1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምስራቅ አፍሪቃ ፈጣን ጣልቃ ገብ ጦርና እና ተግዳሮቱ

ሰኞ፣ ነሐሴ 19 2006

በመጪው ዓመት በታህሳስ ወር ሥራውን እንደሚጀምር የተነገረው «የምስራቅ አፍሪቃ ፈጣን ጣልቃ ገብ ጦር » ሰላም እና መረጋጋት በራቃቸው የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ወታደሮችን እያሰማራ አፋጣኝ ርዳታ ለመስጠት አቅዷል።

https://p.dw.com/p/1D0th
Bildergalerie Somalia Sicherheitslage Kind und Soldat 2013
ምስል STUART PRICE/AFP/Getty Images

የምስራቅ አፍሪቃ አገራት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ባለፈው ዓርብ እንዳስታወቁት የምስራቅ አፍሪቃ ፈጣን ጣልቃ ገብ ጦር ከመጪው ታህሳስ ወር አንስቶ ዝግጁ ይሆናል።ጦሩ ከ10 አገራት ማለትም ከሶማሊያን ከሩዋንዳ፣ ከብሩንዲ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ከዩጋንዳ ፣ ከሲሸልስ፣ ከኮሞሮስ፣ ከጅቡቲ እና ከሱዳን የሚውጣጣ ሲሆን ከነዚሁ ሃገራት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኝም ተገልጿል።«ይህ በተለይ በግጭት ጊዜ ጣልቃ የሚገባ እና የግጭት ቦታዎችን የሚያረጋጋ ኃይል ለመፍጠር በምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት የተደረገ ጥረት ነው። እቅዱ ላለፉት 15 ዓመታት በሂደት ላይ ነበር። እንደሚመስለኝ የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ይህንን ፈጣን ጣልቃ ገብ ጦር በመመስረቱ ረገድ ትልቅ መሻሻል አሳይተዋል።»

ይላሉ ረሺድ አብዲ- የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ። የፈጣን ጣልቃ ገቡን ጦር አላማ ያወደሱት አብዲ ጦሩ ብዙ ሰራዊት እንደሚያሻውም ሳያነሱ አላለፉም። ከ10 ሀገራቱ የሚውጣጡት ወታደሮች ቁጥር 5000 ብቻ ነው።« ይህ እጅግ አነስተኛ ኃይል ነው። በደቡብ ሱዳንም ሆነ በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች ማሟላት አይችልም። ምሳሌ ለመስጠት ያህል እንኳን በሶማሊያ ያለው የአሚሶም ጦር ከ 22 ሺ በላይ ነው ። ይህ በግልፅ እንደሚያሳየው ሶማሊያ ያለው ብቻ ነው ። ይህ መስፈርቶቹ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆኑ ያሳያል።እና ይህ ለወደፊቱ ከወዲሁ ተዘጋጅቶ የተቀመጠ ጥሩ ነገር ይመስለኛል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን መደረስ የነበረበት ላይ ደርሰናል ለማለት ያዳግታል፤ በርግጠኝነት ተጨማሪ ኃይል ያስፈልገናል።»

Offensive der AMISOM
ምስል AP

የምስራቅ አፍሪቃ ፈጣን ጣልቃ ገብ ጦርን ዕውን ለማድረግ በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውታል። በተለይ የገንዘብ ችግር። እንደዚህ አይነት ጦር ለመመስረት በቂ ገንዘብ ያሻል ይላሉ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ አብዲ « በታሪክ አፍሪቃ የሚያስፈልጋትን የፀጥታ ጥበቃ ጉዳዮች በአመዛኙ በገንዘብ ችግር ምክንያት በራሷ አሟልታ አታውቅም ። በቅርቡ በምዕራብ አፍሪቃ የሆነውን ስንመለከት ፈረንሳይ ወታደሮቿን ወደ ማሊ መላክ የነበረባትን ጊዜ መጥቀስ እንችላለን። ይህ የአፍሪቃ ሀገራት በግልፅ ዘላቂና አስተማማኝ የገንዘብ ማግኛ መንገድ በመፍጠር ረገድ ወደ ኃላ እንደቀሩ ያመላክታል።»

ይሁንና ይላሉ ራሺድ አብዲ የምስራቅ አፍሪቃ ፈጣን ጣልቃ ገብ ጦር ወደፊት ከ5 እስከ 10 ዓመታት በቂ መዋጮ ሊያገኝ ይችላል። ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ አድርገው የጠቀሱትም ዮናይትድ ስቴትስን እና የአውሮፓ ህብረትን ነው ። ሮይተርስ ዜና ወኪል ባወጣው ዜና ላይ የምስራቅ አፍሪቃ ፈጣን ጣልቃ ገብ ጦር በእቅዱ መሰረት ከህዳር ወር አንስቶ የጋራ ወታደራዊ ልምምድና ስልጠና የሚያደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የሚኖራትን ጉልህ ሚና ራሺድ አብዲ እንደሚከተለው አስረድተዋል።

Infografik AMISOM Mission der Afrikanischen Union in Somalia

« የኢትዮጵያ ሚና እጅጉን ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ቀንድ የላቀ የጦር ኃይል ያላት ሃገር ናት ። የተባባሰ የግጭት ማዕከላት በነበሩት በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሌሎችም ቦታዎች፤ በቂ ተሞክሮዎች አሏት። እንዲሁም ሙያዊ ብቃት ያለው ጦር አላት። እና ኢትዮጲያ ብዙ አስተዋፅዎ ልታደርግ የምትችልበት አቅም አላት ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊም ይሁን የጦር አቅሟን ተጠቅማ የበኩሏን ሚና መጫወቷ አዲስ ነገር አይደለም ።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ