1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሪዮ ዴጄኔሮዉ ጉባኤና ዉጤቱ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 19 2004

ካለፈዉ ረቡዕ አንስቶ ለሶስት ቀናት ተካሂዶ ዓርብ ዕለት የተጠናቀቀዉ Rio+20 የተሰኘዉ ዘላቂነት ስላለዉ ልማት የሚነጋገረዉ የተመድ ጉባኤ፤ ለአንዳንዶቹ ስኬት ለሌሎቹ ደግሞ ካሰበዉ ያልደረሰ ተደርጎ እየተገለፀ ነዉ። ኤዉ ከ190 በላይ

https://p.dw.com/p/15Lhk
ምስል Reuters

ሀገሮች የተዉጣጡ ተሰብሳቢዎችን አገናኝቶ ማነጋገሩ መልካም ቢባልም በተለይ አፍሪቃ የልቧ አልደረሰም ነዉ የተባለዉ። በአንፃሩ ለዘላቂ ልማት መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች የታዩባቸዉ አንዳንድ ፕሮጀክቶችም በአርአያነት ቀርበዉበታል። ብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ ላይ የተካሄደዉ የተመድ ዘላቂነት ስላለዉ ልማት የሚነጋገረዉ ጉባኤ ሲጠናቀቅ የጉባኤዉ ዋና ጸሐፊ ሻህ ዙካንግ «ይህ ማንንም የማያስደስት ዉጤት ነዉ። የእኔም ሥራ ሁሉንም እኩል አለማስደሰት ነዉ።» ሲሉ ተደምጠዋል፤ Rio + 20 የተሰኘዉ ጉባኤ ዉጤት ማንንም አለማስደሰቱን ሲያመለክቱ።

የዘንድሮዉ Rio + 20 ጉባኤ ቀጣይ ጉባኤዎችን ወልዶ ከመጠናቀቁ በቀር ተሳታፊዎች የጠበቁትና ሊደረስበት የታለመዉ ስምምነት እንዳልተገኘበት ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። ጉባኤዉ ለዘላቂነት ልማት የሚያመቻች የጋራ እቅድ በመንደፍ ለአረንጓዴ ኤኮኖሚ ማበረታታትን እንደዋነኛ ግቡ አቅዶት ነበር። የጉባኤዉ መሪ ፅንሰ ሃሳብም «የወደፊታችን ሊሆን የምንፈልገዉ» የሚል ተስፋ ያዘለ ሆኖ ሳለ ይህ ጉባኤ ግን ከሶስት ቀናት ቆይታዉ በኋላ የዛሬ 20ዓመት ሲካሄድ የተነሳለትን መሠረታዊ ግብ ለማሳካት ከመንገዳገድ ዉጭ የተጨበጠ ነገር አልታየበትም ተብሏል።

Rio+20 Ban Ki-Moon UN Generalsekretär
ምስል REUTERS

ዓለምን የሚያነጋገረዉ የፋይናንስ ቀዉስ ጥላዉን እንዳጠላበት የሚገልፁ ወገኖች ለዘላቂ ልማት ሊደረጉ የሚገባቸዉን ተግባራት በጋራ ለመወሰን የፖለቲካ ፈቃደኝነትን ማገቱን ነዉ የጠቆሙት። በጉዳዩ ላይ ዳግም ከመነጋገር ዉጭ ሌላ ነገር ያልታየበትን አጋጣሚ ከተሰብሳቢዎች አንድ መቶ የሚሆኑት ሀገሮች እንደስኬት ሲያዩት፤ በአንፃሩ ቀጣይ ስብሰባ ብቻ ወልዶ መቋጨቱን የተቹ ወገኖች ደግሞ ክስረት ብለዉታል። ከምንም በላይ በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ በደረሰዉና በሚደርሰዉ ብክለት ለድርቅ እና ረሃብና የተዳረጉት የአፍሪቃ ሀገሮች በዉጤቱ አለመደሰታቸዉ ተገልጿል። በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሀገሮች መሪዎች እንደጀርመን ዩናይትድ ስቴትስ ያሉት ሀገሮች መሪዎች አለመገኘታቸዉን ደግሞ ለአካባቢ ተፈጥሮ ክብካቤ የሚሟገቱ ወገኖች ክፉኛ ተችተዉታል። እንደእነሱ አገላለጽ እነዚህ ወገኖች ለችግሩ ትኩረት አልሰጡም፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ዉስጥ የሚገኘዉ የማኅበራዊ ተቋም ጥምረት ፕሬዝደንት ኒካይሰ ሙሉቢ፤

«ጉባኤዉ የማይቀየር መልኩ ለዉድቀት ተዳርጓል። የተሳታፊዎቹ ሀገሮችን ቁርጠኝነት ያካተተ አሳሪና የጋራ ስምምነት እንደማይኖር ግልፅ ነበር። በዚያ ላይ የደቡብ ሀገሮች ለተፈጥሮ ጥበቃ እንዲያዉሉት የታሰበዉ የገንዘብ ድጋፍም ስምምነትም አልታየበትም። ሌላዉ ቀርቶ የአማዞን አካባቢ እጣ ፈንታ ከፊታቸዉ የተደቀነዉ የኮንጎ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች ብዝሃ-ህይወትም ትኩረት አላገኘም።»

ሌላዋ ናይጀሪያ ዉስጥ የአንድ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፕሬዝደንት የሆኑት ጆይስ ኦጎ ኦጉዋዚ በዉጤቱ ባይደሰቱም የአካባቢ ተፈጥሮን ከመከባከብ አንፃር ሊደረጉ ስለሚችሉ ነገሮች መረጃ አግኝቼበታለሁ ይላሉ፤

Rio+20 Gipfel Umweltaktivisten
ምስል AP

«በሁኔታዉ እኔም አልተደሰትኩም ነገር ግን፤ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሊደረግ ስለሚቻለዉ ሁሉ በርካ መረጃ አግኝቼበታለሁ።»

የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ጊ ሙን ጉባኤዉ በተከፈተ በሁለተኛ ቀኑ በአዉሮጳዉያኑ 2030ዓ,ም የኃይል ምንጭ ለሁሉም እንዲዳረስ የሚል እቅዳቸዉን ለንግድ ተቋማትና ባለወረቶች አቅርበዋል። የተባለዉ እቅድ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ፈላጊ ነዉ። በእቅዱ መሠረት ከሃምሳ በሚበልጡ አፍሪቃ፤ እስያ፤ ላቲን አሜሪካና የደሴት አዳጊ ሀገሮች ዉስጥ የሚኖር 1,3 ቢሊዮን ህዝብ ንፁህና ዉጤታማ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ታልሟል። ባን ዘላቂና ቀጣይነት ያለዉን የኃይል ምንጭ የመጠቀምን ግብ ማሳካት የማይቀር ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል። ይህም አሉ ዋና ጸሐፊዉ ልማት፤ ማኅበራዊ እና የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃን የሚያሰናስል ወርቃማ ድር ነዉ። ይህን ማሳካት ማለት በአየር ብክለት ምክንያት በየዓመቱ የሚከሰትን በሚሊዮን የሚቆጠር የሴቶች እና ህፃናትን ሞት ማስቀረት ነዉ። እቅዱና ዓላማዉ ቢያጓጓም ተወያይ ሀገሮች በየራሳቸዉ ጉዳይ መወጠራቸዉ ወደስምምነት የሚያደርሱ መንገዶችን ዘግቷል።

77 አባል ሀገሮች የተካተቱበት ድሃ ሀገሮችን የሚወክለዉ ቡድን አዉሮጳና ዩናይትድ ስቴትስ ከዛሬ 250ዓመት የምድሪቱን ጥሬ ሃብቶች አሟጠዉ የበሉበትን ታሪካዊ ባለእዳነታቸዉን በማስታወስ የበለፀጉት ሀገሮች በድሃ ሀገሮች የሚታየዉን የአካባቢ ተፈጥሮ ለማሻሻል የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ከዚህም ሌላ የቴክኒዎሎጂ ሽግግሩን በነፃ በማቅረብም አዳጊ ሀገሮች ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ተጠቅመዉ የፀዳ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲፈጥሩ እንዲረዱ ሞግተዋል።

Rio+20 Konferenz 2012
ምስል DW

በተቃራኒዉ የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካን ዛሬ ድሃ የሆኑት ሀገሮች ነገ ቢበለፅጉ ወደዚህ ጉባኤ እንደማይመጡ በማመልከት ለሚያደርጉት ድርድር ታሪክን ለመምዘዝ ወደኋላ ባይመለከቱ መልካም እንደሚሆን አሳስበዋል። በዚህ ጉባኤ ምንም እንኳን በጋራ የተደረሰበት ስምምነት የለም ይባል እንጂ ሀገሮች በተናጠል ባደረጓቸዉ ድርድሮች ስኬት ታይቶባቸዋል። ለምሳሌ ራሷ አሜሪካ እስከየአዉሮጳዉያኑ 2020ዓ,ም ድረስ የደን ጭፍጨፋን ለመታደግ ከአራት መቶ ከሚበልጡ ኩባንያዎች ጥረታቸዉን ለመደገፍ ተዋዉላለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ