1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ

ቅዳሜ፣ የካቲት 12 2008

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በ2013 ዓም ከስልጣን የተወገዱት የቀድሞው ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜ ጠቅላይ ሚንስትር የነበረበት ፎስተ አርሾንዥ ቱዋዴራ ሳያሸንፉ እንዳልቀሩ የምርጫ ውጤቶች አሳይተዋል።

https://p.dw.com/p/1Hz3P
Zentralafrika Wahlen
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

[No title]

ይሁንና፣ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋውን እና ወደ 500,000 ሰዎችን ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሸሹ ያደረገውን ካለፉት ሶስት ዓመታት ገደማ ወዲህ በሙስሊሞቹ የሴሌካ ዓማፅያን እና በክርስትያኖቹ የፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች መካከል የቀጠለውን ቀውስ አብቅቶ በሀገሪቱ እንደገና ሰላም ያወርዳል ተብሎ የተጠበቀው እና ባለፈው እሁድ የተካሄደው የመለያ ምርጫ ተጭበርብሮዋል የሚሉት በመጀመሪያው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸንፈው የነበሩት በቀድሞው ፕሬዚደንት ፌሊክስ አንዥ ፓታሴ አመራር እጎአ ከ1999 እስከ 2001 ዓም ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት የቱዋዴራ ተፎካካሪ አኒሴት ዦርዥ ዶሎገሌ የውጤቱን ትክክለኛነት አጠያይቀዋል።
ቀጣዩ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ይሆናሉ የሚባሉት ፎስተ አርሾንዥ ቱዋዴራ ለመለያ ምርጫ መድረሳቸው ራሱ ብዙዎችን አስገርሞዋል። ምንም እንኳን የቀድሞው ፕሬዚደንት ቦዚዜ ጠንካራ ድጋፍቸውን ቀደም ሲል ከራሳቸው ጋር ህብረት ለፈጠሩት ዶሉገሌ ቢሰጡም፣ ቱዋዴራ የብዙውን መራጭ ድምፅ ላገኙበት በጠቅላይ ሚንስትርነት ዘመናቸው ያስመዘገቡት ውጤት እንዳለው የፖለቲካ ተንታኝ ኒክ ሎንግ ሚና ይናገራሉ።
« በመጀመሪያ ደረጃ ቱዋዴራ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተሸንፈው ከምርጫው በወጡት የራሳቸው አካባቢ እና ጎሳ ድጋፍ የነበራቸው ሌሎቹ ፕሬዚደንታዊ እጩዎች ዘንድ ከዶሎገሌ የተሻለ ተቀባይነት አግኝተዋል፣ የቀድሞው ገዢ ፓርቲ ክዋናካ ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ቱዋዴራ በምርጫ ዘመቻው ወቅት የብዙዎቹን የመንግሥት ሰራተኞች እና ተከታዮቻቸውን ድጋፍ ሊያተርፉ ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከ2008 እስከ 2013 ዓም ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ባገለገሉባቸው አምስት ዓመታት የሲቭል ሰራተኞች ደሞዝ እንዲከፈል አድርገዋል። እርግጥ፣ ዶሎገሌ፣ የሰራተኛው ቁጥር 24,000 ብቻ ነበር በሚል አስተናንሰዋል። ይሁንና፣ በመልካም አስተዳደር ጉድለት በምትታወቀዋ በዚችው ሀገር ለመንግሥት ሰራተኞች ደሞዝ መክፈላቸውል መቻላቸው ሊካድ የማይችል ጥሩ ድርጊት ነው። እና ይህ ተግባራቸው ቱዋዴራን የተሻሉ ፕሬዚደንት ያደርጋቸዋል የሚል አስተያየት አትርፎላቸዋል።»
Zentralafrikanische Republik UN Soldaten
የተመድ ወታደሮችምስል Getty Images/AFP/M. Longari
በዚያም ሆነ ቱዋዴራ እና ዶሎገሌ እርስ በርስ መወቃቀሳቸውን ትተው በመላ ሀገሪቱ፣ በተለይም፣ የ2013 ዓም ዓመፅ በተጀመረበት በብዛት ሙስሊሞች በሚኖሩበት ኋላ ቀር በሚባለው በሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢ መረጋጋት ለማውረድ እና ሀገራቸውን መልሰው በመገንባቱ ተግባር ተባብረው ለመስራት ቢሞክሩ መልካም እንደሚሆን «ቻተም ሀውስ» የተባለው ለንደን የሚገኘው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ፖል ሜሊ አስታውቀዋል።
«በመጀመሪያ፣ ሰላም እና እርቀ ሰላም ለማውረድ የተነቃቃውን ሂደት ወደፊት ማራመድ አለባቸው። ምክንያቱም፣ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት የተካሄደው ውዝግብ በዚችው የሀይማኖት ግጭት ታሪክ ባልነበረባት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ህበረተሰብ ውስጥ ስር የሰደደ ልዩነት ፈጥሮዋል። ይህ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታየው አለመረጋጋት ባንዳንድ አካባቢዎች በሀገሪቱ የክርስትያን እና የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል አለመተማመን እና አልፎ አልፎም ጥላቻ ፈጥሮዋል። እና እነዚህን ልዩነቶች ማስወገደ እና የጥላቻን አስተሳሰብ ማብቃት አዳጋች ነው የሚሆነው።»
ቀጣዩ የማዕከላይ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ይሆናሉ የሚባሉት ቱዋዴራ የሙስሊሞቹ እጩ የነበሩት የየካሪም ሜካሱዋ ን ድጋፍ ማግኘታቸው ሀገሪቱን የሚጠብቃትን የእርቀ ሰላም የማውረዱን ተግባር ለማራመድ እንደሚረዳቸው ጥሩ ቅድመ ግዴታ ታይቶዋል። በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱትን የታጠቁ ቡድኖች የጦር መሳሪያ የማስፈታቱ ተግባር አዝጋሚ በመሆኑ፣ እንደ ፖል ሜሊ አስተያየት፣ የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ አሁንም ገና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።
«ፀጥታ የማስጠበቁ ተግባር በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ላይ ጥገኛ ይሆናል። የጦር መሳሪያ የታጠቁትን ቡድኖች ትጥቃ የማስፈታትና ወደ መደበኛው ኑሮ የመመለስ ግዙፍ ስራ ይጠብቀዋል። በዝርፊያ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩትን መሳሪያ ያነገቱ ወጣቶችን ከዚሁ ኑሯቸው እንዲለያዩ ማግባባቱ በጣም አዳጋች ነው የሚሆነው።»
አርያም ተክሌ
ማንተጋፍቶት ስለሺ