1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የምላዲች ግፍ፤ ፍትሕ እና ሰርቦች  

ረቡዕ፣ ኅዳር 13 2010

ሐምሌ 1995።ስሬብሬንሳ።በከፊል ኦና ናት።ራትኮ ምላዲች የሚያዙት ጦር ተቆጣጠራት።የዘመኑን ዘመናይ ታንክ፤መድፍ መትረየስ የታጠቀዉ  ጦር ከተማይቱን መቆጣጠሩ ለሰርቦች ከፍተኛ ድል፤ ለምላዲች ታላቅ ምርኮ ነበር።«ጨዋዉ፤ ምስጉኑ» የጦር መሪ ድብቅ ዓላማቸዉን መደበቅ አልቻሉም።

https://p.dw.com/p/2o4pq
Bosnien Herzegowina eine bosnische Frau reagiert in Potocari auf das Urteil von Ratko Mladic in Den Haag
ምስል Reuters/D. Ruvic

Mladic Urteil - MP3-Stereo

የቀድሞዉ የቦስኒያ ሰርብ የጦር አዛዥ ጄኔራል ራትኮ ምላዲች በዘር ማጥፋት እና በጦር ወንጀለኝነት የእድሜ ልክ እስራት ተበየናባቸዉ።ምላዲች እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1990ዎቹ ቦስኒያ ሔርሶ ጎቪና በተደረገዉ ጦርነት በብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ ሠላማዊ ሙስሊሞች መጨፍጨፍ ተጠያቂ ተደርገዉ ተከሰዉ ሲሟገቱ ነበር።ዘ ሔግ-ኔዘርላንድስ ያስቻለዉ ፍርድ ቤት ዛሬ ያሳለፈዉ ፍርድ ለፍትሕ ፈላጊዎች የፍትሕ ልዕልና ለሰርቦች ግን ፀረ-ሰርብ ፍርድ ነዉ።ስርድያን ጎቤዳሪካ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ምሥራቅ ቦስኒያ ዉስጥ ተወለዱ።።1942 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) በ23 ዓመታቸዉ የያኔዋ የይጎዝላቪያ ሕዝባዊ ጦር አባል ሆኑ።ጎበዝ ወታደር፤ ጨዋ መኮንን፤ ቆፍጣና የጦር መሪ እየተባሉ ካንዱ ማዕረግ ወደሌላዉ በፍጥነት እያደጉ በመካከለኛ ዕድሜያቸዉ ከፍተኛዉን ማዕረግ ለጠፉ።ጄኔራል።ራትኮ ምላዲች።በ1992 በቦስኒያ የሰርብ ጦር አዛዥነትን በተረከቡ ማግስት ቦስኒያን የሚያነደዉን ጦርነት እንደአዛዥ ያግፈጠፍጡት ገቡ።
ሐምሌ 1995።ስሬብሬንሳ።በከፊል ኦና ናት።ራትኮ ምላዲች የሚያዙት ጦር ተቆጣጠራት።የዘመኑን ዘመናይ ታንክ፤መድፍ መትረየስ የታጠቀዉ  ጦር ከተማይቱን መቆጣጠሩ ለሰርቦች ከፍተኛ ድል፤ ለምላዲች ታላቅ ምርኮ ነበር።«ጨዋዉ፤ ምስጉኑ» የጦር መሪ ድብቅ ዓላማቸዉን መደበቅ አልቻሉም።
                                         
«በመጨረሻ፤ በዚሕ አካባቢ የሚገኙ ቱርኮችን የምንበቀልበት ጊዜ ደረሰ» አሉ ጄኔራሉ።ቱርኮች ያሏቸዉ ሙስሊም ቦስኒያዎችን ነበር።ከሙስሊምእነታቸዉ ሌላ ልክ እንደ ጄኔራሉ የይጎዝላቪያ ዜጋ-የቦስኒያ ተወላጆች ናቸዉ።ጄኔራሉ «ብቀላ» ያሉትን ዘመቻ ቀጠሉ።ከ13 ዓመት ታዳጊ ወጣት እስከ 94 ዓመት አዛዉት የሚገኝ 8ሺሕ ሙስሊም ወንድ እየታደነ፤ ታሰረ፤ተደበደበ፤ ተገደለ።ሴቶች ተደፈሩ።ተገረፉ።ተሰደዱ።ኔድዣድ አቬዲች አንዱ ነዉ።
                                
«ይሕ የመግደያ ሥፍራ ነበር።ሐምሌ 14 ሌሊት 1995 ወደዚሕ አመጡኝ።እዚሕ በጥይት ደበደቡኝ።»
አቬዲች ያኔ 17 ዓመቱ ነበር።ምላዲች ግፉ ከዋሉባቸዉ ብዙ ሺዎች አንዱ ነዉ።ስሬብሬንሳ ምላዲጅ ጦር እጅ ስትወድቅ ወደ ጫካ ለማምለጥ ሞክሮ ነበር።ሰርቦች ያዙት አሰሩት፤ ገረፉት በስተመጨረሻ ከብዙ ብጤዎቹ ጋር ወደ መገደያዉ ሥፍራ ነዱት።መሬት ላይ አስተኙት።
                                     
«ተኩሶብን።የቀኝ ሆዴን፤ክንዴን እና ግራ እግሬን ተመታሁ።በአስከሬን ተከበብኩ።ሞቴን ተመኘሁ።»ግን አልሞተም።እስኪጨልም ጠብቆ እንደሱ ነብሳቸዉ በትዓምር ከተረፈች ብጤዎቹ ጋር እየተጎተተ ቅርብ ከሚገኝ ጉባታ ጢሻ ዉስጥ ተሸሸገ።«በማግስቱ ቁልቁል ስመለከት ማታ የሸሸሑት መስክ በደም፤ አካል፤ ጨርቅ ጎድፎ አየሁት።«ሰዉ ምንም ምክንያት ሳይኖረዉ እሱን መሰሉ ሰዉ ላይ የሚጨክነዉ ለምንድነዉ? እያልኩ አሰብኩ» ይላል የዛሬዉ ጎልማሳ።ፍልስፍና ብጤ ጀመረ የያኔዉ ወጣት።
የራትኮ ምላዲች ልጅ ዳርኮ ምላዲች ግን የአባታቸዉን ወንጀል አይቀበሉትም። የ48 ዓመቱ የኮምፒዉተር ባለሙያ እንደሚሉት አባታቸዉ እንደወታደር ትዕዛዝ-ነዉ የፈፀሙት።
                               
«ምንም አይነት ወንጀል እንዲፈፀም አላዘዘም።እንደ ወታደር  በታቸለዉ መጠን በሥርዓት ነዉ የተወጣዉ።በቅጡ ካልሰለጠኑ ፋኖዎች ይልቅ እሱ እንደዚያ ዓይነት ሥልጣን ላይ በመኖሩ ቦስኒያዎች ራሳቸዉም እድለኞች ናቸዉ።አለበለዚያ ጦርነቱ ከደረሰዉ የከፋ ደም አፋሳሽ ይሆን ነበር።» 
ሌሎች ብዙ ሰርቦችም ምላዲችን እንደ ብሔራዊ ጀግና ነዉ የሚቆጥሯቸዉ። ዘሔግ-የሚያስችለዉን ፍርድ ቤትም ፀረ-ሰርብ አድርገዉ ያዩታል።አቬዲች ግን ሰርቦችን «ለምን ትዋሻላችሁ» ይጠይቃል።
ፍርድ ቤቱ ጄኔራሉን ከስሬብሬንሳዉ ጭፍጨፋ በተጨማሪ ሳርዬቮን አስከብበዉ ከ10 ሺሕ በላይ ሕዝብ ማስጨረሳቸዉን  አረጋግጦ-እነሆ ዛሬ ፈረደባቸዉ። ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ሰርጌ ብራሜርትስ ፍርዱን ለዓለም አቀፍ ፍትሕ የማዕዘን ድጋይ ብለዉታል።የሰርብ ጠቅላይ ሚንስትር አና ብራናቢች ያለፈዉን እንርሳዉ።

Niederlande Urteil Ratko Mladic | Demo
ምስል picture-alliance/AP Photo/P. Nijhuis
Niederlande Urteil Ratko Mladic | Fernsehübertragung
ምስል picture-alliance/AA/n: Ibrahimkadic

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ