የሩዋንዳ ልማት የገንዘብ ተቋም
ሐሙስ፣ ኅዳር 20 2005
የፋይናንስ ሃላፊነቶችን መሸከም ፣ ልማትን በማፋጠን ከልማት እርዳታ ጥገኝነት መላቀቅ ናቸው በእንግሊዘኛው ምህፃር «አጋሲሮ » በመባል የሚታወቀው የመጀመሪያው የሩዋንዳ የልማት ትብብር የገንዘብ ተቋም ግቦች ። ሩዋንዳ ለዚህ ግብ ማስፈፀሚያ የሚውለውን ገንዘብ ለማግኘት የምታስበው ከህዝቡ መዋጮ ነው ። ግን በርግጥ ገንዘቡ በበጎ ፈቃደኝነት ሊገኝ ይችላል ወይ ? በትክክልስ ምን ላይ ይውላል ?
የህዝቧ ቁጥር 10 ሚሊዮን የሚደርሰው በምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ የምትገኘው ሩዋንዳ በህዝብ ብዛት ከተጨናነቁ የአፍሪቃ ሃገሮች አንዷ ናት ። ከህዝቧ ግማሽ ያህሉ ከድህነት ወለል በታች ነው የሚገኘው ። አብዛኛዎቹም የገጠር ነዋሪዎች ናቸው ። «አጋሲሮ »የተባለው የሩዋንዳ ልማት የገንዘብ ተቋም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማገዝ ነው የተመሰረተው ። ባለፈው አመት በነሐሴ በሩዋንዳ መንግሥት የተቋቋመው ይሽው ድርጅት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ይደግፋል ። ለዚህ ፕሮጀክት ድጎማ የሚያደርጉት እጎአ ከ1994 ቱ የሩዋንዳ የርስ በርስ ፍጅት በኋላ ከሃገር ተሰደው በአሁኑ ጊዜ በቤልጂግ በፈረንሳይ ወይም በካናዳ የሚኖሩ ብዙዎች የሩዋንዳ ተወላጆች ናቸው ። በሃገር ውስጥ ያሉ ሃገራቸውን መደገፍ የሚሹ ሩዋንዳውያንም ለዚህ ተቋም አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ በጀርመን የሩዋንዳ አምባሳደር ክርስቲን ንኩሊኪዪና ያስረዳሉ ።
« ይህ በበጎፈቃደኝነት የሚደረግ ነው ፤ እኛም በጎ ፈቃዱ ላይ ነው የምናተኩረው ። ከደሞዝ የሚቆረጥ ወይም እንደ ቀረጥ የሚታይ አይደለም ። ከዚያ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው ምን ያህል እንደሚሰጥ ራሱ የሚወስንበት በበጎ ፈቃድ የሚደረግ መዋጮ ነው ። »
መዋጮው ሩዋንዳውያን ይበልጥ ሃላፊነት እንዲሰማቸውና በሀገራቸው እንዲተማመኑም የሚያደርግ ና የሚያጠነክራቸው ነው ። ሃሳቡ ተቀባይነት በማግኘቱም በመጀመሪያዎቹ 3 ወራት ተቋሙ 23 ሚሊዮን ዩሮ አግኝቷል ። 22 አመታት ጀርመን የኖሩት የሩዋንዳው ስደተኛ ፕሮቪደነ ቱዊሳብ ለተቋሙ ገንዘብ ካዋጡት አንዱ ናቸው ።
« ይህን የገንዘብ ተቋም በደንብ ነው የምደግፈው ። ምክንያቱም ተቋሙ ለሩዋንዳ የፋይናንስ ችግሮች ከመፍትሄም በላይ ነው ብዮ ስለማስብ ነው ። በሃገር ውስጥ እና በውጭ በሚኖሩ ሩዋንዳውያን ላይ አንድ አዲስ ሃሳብ ያጭራል ። ሁል ጊዜ በውጭ እርዳታ ከመመካት ይልቅ ራሳቸውን ችለው የወደፊትን መፃኤ እድል በራሳቸው እንዲወስኑ ያደርጋል ። »
በትጋት ከሚታየው መነሳሳት ጋር ገና ከጅምሩ በመዋጮ የማሰባሰቡ ዘመቻ ላይ ትችቶች እየተሰነዘሩ ነው ። መገናኛ ብዙሃን እንደሚሉት መዋጮው ሁልጊዜም በፈቃደኝነት አይደለም የሚሰጠው ። ሃብታም ሩዋንዳውያን ከገቢያቸው 10 በመቶ እንዲያዋጡ ይጠበቃል ። ከዚህ ሌላ በዚህ መዋጮ የማይሳተፉት የሚገጥማቸው ማህበራዊ ጫናም ከፍተኛ መሆኑን ታዛቢዎች የሚናገሩት ።
« በአንዳንድ ጥቂት ሁኔታዎች መምህራንና ሌሎች ተራ ሠራተኞች ገንዘባቸውና ደሞዛቸው ካለፈቃዳችን ተቆረጠብን ሲሉ ያማርራሉ ። መንግሥትና ባለሥልጣናት እነዚህ ሰዎች በግድ ገንዘብ እንዲያዋጡ ከማድረግ ይልቅ በፈቃዳቸው መዋጮ እንዲሰጡ ማስተማሩ ላይ እንዲተኮር ያደርጋሉ ። »
ሩዋንዳ የውጭ እርዳታ ጥገኛ ናት ። ከበጀትዋ 40 በመቶው የሚሸፈነው ካደጉት አገራት በሚገኝ እርዳታ ነው ። ባለፈው ሐምሌ መጨረሻ ላይ የአውሮፓ ህብረት አሜሪካን ጀርመን ብሪታኒያ ኔዘርላንድስ ና ስዊድን ለሩዋንዳ ከሚሰጡት እርዳታ ከፊሉን አቋርጠዋል ። የዚህም ምክንያቱ በቅርቡ በወጣው የተመድ ዘገባ ሩዋንዳ በምሥራቅ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰውን M23 በመባል የሚጠራውን የኮንጎ አማፅያን ቡድን ትደግፋለች በሚል ነው ። ዘገባው M23 ን ከበሰተጀርባ ሆነው የሚያንቀሳቅሱት የሩዋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ጀምስ ካባርቤ ናቸው ሲልም አመልክቷል ። ሩዋንዳ ግን ክሶቹን አስተባብላለች ። ሩዋንዳ ከአሁኑ የገንዘብ ቅጣቱን እየተቀበለች ነው ። ትንሽቷ አገር ሩዋንዳ ከጀርመን ብቻ 21 ሚሊዮን ዩሮ አጥታለች ። ያም ሆኖ በጀርመን የሩዋንዳ አምባሳደር እንዳሉት የልማት ገንዘብ ማሰባሰቢያው ተቋም በተቋረጠው የውጭ እርዳታ ምክንያት የተጀመረ አይደለም ። የተቋሙን ገንዘብ አሁን የሚቆጣጠረው የሩዋንዳ የገንዘብ ሚኒስቴር ነው ። ይሄ ሃላፊነት በቅርቡ ለገልልተኛ አካል እንደሚሰጥ ተገልጿል
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ