1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳ ነጻ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ኃይላት መሪ መታሰር

ቅዳሜ፣ ኅዳር 12 2002

ሁለት የርዋንዳ ተወላጆች በጀርመን የካርልስሩወ ከተማ ባለፈው ማክሰኞ ተይዘው ታሰሩ። እነርሱም ከአንድ ዓመት ወዲህ በጦር ወንጀል የሚፈለጉ በምህጻሩ የኤፍ ዲ ኤል አር የሚባለው የርዋንዳ ነጻ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ኃይላት፡ መሪ ኢግናስ ሙርዋንሺያካ እና ምክትላቸው ሙሶሚ ስትራተን ናቸው።

https://p.dw.com/p/Kc9L
ኢግናስ ሙርዋንሺያካምስል picture-alliance/ dpa

ሙርዋንሺያካ በጀርመን የፖለቲካ ተገን እና የመንግስቱን ከለላ አግኝተው ስለሚኖሩ የፍትሁ አውታር በአንጻራቸው ርምጃ ለመውሰድ አዳጋች ሆኖበት ነበር የቆየው። የጀርመን ዓቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት በተመድ ጥያቄ በሙርዋሺያንካ ላይ በስብዕና አንጻር ወንጀል ፈጽመዋል ሲል ባቀረበው ክስ መሰረት፡ በ2006 ዓም የመጀመሪያ ምርመራ በመጀመር የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ቢቀማም በማስረጃ መጓደል የተነሳ ፈቃዱ እንደገና መስጠት ግድ ነበር የሆነበት። አሁን በአንጻራቸው የተመሰረተው ክስ ሀቅ መሆኑ ከተረጋገጠ፡ ሙርዋሺያንካ እአአ በ 2002 ዓም በጀርመን ሀገር በተዋወቀው በስብዕና አንጻር ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በሚዳኙበት ህግ መሰረት ጉዳያቸው የሚታየው የመጀመሪያው ይሆናሉ። ይሁንና፡ የሙርዋሺያንካን የርዋንዳ ነጻ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ኃይላት መሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ምስክር እዚህ ጀርመን ሀገር አልተገኘም።
ሙርዋንሺያካን እና ምክትላቸው ስትራተንን ለእስር ያበቃቸው ምክንያት ምንድን ነው?

ኢግናስ ሙርዋንሺያካ የጦር እና በስብዕና አንጻር ወንጀል ፈጽመዋል፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸባሪ የተባለውን ድርጅት መርተዋል፡ የኤፍ ዲ ኤል አር ሚሊሺያዎች እአአ ከ ጥር 2008 እስከ ሀምሌ 2009ዓም ድረስ በምስራቃዊ ኮንጎ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሲቭሎችን ገድለዋል፤ በርካታ ሴቶችንም ደፍረዋል፤ መንደሮችን ዘርፈዋል፤ በእሳት አጋይተዋል፤ ያካባቢውን ነዋሪዎችም ከቤት ንብረታቸው አፈናቅለዋል፤ ብዙ ህጻናትንም በግዳጅ ለውጊያው ተግባር መልምለዋል በሚል ነው የተከሰሱት። ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በርዋንዳ ከተካሄደው የጎሳ ጭፍጨፋ በኋላ ወደምስራቅ ኮንጎ በመሸሽ ከዚያ በርዋንዳ አንጻር ውጊያ የሚያካሂደው የኤፍ ዲ ኤል አር መሪ መሆናቸውን በሚሰጡዋቸው ቃለ ምልልስ ይናገራሉ። በዚሁ ቡድን ውስጥ 800,000 የርዋንዳ ቱትሲ ጎሳ አባላትና ለዘብተኛ ሁቱዎች ለተገደሉበት የጎሳ ጭፍጨፋና አሁንም በምስራቅ ኮንጎ ለተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች ተጠያቂ የሚባሉ የሁቱ ሚሊሺያዎች ተጠቃለዋል። በኮንጎ ያማጽያኑ ቡድን የጦር መሳሪያ ትጥቅ የሚፈቱበትን ድርጊት የሚከታተሉት የዓለም ባንክ ባለስልጣን ሀራልድ ሂንከል ኤፍ ዲ ኤል አር በሰላሙ ላይ ትልቅ መሰናክል መሆኑን ገልጸዋል።
« ኤፍ ዲ ኤል አር አሁንም እንደበፊቱ በኮንጎ ካሉት የውጭ ኃይላት ትልቁ የጦር መሳሪያ ትጥቅ ያለው ቡድን ነው። የያዘውም አካባቢ ትልቅ ስፋት ያለው- በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት እንደመሰረተ ነው የሚቆጠረው። የኤፍ ዲ ኤል አር ህልውና ለሁለቱም ሀገሮች የጸጥታ ችግር ደቅኖዋል። አሁንም በየቀኑ በኮንጎ ህዝብ አንጻር የወንጀል ተግባር ይፈጽማል። እና አሁንም እንደበፊቱም ላካባቢው ትልቁን የጸጥታ ስጋት የደቀነ ቡድን ነው። »
የተመድ ኤፍ ዲ ኤል አር ን የጦር መሳሪያ ትጥቁን ማስፈታት ይፈልጋል። በትጥቅ ማስፈታቱና በመልሶ ማዋሃዱ መርሀ ግብር መሰረት የተለያዩ ስልቶችን ይከተላል። በዚህ ዓመት ብቻ በኤፍ ዲ ኤል አር አንጻር የኮንጎ መንግስት ከርዋንዳና ከዩጋንዳ ጋር በመተባበር ሁለት የተለያዩ የጦር ዘመቻዎችን አካሂዶዋል። በዚህ ጥቃትም ከአንድ ሲህ የሚበልጡ የኤፍ ዲ ኤል አር ተዋጊዎች በገዛ ፈቃዳቸው ትጥቃቸውን ፈተዋል። ይህ ግንየተመድ ተጠሪ ብሩኖ ዶናት ንዑሱ ውጤት ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።
« ችግሩ ተራ ወታደሮቹ ከመሪዎቻቸው ትዕዛዝ ካላገኙ በስተቀር ምንም አይንቀሳቀሱም። እናውቃለን -መሪዎቻቸው የሚኖሩት በጀርመን፡ በአውሮጳ ነው። ጠንካራ ተጽዕኖ ነው ያሳረፉት። ይህም ስራችንን አዳጋች አድርጎብናል። በሌላ አነጋገር ትትቅ ለማስፈታት የምንሞክረው ያለነው ኮንጎ ውስጥ መመሪያቸውን ከጀርመን የሚያገኙ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሚሊሺያዎችን ነው። »
ለዚህም ነው የተመድ የኤፍ ዲ ኤል አር መሪዎችን ስልጣን አልባ ለማድረግ ነው የሚጥረው። ይሁንና፡ ሙርዋሺያናካ እና ምክትላቸው ስታንተን በጀርመን የሚኖሩበት ሁኔታ ይህንኑ ጥረቱን አዳጋች አድርጎት ቆይቶዋል። እንደ ተመድ ዘገባ ሁለቱ ተከሳሾች ከማንሃይም ስልክ ምስራቅ ኮንጎ ለሚገኙት የጦር አዛዥ ሲልቬስትር ሙዳኩሙራ በስልክ ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፉና የዘወትር ግንኙነት እንዳላቸው ተደርሶበታል። ድርጅቱ ማስረጃ እንዳለው አስታውቋል። ይህንን የድርጅቱን አባባል ያረጋገጡት ሙዳኩሙራን የተኩት የቀድሞው የጀነራል ፖል ርዋራካቢዠ የሙርዋሺያካ መታሰር ድርጅቱን መሪ አልባ አድርጎ እንዳስቀረው ነው ያስታወቁት።
« ሁኔታው አስቸጋሪ በነበረበት ጊዜ በየሶስቱ ቀን እንነጋገር ነበር። በተረፈ በሳምንት አንዴ። ሁኔታውን እገልጽለት ነበር። እሱ ደግሞ ስለ ፖሊታዊ ዓላማው፡ ስለዕቅዱ ይነግረኝ ነበር፤ እኔም ዕቅዱን በተግባር እተረጉም ነበር። »
ሙርዋሺያንካ ከጀርመን በመሆን የጦር ትዕዛዝ ያስተላልፉ እንደነበር በተሰማበት ድርጊት አንጻር ተቃውሞ ያሰማችው የርዋንዳ ዓቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ሁለቱ ግለሰቦች በስብዕና አንጻር ወንጀል መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማሳየት በነርሱ አንጻር ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ ያወጣው። ሆኖም ጀርመን ግለሰቦቹ በርዋንዳ ትክክለና ፍትህ አያገኙ ይሆናል በሚል ለዚችው ሀገር የማስረከቡን ሁኔታ ከጥያቄ ውጭ መሆኑን አስታውቃ ነበር። የጀርመን ዓቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሁለት ዓመት የፈጀ ምርመራ አድርጎ መረጃ ከሰበሰበ ባኋላ ነው ያሰራቸው። ለውሁዳን ብሄረሰቦች መብት የሚሟገተው የጀርመናውያን ድርጅት ሀላፊ ኡልሪኽ ዴልዩስ ተጠርጣሪዎቹ መታሰራቸውን ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሲጠብቀው የነበረ በመሆኑና ጥፋተኞች ሳይቀጡ እንዳይታለፉ በጀመረው ትግል ላይ የተገኘ ትልቅ ውሳኔ ነው ሲል ርምጃውን አሞግሰዋል።

ተጠርጣሪዎቹም በኮንጎ ከሚንቀሳቀሰው ቡድናቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸውም ዴልዩስ ገልጸዋል።
« አዘውትረው ወደ ኮንጎ ይመላለሱ ነበር። ገንዘብ ለተዋጊዎቻቸው ግንዘብ ይወስዱ እና በሳተላይት ስልክ አማካኝነትም የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸውም መረጃ አግኝተናል። አንዳንዱ የስልክ ግንኙነታቸው ጭፍጨፋ ከመፈጸሙ በፊት መደረጉም ተረጋግጦዋል። እና ይህ ሁሉ ግለሰቦቹ ጭፍጨፋ እና የጦር ወንጀል በማቀዱ ተግባር ላይ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ጥርጣሬ ፈጥሮዋል። »
ጀርመን ተጠርጣሪዎቹን እንድታስረክባት የርዋንዳ ፍላጎት መሆኑን የርዋንዳ ፍትህ ሚንስትር ርሲስ ካሩጋራማ ቢያስታውቁም፡ የኤፍ ዲ ኤል አር መሪና ተከታያቸው ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ፊት እስከቀረቡ ድረስ ችሎቱ የሚደረግበት ቦታ ወሳኝ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
« ጀርመን፡ ሌሎች የአውሮጳ ህብረት ሀገሮችና ሰሜን አሜሪካ በስብዕና አንጻር ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩና በሀገሮቻቸው የሚኖሩትን በማሰር አዲስ ምዕራፍ የከፈቱበት ሁኔታ ተስፋ የሰጠን ርምጃ አድርገን ተመልክተነዋል። »

አርያም ተክሌ
DW/DPA