዊ ሱዳን ግዛት የዳርፉር ችግር ደግሞ ኤገላንድ እንዳስታወቁት ከደቡብ ሱዳንም የከፋ ነዉ።


«ዳርፉር ደግሞ ሁኔታዉ በፈጥነት እያሽቆለቆለ ነዉ።ሱዳንን በሚያዋስነዉ የቻድ ግዛት ዉጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲሕ እዚያ (ዳርፉር ) ብቻ የነበረዉ ግጭት አካባቢያዊ ባሕሪ ይዟል።እና ስደተኞች ከዳርፉር ወደ ቻድ፣ ከቻድ ወደ ዳርፉር ይሔዳሉ።»

የአንደኛዉን አካባቢ ጦርነትና ግጭት እየሸሸ ወደ ሌላዉ የሚሰደደዉንና በየሐገሩ የሚፈናቀለዉን ሰላማዊ ሕዝብ ለመርዳት አለም አቀፉ ድርጅት የሚያደርገዉን ጥረት አላቋረጠም።ይሁንና ኤገላንድ እንዳሉት በተፋላሚ ወገኖች መካካል ከሚደረገዉ ግጭት እኩል በርዳታ ሠራተኞችና ድርጅት ላይ የሚደርሰዉ ተደጋጋሚ ጥቃት የድርጅቱን ሥራ አዉኮታል።ርዳታ ፈላጊዉንም እየጎዳ ነዉ።

«ባሁኑ ጊዜ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል።ከነዚሕ ሰዎች ጋር የዕለት ከዕለት ግንኙነት የለንም።የተወሰኑን ደግሞ ለብዙ ሳምንታት አላገኘናቸዉም።በዚሕ አካባቢ ያሉትን የነዚሕን ሰዎች ሕይወት ማዳን የምንችለዉ እኛ ነን።ይሁንና በፀጥታ ችግር ምክንያት ሰዎቹ አሉበት መድረስ አልቻልንም።በዚሕም ምክንያት ብዙ ሰዉ ሲሞት እናያለን።»

ሁለት አመት በበለጠዉ የዳርፉር ግጭትና ጦርነት ከሰወስት መቶ ሺሕ በላይ ሕዝብ ተገድሏል።ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈናቅሏል።ወይም ተሰዷል።የአለም ስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ባለፈዉ ሳምንት ሮብ እንዳስታወቀዉ ደግሞ ሱዳንን በሚያዋስነዉ የቻድ ግዛት ግጭት ከተባባሰ ካለፈዉ ጥር ወዲሕ ብቻ ከአዋሳኙ ድንበር አካባቢ ሐምሳ ሺሕ ተጨማሪ ሕዝብ ተፈናቅሏል።