የሰሜን አፍሪቃ ስደተኞችና የላምፓዱዛ ነዋሪዎች
ረቡዕ፣ መጋቢት 21 2003ማስታወቂያ
ሰሞኑን እንኳን ከሊቢያው ጦርነት የሸሹ ወደ 800 መቶ የሚጠጉ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የኤርትራና የሶማሊያ ስደተኞች ላምፔዱዛ ገብተው በተለያዩ አጎራባች ከተሞች ወደ ሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ሰፈሮች ተወስደዋል ። የላምፔዱዛ ነዋሪዎችም ከቱኒዝያው አመፅ ወዲህ ወደ ደሴቲቱ የሚጎርፉ የመንግስት ድጋፍ የማያገኙ ስደተኞችን አቅማቸው በፈቀደው መጠን በሰብአዊነት በመርዳት ላይ ናቸው ። የሊቢያውን ጦርነት በመሸሽ በአደገኛ የጀልባ ጉዞ ተሳክቶላቸው በቅርቡ ኢጣልያ የገቡት ስደተኞች እንደሚሉት ሊቢያ ድንበር ላይ አሁን እንደ ቀድሞው ቁጥጥር የለም ።
በዚህም ምክንያት በህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ነፍሳቸውን ለማዳን ከሊቢያ እየወጡ ነው ። የብዙዎቹ ተስፋም የላምፔዱዛ ደሴት ናት ። ሊቢያ ከ ሶስት ዓመት በፊት ከኢጣልያ ጋር ባደረገችው ስምምነት መሰረት ድንበሯን ስትዘጋ ወደ ደሴቲቱ የሚሰደዱት ቁጥር በ 94 በመቶ ቀንሶ የላምፔዱዛ የስደተኞች መጠለያም ተዘግቶ ነበር ። በቱኒዝያ አንድ ያለው የማግሬብ አገራት ህዝባዊ ንቅናቄ ወደ ግብፅ ብሎም ወደ ሊቢያ ሲሸጋገር ግን ላምፔዱዛ ቀድሞ ከነበረችበት ወደ ባሰ ሁኔታ ተሸጋገረች ። በአሁኑ ሰዓት ደሴቲቱ የደረሱ ስደተኞች ቁጥር ከ 5,486 በላይ ነው ። 20 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ካላት ከላምፔዱዛ ነዋሪዎች በላይ ነው ቁጥራቸው ።
ያም ሆኖ ነዋሪቿ ለነፍሳቸው አድረው የኢጣልያ መንግስት ለስደተኞቹ ማድረግ የተሳነውን እያከናወኑ ነው ። ስደተኞችን ከሚረዱትበበጎ ፈቃደኞች አንዱ ፓውሎ ዲ ቤኔዴቶ ናቸው ። ሶሶት ስደተኞችን አስጠግተዋል ። ግቢያቸውው ውስጥ ስደተኞች እንዲረዱም ፈቅደዋል ።
« በእግዚአብሔር አምናለሁ ። ለዚህም ነው ይህን የማደርገው ። ክርስቲያን ሁሉ ይህን ማድረግ ይችላል ። ጥቂት ፍራሾችን መስጠት እችላለሁ ። ከግቢየ መናፈሻም የተወሰነውን ክፍል እንዲጠለሉበት ፈቅጃለሁ ። ንፁህ ነው ። ለህፃናትም ሆነ ለአዋቂዎች እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ድንኳን መትከል ይቻላል ። »
መንግስት ከአቅሜ በላይ ሆኗል ሲል ዞር ብሎ የማያያቸውን ስደተኞች ነዋሪዎች በቤተ ክርስቲያን በትምህርት ቤትና በልዩ ልዩ አዳራሾችም አስጠልለው እየታደጉዋቸው ነው ።
የአካባቢው ሰበካ ጉባኤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በራሱ ማዕከል ውስጥ አስጠግቷል ። ቪካር ዶን ኣልዶ ራይና እንዳስረዱት ከበጎ ፈቃደኞች አልባሳትም በእርዳታ ይሰበስባሉ ።
«ሰዎቹ እጅግ በጣም ተባባሪዎች ናቸው ። በእውነቱ ያልተጠበቀ ልገሳ ነው ያደረጉት ። በቅርቡ ነው ልብስ መሰብሰብ የጀመርነው ። ከአሁን በኃላ ለሚመጡት በተለይም መጠለያ አጥተው ውጭ ለሚያድሩት ልብስ መስጠት እንችላለን ። »
እንደ ቪካር የስደተኞቹ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉንም እንደሚፈልጉት መርዳት አልቻሉም ። የሚመለከታቸው አካላት በአካል ወደ ስፍራ መጥተው ችግሩን በራሳቸው ቢገነዘቡ ነው የተሻለ ይሆናል እንደርሳቸው
« ምናልባት እዚህ ስለ ሚሆነው መወሰን የሚችሉት ላምፔዱዛ ውስጥ የተወሰኑ ሰዓታት መቆየት ይኖርባቸዋል ። ያን ካደረጉ እዚህ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ በቀላሉ መረዳት በቻሉ ነበር ። »
ስደተኞች በብዛት ይጎርፉብኛል የሚል ስጋት ያደረበት የኢጣልያ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ እርዳታ እየጠየቀ ነው ። የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ አገራቸው የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ እንደሚልኩ ዝተዋል ። ከቱኒዝያው ንቅናቄ አንስቶ እስካሁን ላምፔዱያ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከአስራ ስምንት ሺህ በላይ ነው ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ
ማስታወቂያ