1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ኅዳር 16 2009

«የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት» በሳምንቱ ውስጥ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ጎላ ብለው የወጡ መነጋገሪያ ርእሰ ጉዳዮች የሚተነተኑበት ዝግጅት ነው። በዝግጅቱ የተለያዩ ርእሰ-ጉዳዮች ተዳሰዋል።

https://p.dw.com/p/2TGNZ
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ጥንታዊ አዉሮፕላኖችን እያበረሩ የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራትን የሚጎበኙ አስራ-ሰባት አብራሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰራቸው የመዘገቡን ዜና በርካቶች ተቀባብለውታል። የአማራ ክልል የካቢኔ ሹም ሽር፤ ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪዎች ለግንባታ የሚውል ብረት ይዘው ተሰወሩ መባላቸው፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አመጽ አስነስተው እንደነበር መገለጡም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተነሱ ነጥቦች ነበሩ። የአማራ ክልል የካቢኔ ሹም ሽር እና በኢትዮጵያ አዲስ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ የሚሉት ጉዳዮች ደግሞ በስፋት መነጋገሪያ ሆነዋል።

ሲኖትራክ የተሰኙ 15 ከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ከነጫኗቸው የግንባታ ብረቶች ተሰወሩ መባሉ ብዙዎችን ፈገግ ያሰኘ የሰሞነኛው የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ርእስ ነበር።  ሶደሬ ቲዩብ  «ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል በ15 ሲኖትራኮች የተጫነ ብረት መጥፋቱ ተጠቆመ» በሚል ርእስ ሪፖርተር ያቀረበውን ጽሑፍ በትዊተር ገጹ አስነብቧል። 

 ኃላፊዎቹ «አልነበርንም አልሰማንም» ብለዋል ሲል የሚንደረደረው ጽሑፍ፦ «በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የገዛው በ15 ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች የተጫነ ብረት፣ ከነተሽከርካሪዎቹ መጥፋቱን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ» በማለት ይቀጥላል፡፡

«ኢንተርፕራይዙ እያስገነባቸው ለሚገኙት የ40/60 የቁጠባ ቤቶች መሥሪያ የሚውል፣ በሚሊዮኖች ብር የተገዛ ብረት አቃቂ በሚገኘው የዋናው ሳይት መጋዘን የሚያከማች ቢሆንም፣ በ15 ሲኖትራኮች የተጫነና መጠኑ ለጊዜው ያልታወቀ ብረት መጥፋቱን ምንጮች አስረድተዋል» የሚለው ጽሑፍ ወረድ ብሎ «ኅዳር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ መጋዘኑ የሄዱት ተሽከርካሪዎች ብረቱን ሳያወርዱ ወደ ሌላ ሳይቶች እንዲወስዱ በመጋዘኑ ኃላፊዎች መታዘዛቸውንና የመረካከቢያ ሰነድ ሳይለዋወጡ እንዳልቀሩ የገመቱት ምንጮች፣ በዕለቱ ወይም በማግሥቱ ማድረስ የነበረባቸው ቢሆንም የት እንደደረሱ አልታወቀም ብለዋል» እያለ ይቀጥላል። ጽሑፉ  በግንባታ ላይ ያላ ሕንፃ ምስልም ተካቶበታል። 

እሸቱ ሆማ ቄኖ በፌስቡክ ገጹ «ሲኖ ትራክ የሰው ነፍስ አጠፋ ነበር የምንሰማው፣ ዛሬ ደግሞ የግንባታ ብረት ይዞ መጥፋት ጀመረ» ሲል ጽፏል።

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ተቋም ትላንትና ባወጣዉ ዘገባ፤ በኢትዮጵያ ኤሌኞ ባስከተለዉ ከባድ ድርቅ ምክንያት በተከሰተዉ ከፍተኛ ጎርፍ፤ የጤና ችግር፣ የማኅበረሰቡ መሰረታዊ አገልግሎቶች መቃወሱ በ9,7 ሚሊዮን ነዋሪዎች ላይ የደረሰዉ አሉታዊ ተፅኖዉ መቀጠሉን አስታዉቀዋል።

Soziale Netzwerke
ምስል imago/Schöning

ድርጅቱ በመግለጫዉ በቀጣይ በሃገሪቱ አዲስ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ባላፈዉ ሳምንት ባወጣዉ መግለጫ ማስጠንቀቁ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ የርዳታ ድርጅቶች ችግሩን ለመቅረፍ ምን ማድረግ አለባቸዉ ይላሉ? አስተያየታችሁን አጋሩን ስንል በዶይቸ  ቬለ የአማርኛው ክፍል የፌስቡክ ገጽ ላቀረብነው ጽሑፍ በርካታ ተከታዮቻችን አስተያየት ሰጥተውበታል።

እዮብ እዮብ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፦ «የልማት መንግስታችን በክርምት በክረምት ችግኝ ይዞ በቴሌቪዢን ብቅ ለማለት ብቻ ነው የታደለው ሠርቶ የማሠራት ብቃት የላቸውም ወሬ ብቻ ናቸው። ለዛነው ድርቁ የተደጋገመው» ሲሉ አስነብቧል።

ኪዳኔ ወልደገብርኤል ደግሞ፦ «ወሬው ውሃ ኣይቃጥርም» ሲሉ አጠር ያለ አስተያየት ሰጥቷል። ማኅሌት አድማሱ በበኩሏ፦ «እያነቡ እስክስታ የሚለውን ዘፈን ለኢህአዴግ ጋብዙልኝ» ሲሉ በተመሳሳይ አጠር ያለ ጽሑፍ አስፍራለች። ኢትዮጵያ ትቅደም ደግሞ፦ «የበኩላችሁን ተወጡ እናንተም እንላለን ለወገን ደራሽ ወገን ነውና» ብሏል።

ዮሐንስ ሞላ በጌስቡክ ገጹ፦« ‘ገዱ አንዳርጋቸው የክልሉ ምክር ቤት ላይ ባደረገው ንግግር በትግራዮች ላይ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን በግልጽ አመነ፡፡ ይቅርታ ጠየቀ፡፡’ይላል ዳንኤል ብርሃኔ» ሲል ያሰፈረው ጽሑፍ ወረድ ሲል እንዲህ ይነበባል፦ «ዕለት ዕለት፣ በንግግር እና በተግባር፥ በሰው ልጆች (ኢትዮጵያውያን) ዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽመው መንግስት ወገን ሁኖ፤ ገዱን፥ የመንግስትን ሌላ ወኪል እያጣቀሰ። ኧረ ተዉ ተናግራችሁ አታናግሩን!» በማለት ይጠናቀቃል።

ከዮሐንስ ጽሑፍ ስር የሰፈረው የኢዮብ ብርሃነ አስተያየት፦ «ቤኔሻንጉል እና ዲላ የተፈጸሙት ወንጀሎች ለዛውም ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ቤተክርስቲያን እና መስጊድ ሁሉ በእሳት የነደደባቸውንስ ማን ያስታውሳቸው ?የጉድ አገር!!!» ሲል ይነበባል።

ከበደ ካሳ በፌስቡክ ገጹ «የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት እያደረገ ባለው የአማራ ክልልን ካቢኔን እንደ አዲስ የማዋቀር ሂደት በአዲስ የቀረቡ 12 የካቢኔ አባላት የሚከተሉት ናቸው» ሲል ስም  ዝርዝራቸውን አስፍሯል።

ሜጀር ጀረናል ሸምሱ ቢረዳ ፒኤችዲ የተሰኘው የትዊተር ተጠቃሚ «የአማራ ክልል ካቢኔ ተበወዘ። # የሀገር ውስጥዜና» ሲል ጽፏል።

Symbolbild Jobsuche Social Media
ምስል Fotolia/Foto-Ruhrgebiet

በቀለ ማርኮ በትዊተር ገጹ፦ «ጅማ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች ተቃውሞ ስትናጥ አደረች » የሚል ጽሁፍ አስነብቧል። «ኢትዮጵያ፤ በቂሊንጦ እስር ለሕይወት መጥፋት ምክንያት በሆነው የእሳት ቃጠሎ  እስረኞች ተከሰሱ» ሲል ቢቢሲ በድረ-ገጹ ያስነበበው ዜና በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተንሸራሽሯል።

በነሐሴ ወር ማብቂያ ላይ በቂሊንጦ እስር ቤት ለተነሳው እሳት 38 የቂሊንጦ እስረኞች ተጠያቂ  ተብለው መከሰሳቸውን ጽሑፉ ያስነብባል። «በነሐሴ መገባደጃ እስር ቤቱ ላይ  እሳቱን በትክክል ምን እንዳስነሳው የሚገልጥ ዝርዝር ማብራሪያ በቀላሉ የማይገኝ ሆኖ ቀይቷል» ሲልም ቢቢሲ አክሏል። 

ጥንታዊ አዉሮፕላኖችን እያበረሩ የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራትን የሚጎበኙ አስራ-ሰባት አብራሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የመታሰራቸው ዜና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙዎች ተቀባብለውታል።

ዘ ጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ በድረ-ገጹ ያስነበበው ዜና አብራሪዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የተያዙት ‘ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ በመግባታቸው ነው’ ሲሉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መናገራቸውንም አክሎ ዘግቧል።  ጋዜጣው ዘግየት ብሎ አብራሪዎቹ መለቀቃቸውን አትቷል።

ጋዜጠኛ ደረጄ ሐብተወልድ በትዊተር ገጹ፦ ውድድር ላይ የነበሩ ሚጢጢዬ አውሮፕላኖችን አግተው- ልክ እሳት የሚተፋ የጦር አውሮፕላን እንዳገቱ ይፎክሩብናል እንዴ?! ተራሮችን ያንቀጥቀጠ ትውልድ የተጻፈውም እንዲሁ ነው»  ሲል አስነብቧል።

የሱዳኑ አማጺያን መሪ ሪይክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ከአየር ማረፊያ ተመለሱ የሚለው ዜናም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ