1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳ ጎሣ ጭፍጨፋ ተጠርጣሪ ችሎት በኪጋሊ

ረቡዕ፣ የካቲት 19 2006

በርዋንዳ የጎሣ ጭፍጨፋ ወቅት የግድያ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ተብለው የተጠረጠሩት የቀድሞው የወንጌላዊቷ ጴንጠቆስጤ ቤተ ክርስትያን ቄስ ዣን ቦስኮ ዊኪንዴ ችሎት ዛሬ በመዲናይቱ ኪጋሊ ተጀመረ።

https://p.dw.com/p/1BFks
Jean Bosco Uwinkindi Anklage wegen Völkermord
ምስል Getty Images/AFP

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ፣ « አይ ሲ ሲ » በጎሣ ጭፍጨፋ እና በስብዕና አንፃር ወንጀል ተሳታፊ ነበሩ ባላቸው ዊኪንዴ ላይ የእስር ማዘዣ ያወጣው እአአ በ2001 ዓም ነበር። በ2010 ዓም በዩጋንዳ ተይዘው የታሰሩት ዊኪንዴ የርዋንዳ የጎሣ ጭፍጨፋ ወንጀል ይታይበት ወደነበረው ወደ አሩሻ ታንዛንያ ከተዛወሩ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነበር ፍርድ ቤቱ በ2012 ዓም ለርዋንዳ ያስረካባቸው። ሂልከ ፊሸር የጻፈችውን አርያም ተክሌ እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች።

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ፣ « አይ ሲ ሲ » ከተመሠረተ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገራቸው ባስረከባቸው ርዋንዳዊው ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ዊኪንዴ ላይ አሁን በኪጋሊ ችሎት መጀመሩን የርዋንዳ ዜጋ የሆኑት እና ለጎሣው ጭፍጨፋ ሰለባዎች የሚሟገተው በምሕፃሩ «ሰርፍ» የተባለው ድርጅት ጠበቃ አልበርት ጋሳክ ታሪካዊ ብለውታል።

« የዊኪንዴ ችሎት ወደ ርዋንዳ የተዛወረበት ድርጊት የዊኪንዴ የትውልድ ቦታ በሆነው በቡጊሲራ የጎሣ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑት ሰዎች ፍትሕ ለማግኘት ለሚያካሂዱት ትግል ዕውቅና የሰጠ ርምጃ ነው ብለን እናምናለን። ዊኪንዴ በርዋንዳ ወንጀል ፈፀመዋል። እና የርዋንዳ ህብረተሰብ ምን እንደተፈፀመ እና ፍርድ ቤቱም በተጠርጣሪው አኳያ የጀመረውን ችሎት ሂደት በቀጥታ መከታተል ይችላል። »

Symbolbild Völkermord in Ruanda
ምስል picture-alliance/dpa

እአአ 1994 ዓም በርዋንዳ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊው ነው። በዚያን ወቅት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ወር በነበሩት 100 ቀናት አክራሪ ሁቱዎች ከውሁዳኑ የሀገሪቱ ቱትሲዎች መካከል አንድ ሩቡን እና ብዙ ለዘብተኛ ሁቱዎችን ነበር የጨፈጨፉት። ጭፍጨፋው ካበቃ ከጥቂት ወራት በኋላ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ለጭፍጨፋው ተጠያቂ የሚባሉትን ዓለም አቀፍ ሕግ የጣሱትን ግለሰቦች የሚዳኝ ፍርድ ቤት ማቋቋሙ የሚታወስ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ባለፉት 20 ዓመታት የጎሣውን ጭፍጨፋ ጠንስሰዋል የተባሉ ሚንስትሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት አንፃር ባካሄዳቸው ችሎቶች 44 ጊዜ ብይን ያስተላለፈ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል በርካቶችን በነፃም ለቆዋል። እአአa በ2014 ዓም ስራውን የሚያበቃው የአሩሻው የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት በአሁኑ ጊዜ ፍርድ ቤቱ 17 የይግባኝ ማመልከቻ የቀረበባቸውን ጉዳዮች በመመልከት ላይ ይገኛል።

ጠበቃ አልበርት ጋሳክ የኪጋሊው ችሎት ዊንኪንዴን በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ካላቸው የጎሣው ጭፍጨፋ ሰለባዎች ካሳ ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል በሚል ተስፋ አድርገዋል። ይሁንና፣ በሀምቡርግ ከተማ ያለው የማህበራዊ ምርምር ተቋም ውስጥ ስለ ርዋንዳ ጥናት የሚያካሂዱት ጀርመናዊው ጌርድ ሀንክል ግን የፍርድ ቤቱን ገለልተኝነት ይጠራጠሩታል።

« ፍርድ ቤቱ ለአንድ ወገን ያደላ ነው። ምክንያቱም የአሩሻው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አንዱ ወገን፣ ብሎም ሁቱዎቹ የፈፀሙት ወንጀል ብቻ ነበር የተመለከተው። ሌላኛው ቡድን፣ ማለትም፣ የርዋንዳ አርበኞች ግንባር፣ በምሕፃሩ፣ «አርፒኤፍ» የፈፀመውን ወንጀል ግን በፍፁም ሳያነሳው ነው የቀረው። »

Internationaler Strafgerichtshof für Ruanda in Arusha (Tansania)
ምስል Tony Karumba/AFP/Getty Images

በፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ የተመራውና በቀድሞው ፕሬዚደንት ሀቢያሪማን መንግሥት አንፃር ይዋጋ የነበረው የርዋንዳ አርበኞች ግንባር እአአ በ1994 ዓም ሀገሪቱን ተቆጣጠሮ ጭፍጨፋውን አብቅቶዋል፤ ይሁንና፣ ጭፍጨፋውን ካበቃ ወዲህ በሥልጣን ላይ የሚገኘው የርዋንዳ አርበኞች ግንባር በዚያን ወቅት አስከፊ ጭፍጨፋ አካሂዶዋል በሚል ተወንጅሎዋል። በዚህም የተነሳ ዛሬ በቀድሞውን ቄስ ዣን ቦስኮ ዊኪንዴ አንፃር በኪጋሊ የተጀመረው ችሎት ሂደት ፍትሓዊ መሆኑን እንደሚጠራጠሩት ጌርድ ሀንክል ገልጸዋል። በርዋንዳ በርካታ ችሎቶችን የተከታተሉት ሀንክል የፍርዱ ሂደት በዙ ጊዜ ፍትሓዊ እንዳልነበረ ነው ያመለከቱት። ጠበቃ አልበርት ጋሴንክ ግን የችሎቱ ሂደት ፍትሓዊ እንደሚሆን ነው የገመቱት።

« የርዋንዳ የፍትሕ አውታር ለዚሁ ችሎት ተገቢውን ዝግጅት አድርጓል። ምክንያቱም ዊኪንዴ ወደ ርዋንዳ ከመዛወራቸው በፊት ጀምሮ ነው ብዙ የተሀድሶ ለውጥ ያደረገው። »

የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት የዊኪንዴን ችሎት የሚከታተሉ ታዛቢዎቹን በወቅቱ ወደ ኪጋሊ ልኮዋል።

ሂልከ ፊሸር

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ