1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማላዊ ሴቶች እና በሀገራቸው የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅር ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ጥ

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 1 1995

የአፍሪቃ ሴቶች በየሀገሮቻቸው የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅር ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከሀገር ሀገር ይለያያል። ሴይሼልስን በመሳሰሉ ሀገሮች ውስጥ በምክር ቤትና በመንግሥቱ ካቢኔ ውስጥ የሴቶቹ ተሳትፎ ከፍ ያለ ሲሆን፡ ማላዊ ውስጥ አሀዙ ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም፡ የማላዊ ፕሬዚደንት ባኪሊ ሙሉዚ ይህንኑ ሁኔታ ለመቀየር አንድ ጥረት አንቀሳቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/E0lR

የፆታ እኩልነት ሴቶች በምክር ቤት እና በመንግሥት የሥልጣን ቦታዎች ውስጥ ትክክለኛ ውክልና ፡ እንዲሁም በሁሉም የኑሮ ዘርፍ ላይ እኩል ዕድል በሚያገኙበት አሠራር ገሀድ መሆን ያለበት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው። የማላዊ ሴቶች በሀገራቸው ፖለቲካ ያላቸውን ንዑሱን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ትግላቸውን እንዲያጠናክሩ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ባኪሊ ሙሉዚ በየጊዜው ቢያበረታቱም፡ የማላዊ ብሔራዊ ሸንጎ አሁንም የወንዶች ተፅዕኖ የበዛበት አካል ሆኖ ነው የሚገኘው፤ የምክር ቤቱ እንደራሴዎች የማላዊ ርዕሰ ብሔር ለብሔራዊው ሸንጎ የተወሰኑ እንደራሴዎችን፡ ሴቶችን ጭምር መሠየም የሚያስችላቸውን መብት ካልሰጣቸው በስተቀር ይኸው ሁኔታ ወደፊትም እንደማይቀየር ነው ሙሉዚ ሳይታክቱ ለማስረዳት የሚሞክሩት። ምክር ቤቱ ሴቶች በሀገራቸው ፖለቲካ ላይ ተጨማሪ ሚና የሚጫወቱበትን ዕድል የመስጠቱን ጉዳይ በጥሞና ቢያስብበት የተሻለ መሆኑን ካላፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ ከፕሬዚደንቱ ጽሕፈት ቤት ኣካባቢ አስተያየት ይሰማል።

በምሕፃሩ፡ ሳድክ በመባል በሚታወቀው፡ የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ትብብር ድርጅት ሌሎች አባል ሀገሮች አንፃር፡ የማላዊ ሕግ፡ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔሩ አንዳንድ የምክር ቤት እንደራሴዎችን የሚሠይሙበትን መብት እንደማይሰጥ ፕሬዚደንት ሙሉዚ ባኪሊ በማስታወቅ፡ ይህን መብት የሚያገኙበት ሂደት በብሔራዊው ሸንጎ ውስጥ ያለውን የሴቶቹን እንደራሴዎች አሀዝ ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳቸው አስረድተዋል። ታንዛንያ፡ ዩጋንዳ፡ ዛምቢያ እና ዚምባብዌን የመሳሰሉ የሳድክ ሀገሮች፡ ርዕሳነ ብሔር ሀያ ከመቶ የብሔራዊ ሸንጎዎችን እንደራሴዎች የሚሠይሙበት ሕግ እንዳላቸው ነው የማላዊን ሴቶች በውሳኔ አሰጣጡ መዋቅር በይበልጥ ለማሳተፍ ጥረት የጀመሩት ባኪሊ የገለፁት።

የማላዊ ምክር ቤት፡ ፕሬዚደንቱ ሴቶች ተጨማሪ ሥልጣን የሚይዙበትን መብት እንዲሰጣቸው ሙሉዚ ከብዙ ዓመታት ወዲህ የጀመሩትን ጥረታቸውን እስካሁን እንዳከሸፈባቸው በመግለፅ ወቅሰዋል። ሙሉዚ አንዳንድ የምክር ቤት እንደራሴዎችን መሠየም የሚችሉበት ዕድል የማላዊ ሴቶች በወንዶቹ አቻዎቻቸው የተጨቆኑበትን ሁኔታ ለማብቃት እንደሚረዳ በርግጠኝነት ይናገራሉ። ርዕሰ ብሔሩ ይህን መብት ያገኙ ዘንድ በማላዊ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር፡ ሴቶቹ ራሳቸው በፖለቲካው እና በሌሎች የሀገሪቱ የኑሮ ዘርፎች ላይ መብታቸውን ለማስከበር ከወንዶቹ አቻዎቻቸው ጋር እኩል መታገል እንዳለባቸው ሙሉዚ ከማሳሰብ አልቦዘኑም። የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት መሪዎች እአአ እስከ 2005 ዓም ድረስ በሳድክ አባል ሀገሮች ብሔራዊ ሸንጎዎች ውስጥ ያለውን የሴቶችን ተሳትፎ ቢያንስ ወደ ሠላሣ ከመቶ ለማሳደግ ቃል ገብተዋል። መሪዎቹ እአአ በ 1997 ዓም በማላዊ መዲና ብላንታይ ባካሄዱት ጉባዔ ላይ ያካባቢውን ሴቶች ለአድልዎና ለጭቆና የሚዳርጉትን ማኅበራዊ ባህልና ዕድር፡ እንዲሁም ሕጎችን በጠቅላላ ለማስወገድ እና በሀገሮቻቸው ሕገ መንግሥትም ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ነው ግዴታ የገቡት። በመሆኑም፡ ማላዊ ይህንኑ የሳድክ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት እንድታደርግ፡ ካልሆነ ግን የማላዊ ሴቶች ውክልና ወደፊትም ዝቅተኛ ሆኖ እንደሚቀር ነው ፕሬዚደንት ሙሉዚ ያስጠነቀቁት። የማላዊ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ላቭነስ ጎንድዌ የሙሉዚን ጥረት በመደገፍ፡ የብሔራዊው ሸንጎ አባላት ስለዚሁ ጉዳይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለሴቶች መብት ከሚታገሉ ቡድኖች ጋር በመምከር፡ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር የጠየቁትን አንዳንድ እንደራሴዎች መሠየም የሚችሉበትን መብት እንዲሰጡዋቸው የበኩላቸውን ጥሪ አሰምተዋል። ሴቶች ከማላዊ አሥራ አንድ ሚልዮን ሕዝብ መካከል ሀምሳ ሁለት ከመቶውን ቢሸፍኑም እንኳን፡ ባህልና ዕድር ከፍተኛ ተፅዕኖ በበዛባት የማላዊ ምክር ቤት ውስጥ ካሉት እድ መቶ ሰባ ሰባት መንበሮች መካከል አሥራ ሰባቱ ብቻ ናቸው በሴቶች የተያዙት።

የማላዊ ፕሬዚደንት የሀገራቸውን ሴቶች በውሳኔ አሰጣጥ አውታሮች ያለቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት በያዙበት በዚሁ ወቅት፡ የሳድክ ጽሕፈት ቤት ሴቶች መብታቸውን በማስከበሩ ረገድ አሁንም ገና ብዙ ትግል በሚጠብቃቸው በዚሁ አካባቢ አንድ የፆታ እኩልነት ፖሊሲ የማውጣት ሂደት አነቃቅቶዋል። ከጥቂት ጊዜ በፊት የሳድክ አባል ሀገራት መሪዎች በታንዛንያ ባካሄዱት ዓቢይ ጉባዔ ላይ የሴቶቹን መብት ለማስከበር እአአ በ 1997 ዓም የገቡትን ቃል ምን ያህል ተግባራዊ እንዳደረጉ አንድ ዘገባ ቀርቦላቸዋል። በዘገባው መሠረት፡ አንዳንድ ሀገሮች የሴቶችን በምክር ቤትና በመንግሥት ውክልና ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ሳድክ ያስቀመጠውን ዓላማ ገሀድ በማድረግ ላይ መሆናቸውን፡ ሌሎች ደግሞ አሁንም ከዚሁ ዓላማ እጅግ ርቀው እንደሚገኙ የሳድክ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ፕሬጋ ራምሳሚ አስረድተዋል። ይሁንና፡ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት ከነበረው ዝቅተኛውና ተስፋ አስቆራጩ የሴቶች ተሳትፎ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር የሳድክ አባል ሀገሮች የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ በወቅቱ ያንቀሳቀሱዋቸው በርካታ ርምጃዎች የሚሞገሱ መሆናቸውን ዶክተር ራምሳሚ ሳይገልፁ አላለፉም። ሴቶች በሀገሮቻቸው የውሳኔ አሰጣጥ አሠራር ውስጥ የያዙትን ተሳትፎ በማስተካከሉ ረገድ ደቡብ አፍሪቃ፡ ሴይሼልስ እና ሞዛምቢክ ደህና ውጤት ሲያሳዩ፡ አሥራ ስምንት ከመቶ ሴቶች የምክር ቤት እንደራሴዎች ብቻ ያሉዋት ቦትስዋናን፡ ታንዛንያን እና ዛምቢያን የመሳሰሉ ሀገሮች ግን የሳድክ አባል መንግሥታት መሪዎች የሴቶችን ተሳትፎ እአአ በ 2005 ዓም ድረስ ወደ ሠላሣ ከመቶ ለማሳደግ የደረሱትን ስምምነት ገሀድ ማድረግ መቻላቸው እጅግ አጠራጣሪ ነው።