1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አድዋ-የኢትዮጵያ አንድነት እና የዘውጌ ፖለቲካ አቀንቃኞቹ ጥልቅ ልዩነት ማሳያ?

ዓርብ፣ የካቲት 24 2009

የአድዋ ድል 121ኛ አመት ሲከበር የታሪክ አተናተኑ እና የንጉሰ ነገስት ምኒሊክ ተክለ-ስብዓና የኢትዮጵያ አንድነት እና የዘውጌ ፖለቲካ አቀንቃኞችን በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሲያተጋትግ ከርሟል።

https://p.dw.com/p/2YcQ5
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ትናንት ታኅሳስ 23 ቀን 2003 ዓ.ም. የዓድዋ ድል ለ121ኛ ጊዜ ሲከበር እንዲህ በወጣቶች ፉከራ ደምቆ ነበር። ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጩ ምስሎች ይኸንንው አሳይተዋል። በዕለቱ የኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ታምቦ ምቤኪ ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር ዓድዋ ላይ ነበሩ። የበዓሉን አከባበር ችላ ብሏል እየተባለ የሚተቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ዓድዋ ላይ እገነባዋለሁ ያለውን ግን ደግ ሞ ታቅዶ የተዘነጋው የፓን አፍሪካን ሙዚየም ኃሳብ ሆኖ እንደማይቀር ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ከአዲስ አበባ 809 ኪ.ሜትር ተጉዘው ባደረጉት ንግግር የዓድዋ ድል «የአንድነት እና የመተባበር ውጤት ነው።» ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ «የአንድነት እና የመተባበር ውጤት ነው።» ይበሉ እንጂ ለማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን አወዛጋቢ ርዕሰ-ጉዳይ ሆኖ ከርሟል። የፖለቲካ አቀንቃኙ ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳ ዓድዋ የጥቁር ሕዝብን ነፃነት ለመጠበቅ የተደረገ የጥቁር ሕዝብ ጦርነት አድርጎ ማክበር ስህተት ነው ሲል ይተቻል። መኖሪያውን በአውስትራሊያ ያደረገው ዶ/ር ጸጋዬ በፌስ ቡክ ማኅበራዊ ድረ-ገጹ ባሰፈረው ሽንጠ ረዥም ፅሁፍ «ዓድዋን ለማክበር ትክክለኛ ምክንያቶች አሉ።» ይበል እንጂ በዓድዋ ታሪክ ትንታኔ ፈፅሞ እንደማይስማማ ይተቻል። እንደ ዶ/ር ጸጋዬ አባባል ዓድዋ በቅኝ ገዢዎች መካከል የተደረገ ፍልሚያ ነው። «ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ነው ብሎ ማለት ታሪካዊ እውነትን ማዛነፍ ነው» የሚለው ዶ/ር ፀጋዬ ዓድዋ ላይ የአፍሪቃን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ መስዋዕት የሆኑትን መዘከር ተገቢ መሆኑን ግን አስፍሯል። 

ሰይናቴ እሸቴ በበኩሏ «ዓድዋ አንድ ድል ብቻ አይደለም፡፡ ዓድዋ የጥቁሮች ድል ብቻም አይደለም። ይልቁንም የሰውን ልጅ ሰው አይገዛም ሲል የሰውን ተፈጥሯዊ ባሕሪ፣ ያልገዛም ባይነትን ስሜት ያስመሰከረ ጠላትን ቪቫ ምኒሊክ፤ ቪቫ ጣይቱ ብሎ ያስዘመረ ጀግንነት ነው፡፡ ጠላትን ለማወደስ አፍን ያስከፈተ አውሮፓዊያን በውዴታ ግዴታ ልጃቸውን ምኒልክ ብለው እንዲሰየሙ ያስገደደ ሽህ ምንተሸህ ድል ነው ዓድዋ! የማይነጥፍ የድል ዛፍ የማያልፈው የታሪክ መንገድ ዓድዋ….» ስትል ኃሳቧን ገልጣለች። 

Äthiopien Addis Abeba Annual national celebrations Adwa Victoy
ምስል Abel Wabella

የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ «ይህ በድል መንፈስ፣ በእልልታ ብቻ ሳይሆን በአርምሞም ጭምር የሚከበር ቀን ነው።» ብሏል ስለ ዓድዋ በፃፈው የፌስቡክ ፅሁፍ።

«የራስ ክብር ቀን ነው። የአገር ክብር ቀን ነው። ዓድዋ ጊዜ የማያልፍበት የክብርና የትብብር እርሾ ነው። አገርን የሚጠሉ ይህ እርሾ አይጥማቸውም። “ዓድዋ ስለምን የፍጽምናችን መጀመሪያና መጨረሻ አልሆነም?” እያሉ መብሰልሰል አገር የማስተዳደርን እና የታሪክን ውስብስብነት አሳንሶ ከመመልከት የሚመጣ ነው።(ታሪክና ባለታሪኮች አይመርመሩ ማለቴ አይደለም። ግን ሁሉ መርማሪና አስተማሪ አይሆንም።)

የአዝማቾቹ አውራ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ ለባለድል አዝማቾች የሚሰጠው ክብርና ውዳሴ ሁሉ የተገባው ነው። ዘማች ያለአዝማች ምንድን ነው ቢሉ በዕለት ረሃቡ የሚመራ ተራ የገበያ ሕዝብ ነው።

ቁርጠኛውና ታማኙ የዓድዋ ሠራዊት፣ ለባለድል ሠራዊት የሚሰጠው ክብርና ውዳሴ ሁሉ ይገባዋል። አዝማች ያለዘማች ምንድን ነው ቢሉ ብቻውን የሚቆዝም ጎልማሳ ነው።» ሲል ፅፏል።

ዓድዋን በንግሥናቸው የመሩት አፄ ምኒሊክ የሚሰጣቸው ዋጋ እና በጦርነቱ ውስጥ ያላቸው ሚና ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል። መርከብ ነጋሽ በፌስ ቡክ ያሰፈረው «ዓድዋ፣ ምኒሊክና የባህርበር!» የተሰኘ አጭር ፅሁፍ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ይመስላል።

«ምኒሊክ ከዓድዋ በኋላ ወደፊት ያልሄደውና ባሕር በር አልባ ሃገር ያደረገን፣ ከድል በኋላ ሞደሬሽን ስለሚያስፈልግ ነው ፣ሰራዊቱ የተዳከመ፣ የሚበላውን ያጣ ስለነበረና ከዛ ቢቀጥል የተገኘውን ድል አደጋ ላይ የሚጥል ሊሆን ስለሚችል ነው ወዘተ የሚል  መከራከርያ አለ። አይዋጥልኝም !እንደኔ እንደኔ የምኒሊክ ዓድዋ ላይ ማቆም፣ ከምኒሊክ ጠባይና ለባህርበር ካለው (ከነበረው) ዝቅተኛ ግምት የመነጨና አካባቢያዊ ፖለቲካን በደምብ ካለመረዳት የመጣ፣ ይህ በበኩሉ ምኒሊክ የሸዋ ንጉስ ስለነበረና ላንድ ፖወር ስለነበረ የመጣ ይመስለኛል። የምኒሊክን የክተት ጥሪ በማየት ብቻ ይህንን መገመት ይቻላል።»

በማህበራዊ ድረ-ገፆች በንጉሱ ላይ ከቀረቡት ትችቶች መካከል ጄኔራል ሸምሱ ቢረዳ «ኢትዮዽያ ውስጥ ውትድርና፤ግዳጅ እና አፈሳ የተጀመረው በምንሊክ ዘመን ነው።» የሚለው ይገኝበታል። ንጉሱ የባሪያ ንግድን በአዋጅ ማቆማቸውን ጠቅሰው የሚያሞግሷቸው የመኖራቸውን ያክል እራሳቸው በንግዱ ተሳትፈዋል የሚል ወቀሳም አለባቸው። በማሕበራዊ ድረ-ገፆች ለንጉሱ የሚቀርቡ ሙገሳዎችም ይሁኑ የሚሰነዘሩባቸው ወቀሳዎች የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የታሪክ አረዳድ ሰፊ ልዩነት ማሳያ ናቸው። የኢትዮጵያን አንድነት እና የዘውጌ ፖለቲካን የሚያቀነቅኑት ወገኖች ጥልቅ ልዩነት ከሚታይባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች መካከል የዓድዋ ድል እና የምኒሊክ ተክለ-ስብዕና ሁነኛ መገለጫዎች ናቸው።

ጦማሪው በፍቃዱ ኃይሉ ነፃነት አድዋ ነፃነት አድዋ (Bilisummaa adda-ዋ!) በሚል ርዕስ ያሰፈረው ፅሁፍ ከፍተኛ ውይይት ከካሔደባቸው መካከል ይገኝበታል። «ዳግማዊ ምኒልክ በዘመናቸው፣ በኢትዮጵያ ከነበሩት የተሻለ ብልኅ እና ኃያል ንጉሥ ነበሩ። የእርሳቸው ሕልም ከአያት ቅድም አያቶቻቸው የወረሱት ትልቅ ግዛት (empire) የመመሥረት ሕልም ነበር እንጂ ፅድቅን ማድረግ አልነበረም። ከሕልም አንፃር እንደርሳቸው የተሳካላቸው የለም።» የሚለው በፍቃዱ ንጉሱ «በታሪክ አጋጣሚ የዓድዋ ድል ባለቤት ሆነዋል።» ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።

120. Jahrestag der Schlacht von Adwa
ምስል Yared Sumete

በፍቃዱ «ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የሚባልላቸውን ያክል "እምዬ" አልነበሩም። ለንግሥናቸው ቀናተኛ ነበሩ። የተቃወሟቸው እና ያልገበሩላቸው ላይ የማያዳግም ርምጃ የሚወስድ ሠራዊት ይልኩ ነበር። ንጉሠ ነገሥትነትን ለመቆናጠጥ እና ለማጠናከር እየተጣደፉ ባለበት ወቅትም ነው ለአይቀሬው የዓድዋ ጦርነት ሰበብ የሆነውን የውጫሌ ውል ከነስህተቱ የፈረሙት። ከነመኳንንቶቻቸው ባሪያ አሳዳሪም ነበሩ። ባሪያ ንግድ ውስጥም ነበሩበት። ለባርነት ይሸጡ የነበሩበት ደግሞ የገዛ ዜጎቻቸውን ነበር።» ሲል አስተያየቱን ገልጧል። በእሱ አባባል «ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን ቀስ በቀስ የምናሸንፈው፣ የራሳችንን ጨቋኝ የመምረጥ ዕድል የሰጠን ዕድል ነው።» በፍቃዱ በዚህ የፌስ ቡክ አስተያየቱ በርካታ ትችቶች ቀርበውበታል።

እዚያው ፌስ ቡክ ላይ «በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የዳግማዊ አጼ ምኒሊክን ያክል ትልቅ ፕሮፖጋንዳ የተከፈተበት መሪ የለም።» የሚለው ዮና ብር ነው። «አጼ ምኒሊክ እንደ ማንኛውም የዘመናቸው ነገስታት አልገብር ያሏቸውን ሕዝቦች በሃይል አስገብረዋል። በዚህም የሃይል እርምጃ የተጎዱ ወገኖቻችን አሉ። ይሄንን ማንም ሊክድና ሊያስተባባል አይችልም።ሆኖም ግን አጼ ምኒሊክ በዘመናቸው ከነበሩ መሪዎች በጣም የተሻሉ ቅን፤ ግልጽ፤ ሩህሩህና አሳታፊ መሪ እንደነበሩ መካድ አለማወቅ ብቻ ነው። አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን በመመስረታቸውና ነጻነት ስለሰጡን እናከብራቸዋለን እንጂ የፈጸሙት ግፍ የለም ማለት አይደለም። በደንብ አለ። ግን ደግሞ እሳቸው ብቻ የተለየ ግፍ የፈጸሙ ይመስል ስማቸውን አትጥሩ ማለት እብደት ነው።»

የዓድዋ ድል 121ኛ ዓመት ሲከበር የዘመኑ ሐብቴ ዲነግዴን፤ባልቻ ሳፎ እና አሉላ አባ ነጋን የመሳሰሉ  የጦር አበጋዞች አብረው መነሳታቸው አልቀረም። የንግስት ጣይቱ ብጡል ፎቶ ግራፎች እና ንድፎች፤ከታሪካዊ መፃሕፍት እና ተውኔቶች የተቀነጨቡ ንግግሮች በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በብዛት ተሰራጭተዋል።

Logo der Mo Ibrahim Foundation

ከዓድዋ ተሻግረን በዶይቼ ቬለ የፌስ ቡክ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ ወዳደረግንው ውይይት ተሻግረናል። በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው በሰላም ሥልጣን ያስረከቡ አፍሪቃውያን መሪዎችን የሚሸልመው የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ዘንድሮም መስፈርቶቼን የሚያሟላ እጩ አላገኘሁም ብሏል። ጉዳዩን ለውይይት ወደ ፌስ ቡክ ወስደንው ነበር። የዶይቼ ቬለ አድማጮች እንዲሁም የማሕበራዊ ድረ-ገፅ ተከታታዮች ኃሳባቸውን አቀብለውናል።

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች የጋናው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ለዚህ ሽልማት ብቁ ናቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ኃሳባቸውን ገልጠዋል። ሌላ አድማጭ  «ጥቂት የአፍሪካ አገሮች ለምሳሌ እንዴ ጋና ያሉት በቅርቡ ሥልጣንን በህዝብ ፍላጎት በምርጫ በመልቀቅ በጎ ጅምር ቢያሳዩም ፤ አብዛኛዎቹ ሥልጣን ወይም ሞት በማለት እንዴ ሙጋቤ ከሞቱ በኃላ እንኳ ህዝቡ እሳቸውን ነው የሚመርጠው በሚባልበት አህጉር የሚሸለም መጥፋቱ አያስገርመኝም።» ብለውናል።

ጋሊብ ሀሰን ከአዲስ አበባ «ቢያንስ ቢያንስ የጋና መሪ የነበሩት በሰላማዊ መንገድ ስልጣናቸው አስረክበዋልኮ ሽልማቱ ይገባቸዋል።»

«ከአፍሪካ መሪዎች ውስጥ ምንአልባትም አሁን ባለው ዲሞክራሲያዊና ነፃ ምርጫ አካሂደው ሂደቱ ለመጀመር ጥረት ከሚያደርጉ መሪዎች ውስጥ የጠቀስን እንደሆነ የሶማሊያው ተመራጩ ፕሬዝደንት ሙሀመድ አብዱላህና እና የማሊው አዳማ ባሮ ይሆናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።» የሚሉ አስተያየቶች ደርሰውናል።

የስላቅ አስተያየቶችም አልጠፉም። የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እና ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝን የጠቆሙ አድማጮች አሉ። በነገራችን ላይ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስልጣን ላይ በመሆናቸው መዋዳደር አይችሉም።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ