1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት ቀውስ በደቡብ ሱዳን

ሰኞ፣ መጋቢት 5 2008

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን ያለው የሰብዓዊ መብት ይዞታ አሳሳቢ መሆኑን የሚጠቁም ዘገባ አውጥቷል። ዘገባው በአገሪቱ ለሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛው ተጠያቂ ስልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት እንደሆነ ጠቁሟል።

https://p.dw.com/p/1ID17
Südsudan Flüchtlingslager
ምስል Reuters

[No title]

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳንን የሰብዓዊ መብት ይዞታ የፈተሸበት ዘገባ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች በቁማቸው እንደሚቃጠሉ፤ እንስቶችን አስገድደው የሚደፍሩት ተዋጊዎች ድርጊታቸው እንደ አገልግሎታቸው ክፍያ እንደሚቆጠርላቸው አትቷል። ዓለም አቀፉ ድርጅት ደቡብ ሱዳን «በዓለም አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ያለባት» መሆኗንም አስታውቋል። «አስገድዶ መድፈር እንደ አንድ የውጊያ ስልት ጥቅም ላይ እየዋለ» መሆኑን የጠቆመው ዘገባ በአገሪቱ ለሚፈጸሙት ወንጀሎች ዋነኛው ተጠያቂ በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪየር የሚመራው መንግሥት እንደሆነም አትቷል።

.... ከጥቅምት እስከ ጥር ወር ድረስ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ባሰማራቸው ታዛቢዎቹ የሰበሰበውን መረጃ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ይፋ ሲያደርግ በአገሪቱ በሲቪል ዜጎች ላይ የሚፈጸሙት የአስገድዶ መድፈር፤ እንግልት እና ግድያን መሰል አሰቃቂ ድርጊቶች ወደ ጦር ወንጀል ሊያድጉ ይችላሉ ሲል አስጠንቅቋል። የተ... የሰብዓዊ መብቶች አስተባባሪ የሆኑት ዴቪድ ማርሻል የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እና ሰቆቃው በዩኒቲ ግዛት የበረታ መሆኑን ይናገራሉ።

Südsudan Riek Machar Soldaten April 2014
ምስል AFP/Getty Images

«በሲቪል ዜጎች ላይ አስከፊ ሰቆቃ አለ። በበታህሳስ 2013 የተቀሰቀሰውና 2015 የተባባሰው ግጭት በተለይ በዩኒቲ ግዛት የከፋ ነበር። የመንግስቱ የጦር አመራር እና የፖለቲካ አመራር የማፈናቀል፤ የመግደል፤ የመድፈር የማፈን፤ ሲቪል ዜጎች ያላቸውን ሐብት በሙሉ የመዝረፍ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ግፊት አድርገዋል። በዚህም አሰቃቂ ሁኔታ ተፈጥሯል።»

ዘገባው የተ... የጸጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ግብይት ማዕቀብ እንዲጥል ጥቆማ አቅርቧል። በአገሪቱ ለሚታየው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአማራጭ የወንጀለኛ መቅጫ ፍርድ ቤቶች መፍትሔ መፍጠር ካልተቻለ ወደ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ሊመራ እንደሚገባም አሳስቧል።

ባለፈው ሳምንት ይፋ በተደረገው ዘገባ መሰረት ወላጆች ልጆቻቸው ሲደፈሩ እንዲመለከቱ ተገደዋል። በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች፤ የዜጎችን የግል ሐብት እና የቀንድ ከብቶች ስለመዝረፋቸው ህጻናት እና ሴቶችን አስገድደው ስለመድፈራቸው እና አፍነው ስለመውሰዳቸው መረጃ እንዳገኘ የሰብዓዊ መብት ታዛቢ ቡድኑ አስታውቋል።

የተ... የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ኃላፊ ዛይድ ራድ አል-ሑሴይን እንደሚሉት ግን በዘገባው የተካተቱት ወንጀሎች በመላ አገሪቱ ከተፈጸመው ጥቂቱ ብቻ ነው። ታዛቢዎቹ ባልደረሱባቸው የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች የከፋ ድርጊት ሊፈጸም እንደሚችል የጠቆሙት ዛይድ ራድ አል-ሑሴይን የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ግን በተቀረው ዓለም ችላ ተብሏል ሲሉ ተናግረዋል። በተ.. የህጻናት አድን ድርጅት ቃል-አቀባይ ክሪስቶፍ ቦሌራች ሁኔታው እጅጉን አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

«ሁኔታው እጅጉን አሳሳቢ ነው። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት አደጋ ላይ ናቸው። 'የተረሳው አስቸኳይ ሁኔታ' በማለት ለጠራነው ደቡብ ሱዳን ተመሳሳይ እና ከፍ ያለ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።»

Konflikt im Südsudan Flüchtlinge 17.01.2014
ምስል Phil Moore/AFP/Getty Images

የሰብዓዊ መብት ታዛቢ ቡድኑን የመሩት ዴቪድ ማርሻል የመንግስት 'የቀውስ ማሽን' ሊበታተን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። ዴቪድ ከጥቂት ወራት በፊት ከተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቻር ጋር እርቅ ያወረደውን መንግሥት «የሽብር መንግስት» በማለት አምርረው ወቅሰዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናልም 60 ሰዎችን በአንድ የብረት ሳጥን አፍነው በመግደል ወደ ወንዝ ጥለዋል ያላቸውን የደቡብ ሱዳን ወታደሮች በጦር ወንጀል ከሷል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ጥቅምት ወር የመንግስት ወታደሮች ይህን ወንጀል ሲፈጽሙ የተመለከቱ 42 የዓይን ምስክሮችን አነጋግሪያለሁ ብሏል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ