የማሕበራዊ ዕድገት ሁኔታ በኢትዮጵያ
ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2005ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ማሳየቷ ቢነገርም በመረጃው ላይ ዘንድሮም በዝቅተኛው ቦታ ነው የሰፈረችው። የኤኮኖሚው ዕድገት ጭብጥ በሆነ ማሕበራዊ ዕርምጃ በሚገባ አልተንጸባረቀም ማለት ነው። ዘገባው ኢትዮጵያ ከ 187 ሃገራት መካከል በ 173ኛው ቦታ ላይ እንደምትገኝ ያመለክታል።
እርግጥ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ገቢር መሆን ከጀመረበት ከ 2000 ዓ-ም ወዲህ ቢቀር በሶሥት ግቦች በጤና ጥበቃ፣ በትምሕርትና የሕጻናትን ሞት መጠን በመቀነስ ረገድ ጠቃሚ ዕርምጃ እንዳደረገች በምዕራቡ ዓለም ጭምር በየጊዜው ሲነገር ነው የቆየው።
ይሁንና ዓመታዊው ዘገባ እንዳመለከተው አገሪቱ በማሕበራዊው ልማት ዝርዝር ላይ አሁንም በዝቅተኛው ቦታ መገኘቷ፤ በሌላ አነጋገር አገሪቱ አሁንም የድሃ ድሃ ከሚባሉት የመጨረሻ ሃያ ሃገራት ተርታ እንዳለች መቀጠሏ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሣ ነው። ኢትዮጵያ ለነገሩ ባለፉት ዓመታት ከምዕራቡ ዓለም በቢሊዮን የሚቆጠር ከፍተኛ የገንዘብ ዕርዳታ ከሚያገኙት ቀደምት ሃገራት አንዷ ሆና ቆይታለች።ይህም ሆኖ ግን ከሶሥት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ዛሬም በውጭ የምግብ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ሲሆን የሚሌኒየሙ ግቦች ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ባሻገር በተለይም ድህነትን በግማሽ በመቀነሱ ረገድ የጊዜ ገደቡን ጠብቆ ቢቀር የተቃረበ ውጤት እንኳ ማሣየቱ የሚያጠያይቅ ነው።
በነገራችን ላይ የማሕበራዊው ልማት ዘገባ በታዳጊው ዓለም በአጠቃላይ መሻሻል መታየቱን ሲያረጋግጥ ችግሩ እንዳለ ከቀጠለባቸው 25 ሃገራት 24ቱ አፍሪቃ ውስጥ እንደሚገኙም አመልክቷል። ለማሕበራዊው ልማት መሻሻል ሁል-አቀፍ የሆነ ሰፊ ሕብረተሰባዊ ዕርምጃ አስፈላጊ ሲሆን የኤኮኖሚ ዕድገትን ወደ ማሕበራዊ ዕርምጃ መለወጥና የኤኮኖሚ ብቃትን ማዳበር መቻሉም አንዱና ዋነኛው ቅድመ-ግዴታ ነው።World Economic Forum የተሰኘው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ባለፈው ሣምንት ማብቂያ የ 2012/13 ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ብቃት፤ የምርታማነት ዘገባውን ሲያቀርብ ኢትዮጵያ እዚህም ከ 143 ሃገራት 121ኛ ሆና ነው የተቀመጠችው። በአፍሪቃ ውስጥ ደግሞ ከ 37 ሃገራት መካከል 22ኛውን ቦታ ይዛለች።
ለግንዛቤ ያህል ዘገባው ደቡብ አፍሪቃን፣ ሞሪሺየስንና ሩዋንዳን በአፍሪቃ ቀደምት ሲያደርግ የመጨረሻውን ቦታ የያዙት ቻድ፣ ጊኒና ሢያራ ሌዎን ናቸው። እንግዲህ የኤኮኖሚ ብቃት ወይም አቅም ግምቢያውም ብዙ መሻሻልን የሚጠይቅ መሆኑ አልቀረም። ይህ በተለይ በዝግጅታችን ሁለተኛ ክፍል በሰፊው የምናተኩርበት ጉዳይ ይሆናል። ለዛሬው የኢትዮጵያን ማሕበራዊ ልማትና የኤኮኖሚ ይዞታ በተመለከተ በዚህ በጀርመን የአፍሪቃ የሰላምና የምጣኔ-ሃብት ዕድገት አማካሪ የሆኑትን የኤኮኖሚ ምሁር ዶር/ፈቃደ በቀለን አነጋግሪያለሁ፤ ያድምጡ!
መሥፍን መኮንን
ተክሌ የኋላ