1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ አውታሮች አጠቃቀም ስነምግባር

ዓርብ፣ የካቲት 15 2005

እንደ ፌስቡክ ባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፎች አንዳንዶች የቤተሰባቸውን ሀዘን ጭምር ድንገት የሚረዱበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ከስነምግባር ውጪ የሆኑ አፀያፊ ምስሎችና ፅሁፎችም እንዳሻቸው ይወጣሉ፣ ሌላም ሌላም። የኢንተርኔት አጠቃቀም ስነምግባር እስከምን ድረስ መሆን አለበት?

https://p.dw.com/p/17jfu
ምስል Fotolia/MH

የመናገር እና የመፃፍ ነፃነት መቼም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ መግባት የማይገባው ተፈጥሯዊ መብት መሆኑ ሀቅ ነው። ይህ ሲባል ታዲያ ለዕይታ የምናበቃቸው ፅሑፎች፣ ምስሎች ብሎም ማናቸውም ነገሮች ስነምግባርን የተከተሉ መሆናቸውን ባለመዘንጋት ነው። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅታችን የምናተኩርበት ጉዳይ ነው። በማኅበራዊ አውታሮች በንቃት የሚሳተፍ ወጣት እና የዩኒቨርሲቲ ምሁር ጋብዘናል፤ አብራችሁን ቆዩ።

የኢንተርኔቱ ዓለም መሬት ላይ የምናስተውለው የዕለት ተዕለት ክስተት ነፀብራቅ ነው ቢባል የሚያከራክር አይመስለኝም። በእርግጥ የገሀዱ ዓለም ክስተት ማጠንጠኛው ይፋዊ አለያም ግላዊ ሊሆን ይችላል። በዚህም አለ በዚያ ግን በኢንተርኔትም ሆነ በማንኛውም መንገድ ክስተቱ የሚገለፅበት መንገድ ምን ያህል በስነምግባር መቃኘት ይኖርበታል? ወጣት ዳንኤል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጥበባት ኮሌጅ የቴአትር ክፍል ውስጥ ኮሚኒኬሽን ያስተምራል፤ ለጥያቄው መልስ አለው።

ወጣት ዳንኤል ከዚያም ባሻገር አፀያፊ ቃላቶችንና ምስሎችን መጠቀም እንደማይገባን በመጥቀስ መረጃዎችን ማኅበራዊ አውታሮች ላይ ስናስቀምጥ ሌሎችን በማይጋፋ መልኩ መሆን እንዳለበት ይገልፃል። ወጣት በፍቃዱ በበኩሉ አንዳች ነገር ለእይታ ወይንም ለንባብ ወደ ኢንተርኔቱ ዓለም ይዞ ብቅ ከማለቱ አስቀድሞ ምን አይነት ጥንቃቄ እንደሚያደርግ በዚህ መልኩ ይገልፃል።

የማኅበራዊ አውታሮች በከፊል
የማኅበራዊ አውታሮች በከፊል

ስነምግባር ላይ ያተኮረ ጥንቃቄ ማድረግ ሲባል ግን ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ባህልን የመግደል ግላዊ ሳንሱር እንዳልሆነ ወጣቱ አፅንኦት ይሰጥበታል።

በእርግጥም ይህን ዝግጅት ለማሰናዳት አስተያየታቸውን እንዲገልፁልኝ የጠየቅኳቸው በርካታ ወጣቶች በተለያየ ምክንያት ለቃለ-መጠይቁ ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ገልፀውልኛል። ወጣቶቹ በማኅበራዊ አውታሮች ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ መሆናቸው ደግሞ ነገሩን የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል።

የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ወጣት ዳንኤል የአስተሳሰብ ልዩነት ይዞ መወያየቱ ለእድገት ወሳኝ መሆኑን ይጠቅሳል። ዳንኤል ስነምግባር ላይ ትኩረት አድርገን የአስተሳሰብ ፍጭትን እናበረታታ ሲል፤ የማኅበራዊ አውታሮች ንቁ ተሳታፊው ወጣት በፍቃዱ በበኩሉ ወጣቶች ከግል ሳንሱር ወጥተው ስነምግባርን የተከተለ የንግግር ባህልን እንዲያዳብሩ ጥሪ ያስተላልፋል።

የማኅበራዊ አውታሮች አጠቃቀም ስነምግባር እስከምን ድረስ መሆን አለበት? በሚል ርዕስ ሁለት ወጣቶችን አነጋግረን ያሰናዳንላችሁ የወጣቶች ዓለም ጥንቅር በዚህ ይጠናቀቃል። በጉዳዩ ዙሪያ ድረ-ገፃችን ላይ አስተያየት በመስጠት ለተሳተፋችሁ በሙሉ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ። ሙሉውን ዝግጅት ለማድመጥ ከታች የሚታየውን የድምፅ ማጫወቻ ይጠቁሙ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ