1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞሬኖ ኦካምፖ ስንብት

ሐሙስ፣ ሰኔ 7 2004

እአአ ሐምሌ አንድ 2002 ዓም የተቋቋመው ዴን ኻግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ዋና ዓቃቤ ሕግ አርጀንቲንያዊው ጠበቃ የልዊስ ሞሬኖ ኦካምፖ የሥልጣን ዘመን በዛሬው ዕለት ያበቃል።

https://p.dw.com/p/15Ec5
File -- IN a Feb. 27, 2007 file photo the International Criminal Court's prosecutor Luis Moreno-Ocampo reacts during a press conference in The Hague, Netherlands. In a briefing to the Security Council on Nov. 2, 2011, about Nato in Libya, Moreno-Ocampo said "there are allegations of crimes committed by NATO forces (and) these allegations will be examined impartially and independently." (AP Photo/Peter Dejong/file)
ምስል AP

እአአ ከሰኔ 16 2003 ዓም የዋና ዓቃቤነት ሥራቸውን በይፋ የጀመሩት ኦካምፖ በፍርድ ቤቱ ባገለገሉባቸው ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በአፍሪቃ የጦር ወንጀል ፈፅመዋል ባሉዋቸው ግለሰቦችና የሀገር መሪዎች ላይ ክስ የመሠረቱ ሲሆን፡ ይህ ርምጃቸው ከብዙ አፍሪቃውያን ወቀሳ አፈራርቆባቸዋል።

የዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ ልዊስ ሞሬኖ ኦካምፖ ሥራቸውን ሲጀምሩ በፍርድ ቤቱ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ሁለት ሠራተኞች ብቻ ነበሩ። እና ኦካምፖ ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋ በመሆን የዓቃቤ ጽሕፈት ቤቱን ከሥር ማቋቋም ነበረባቸው። ተሰናባቹ ዋና ዓቃቤ ሕግ ኦካምፖ የመጀመሪያ ጊዜ ችግሮችን ሁሉ አሸንፈው ፍርድ ቤቱ የተነሳበትን ፡ ብሎም የጦር ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረቡን ዓላማ ወደፊት እንዲያራምድ በማድረግ ወሳኝ ሚና በመጫወታቸው እንደሚታወቁ የሂውመን ራይትስ ዎች የዓለም አቀፍ የፍትህ ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ ዠራልዲን ሚቲዮሊ ሴልትነር አመልክተዋል።
« አያሌ ክሶችን በመጀመሩ ረገድ ጉልህ ታታሪነትን አሳይተዋል። እንደሚታወቀው፡ በሰባትአፍሪቃውያት ሀገሮች ውስጥ ምርመራ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፤ በሀያ ሰምንት ሰዎች ላይ፡ በሦስት ርዕሳነ ብሔር፡ ማለትም፣ በሱዳኑ ፕሬዚደንት ኧል በሺር፡ በማቹ የሊቢያ መሪ ሞአመር ጋዳፊ እና በቀድሞው የኮት ዲቯር ፕሬዚደንት ሎውሮ ባግቦ ላይ ጭምር ክስ መሥርተዋል። »
በኦካምፖ ዋና ዓቃቤ ሕግነት ፍርድ ቤቱ እስካሁን በዴሞክራቲክ የኮንጎ ሬፓብሊክ፡ በዩጋንዳ፡ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ፡ በዳርፉር፡ ሱዳን፡ በኬንያ፡ በሊቢያ እና በኮት ዲቯር ተፈፀሙ የተባሉ የጦር ወንጀሎችን በመመርመር ላይ ይገኛል። ከነዚሁ መካከል አራቱ በራሳቸው በአፍሪቃውያቱ ሀገሮች፡ ሁለቱ በተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት፡ አንዱ ደግሞ በዋና ዓቃቤ ሕጉ ነበር ለፍርድ ቤቱ የተጠቆሙት። ክስ ከመሠረቱባቸው ሀያ ስምንት ሰዎች መካከልም የሀያ ሁለቱ እየታየ የሚገኝ ሲሆን፡ በ 19 ሰዎችም ላይ የእሥር ማዘዣ አስተላልፏል።
ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያው ችሎቱ የተመለከተው በሰሜን ምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ኮንጎ የኢቱሪ አካባቢ ሕፃናትን ለውጊያ ተግባር መልምለዋል፡ የጭካኔ ተግባርም እንዲፈፅሙ አስገድደዋል በሚል ባለፈው መጋቢት ወር ጥፋተኝነታቸው በፍርድ ቤት የተረጋገጠባቸውን የጦር ባላባት ቶማስ ሉባንጋን ጉዳይ ነበር። በቅርቡ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቁት ቶማስ ፍርዳቸው ሉባንጋ በሠላሣ ዓመት እሥራት እንዲቀጡ ኦካምፖ በትናንቱ ዕለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። በኦካምፖ ከሻስነት በሉባንጋ አንፃር የመጀመሪያ ችሎት መካሄዱ፡ እንደ ወይዘሮ ዠራልዲን ሚቲዮሊ ሴልትነር አስተያየት፡ የፍርድ ቤቱን ተዓማኒነት በማሳደጉ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
« በመጀመሪያ የሚደረግ ችሎት ትልቅ ትርጓሜ አለው፤ ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ በርግጥ ሥራውን መጀመሩን የሚያሳይ በመሆኑ ብዙ ትኩረት ይስባል። የእሥር ማዘዣ ከማስተላለፍ አልፎ ፍትህ ለማውረድ እየሠራ መሆኑን ያሳያል። የመጀመሪያ ችሎት እንደመሆኑ መጠን ብዙ ጉድለቶች ታይተውበታል። ይህ ብዙ የሚያስገርም አይደለም። በሌሎች ፍርድ ቤቶችም እንደዚሁ ነው። የመጀመሪያው ችሎት ሁሌ ብዙ ሙከራ የተካሄድበት፡ ብዙ ሕጎችም ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋሉበት ነው። ግን የሉባንጋ ችሎት የሞሬኖ ኦካምፖ ጽሕፈት ቤት ሥራውን በማከናወኑ ሂደት ላይ ያጋጠሙትን አንዳንድ ችግሮች አጉልቶዋል። በተለይ በቦታው በመገኘት ምርመራውን የመራበት አሰራሩ፡ ያገኛቸውን መረጃዎች ትክክለኛነት አለማመሳከሩ እና ያዓቃቤ ሕጉ ጽሕፈት ቤት በብዛት ባካባቢ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ ጥገኛ የሆነበት አሠራሩ ከዳኞች ብዙ ነቀፌታ ደርሶበታል። »
ፍርድ ቤት በኬንያ ከ2007ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ 1,200 ሰዎች የተገደሉበትና ከ 60,000 የሚበልጡ በተፈናቀሉበት ግጭት ላይ እጃቸው አለበት በሚል ኦካምፖ ክስ የመሠረቱባቸው አራት ኬንያውያን ባለሥልጣናትን ጉዳይ መመልከቱን ይቀጥላል፤ ምንም እንኳን አንዳንዶች የኦካምፖ ስንብት በተጀመረ የችሎቱ ሂደት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ቢሰጉም። ወይዘሮ ዠራልዲን ሚቲዮሊ ሴልትነር ግንየፍትሑ አውታር ሥራ እንደሚቀጥል ነው ያመለከቱት። ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በተለይ ትኩረቱን ያሳረፈው በአፍሪቃ ላይ ነው በሚል በተለይ ከአፍሪቃውያን ብዙ ወቀሳ ተፈራርቆበታል። የሂውመን ራይትስ ዎች የዓለም አቀፍ የፍትህ ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ ዠራልዲን ሚቲዮሊ ሴልትነር ግን ወቀሳው ትክክለኛ አይደለም ባይ ናቸው።
« አዎ በፍርድ ቤቱ እየታዩ ያሉት ሰባቱ ክሶች ሁሉ የአፍሪቃውን አህጉር የሚመለከቱ ናቸው። ከሰባቱ መካከል አራቱ ለፍርድ ቤቱ የተጠቆሙት በራሳቸው በአፍሪቃውያቱ ሀገሮች መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሥልጣንም የተገደበ መሆኑን ማስታወስም ተገቢ ነው። ፍርድ ቤቱ ርምጃ ሊወስድ የሚችለው የተባለችው ሀገር የፍርድ ቤቱ ምሥረታ ውልን የተቀበለች ስትሆን ብቻ ነው። »
ኦካምፖን የሚተኩት ጋምቢያዊቷ ፋቱ ቤንሱዳ በነገው ዕለት የዓለምዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ሕግነት ሥራቸውን በይፋ ይጀምራሉ።

Congolese warlord Thomas Lubanga sits in the courtroom of the International Criminal Court (ICC) in The Hague, Netherlands, Thursday, Aug. 25, 2011. Prosecution lawyers are wrapping up the ICC's landmark first trial by urging judges to convict a Congolese warlord of recruiting child soldiers and sending them to fight in his country's brutal conflict. Lubanga's trial was the first international case to focus exclusively on child soldiers. (Foto:Michael Kooren, Pool/AP/dapd)
ቶማስ ሉባንጋምስል dapd
2010-07-22 THE HAGUE - The exterior of the International Criminal Tribunal for the former Yugoslavia (ICTY), which is a United Nations court of law dealing with war crimes that took place during the conflicts in the Balkans in the 1990¿s. It is located in The Hague, The Netherlands. ANP XTRA LEX VAN LIESHOUT
ዓ/ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍ/ቤትምስል picture-alliance/ANP XTRA

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ