1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊ ምርጫ፤ ደስታና ቁጣ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 2005

በማሊዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ የሚሳካላቸዉ ይመስላል። የእሁዱ ምርጫ መነሻ ዉጤት የሚያመለክተዉም ይህንን ነዉ። የሆነ ሆኖ ኬይታ በምርጫዉ ያገኙት የድምጽ መጠን ገና አልተረጋገጠም። የዶቼ ቬለዋ ካትሪን ጌንዝለር እንደዘገበችዉ ግን የማሊ የፖለቲካ ተቃዋሚ ወገን በዚህ አልተደሰተም።

https://p.dw.com/p/19HtS
ምስል DW/K.Gänsler

ባማኮ ዉስጥ ፈንጠዝያዉ ከወዲሁ ጀምሯል። ሰኞ ማምሻዉን ጎዳናዉን የሞሉት የማሊ ወጣቶች የፕሬዝደንታዊ እጩ ተፎካካሪ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ ምስል በመያዝ IBK እያሉ ሲጨፍሩ ተደምጠዋል። IBK የፕሬዝደንታዊዉ እጩ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ ስም ምህጻር ነዉ። እሳቸዉም እሁድ ዕለት ድምጻቸዉን ከሰጡ ዜጎች የ50 በመቶዉን ማሰባሰብ መቻላቸው ተነግሯል። የአገር አስተዳደር ሚኒስትሩ ኮሎኔል ሙሳ ሲንኮ ኩሊባሊ ሰኞ አመሻሹ ላይ ይህን የሚጠቁመዉን የመነሻ የምርጫ ዉጤት ይፋ አደረጉ፤
«ከወዲሁ አንድ ነገር እየታየ ነዉ፤ ሌሎች ተወዳዳሪዎችን በከፍተኛ ብልጫ እየመሩ የሚገኙ እጩ ተወዳዳሪ አሉ፤ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ። የሚታየዉ ልዩነት መዝለቁ ወሳኝ ነዉ። እንዲያ ከሆነም ለእሁዱ ምርጫ የመለያ ምርጫ አያስፈልግም ማለት ነዉ።»

Mali Präsidentschaftswahl 30./31. Juli
ምስል DW/K.Gänsler


ከዚህ መግለጫ በኋላ ለኢብራሂም ቡባከር ኬይታ ደጋፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ አላስፈለገም። ለእነሱ የሚደግፏቸዉ እጩ ተወዳዳሪ IBK የማሊ ፕሬዝደንት ለመሆን አሸንፈዋል። ሆኖም ግን የመነሻ ዉጤቱ ሲገለጽ ቁጥር ባለመጠቀሱ ጉዳዩ ገና አሻሚ እንደሆነ ነዉ። ኩሊባሊ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማን እንደሚመራ ከመጠቆም በቀር በምን ያህል ድምፅ የሚለዉን ቢጠየቁም ቁጥር አልጠቀሱም።
«እሳቸዉ ተወዳዳሪዎቻቸዉን በከፍተኛ ድምፅ እየመሩ መሆናቸዉን ተናግሬያለሁ፤ ዉጤቱን ነገ ይፋ እናደርጋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»
ይህ የኮሎኔሉ አገላለጽ ደግሞ በፈንጠዝያ ከተሞላዉ የባማኮ ጎዳና በተቃራኒ ጥርጥር አስከተለ፤ በተለይም በተቃዋሚዎች አካባቢ። የእሁዱ ምርጫ አብቅቶ የምርጫ ጣቢያዎች እንደተዘጉ ነዉ ይህ መግለጫ የተሰጠዉ። ወዲያዉ ደግሞ አንድ የአገር ዉስጥ ራዲዮ IBK የብዙሃኑን ድምፅ ማግኘታቸዉን ተናገረ። ወሬዉም ተዛመተ፤ ሆኖም ሁሉም እጩ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ዉጤቱ ተጠቃሎ ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ አስተያየት መስጠትን አልፈለጉም። የተቃዋሚዉ ወገን ደጋፊዎች ቁጣ ጋለ። ኢና ማይጋ ከሶሚላ ሲሴ የምርጫ ቅስቀሳ ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ቆማለች። የምትደግፋቸዉ እጩ ተወዳዳሪ ያገኙትን ነጥብ ለመስማት ብትመኝም ባለስልጣኑ ቁጥሩን አለመጥቀሳቸዉ ችግር ያስከትላል ባይ ናት፤
«በሆነዉ ነገር እኛ በምንም መንገድ አንስማማም። አንድ ሚኒስትር ዉጤቱን ገለጹ። የተገኘዉን ድምፅ በመቶኛ እንዲገልጹልን ጠይቀናቸዉ ነበር። ግን አልገለጹም። በእዉነት ይህ ሃቅ ነዉ። ችግር ያስከትላል።»
አሁን የማሊ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዉጤት የአገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ ሊወስን ይላል የሚል ግምት አለ። ካለፈዉ ዓመት መጋቢት ወር ማለቂያዉ መፈንቅለ መንግስት በኋላ በዚያ ላይ ሰሜናዊ ማሊ በሙስሊም ሚሊሺያዎችና አዛዋድ በተሰኘዉ ቡድን ቁጥጥር ሥር ለወራት ከቆየ ወዲህ የተካሄደ የመጀመሪያው ነዉ። በዚህ ምክንያትም ወደዴሞክራሲ ለሚደረገዉ ጉዞ ወሳኝ ርምጃ ተደርጎ ነዉ የተወሰደዉ። በችኮላ የተገለጸው የምርጫ ዉጤት ሁኔታዉን ሊያበላሽ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል የአፍሪቃ ብሄራዊ ዴሞክራሲ ተቋም ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ፎሙንዮ ያመለክታሉ፤
«ለማሊያዉያን የሚበጀዉ የምርጫ ግልፅነት ነዉ።
የምርጫዉ አካሄድ ግልጽ ተዓማኒ እና ሚዛናዊ ከሆነ ዉጤቱም ተቀባይ ይኖረዋል፤ ውጤቱ የሆነውም ቢሆን። ነገር ግን ስርዓቱን ባለማክበር አስቀድሞ አሸናፊነቱን የሚያዉጅበት ሁኔታ ካለ ማሊያዉያን ተነስተዉ ቁጣቸዉን መግለጻቸዉ አይቀርም።»

Ibrahim Boubacar Keita Präsidentschaftskandidat in Mali
ኢብራሂም ቡባከር ኬይታምስል Reuters/Adama Diarra


በምርጫዉ ድምጿን የሰጠችዉ ኢና ማይጋ ይህንኑ ታጠናክራለች። እስካሁን የሚነገረዉን የምርጫ ዉጤት በምንም መልኩ አንቀበለዉምም ባይ ናት።
«በምንም መንገድ በዚህ አንስማማም። ለተቃዉሞ ሰልፍ መዉጣት ካለብንም፤ ያንን እናደርጋለን።»
እንደ እሷ ከሆነም የምትደግፋቸዉ እጩ ተወዳዳሪ ሙማይ ሲሴ ለዳግም ምርጫ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ይህን ደግሞ ራሳቸዉ ሲሴ የመጀመሪያዉ የምርጫ ዉጤት ይፋ ከመሆኑ አስቀድመዉ በስልት ግልጽ አድርገዋል።
«ከ1984ዓ,ም አንስተን የዚችን አገር ፖለቲካና ፖለቲካ ኃይሎች እናዉቃቸዋለን። ዛሬም ዳግም ምርጫ መካሄዱ አስፈላጊ ነዉ ። አይቀርምም።»
የቀድሞዉ የማሊ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢብራሂም ቡባከር ከይታ ዘገባዎች እንደሚሉት አሁንም በተሻለ የመሪነት አብላጫ ድምጽ እንደያዙ ነዉ። ተቃዋሚዎቻቸዉ ምርጫዉ ካልተደገመ በቀር ዉጤቱን ሊቀበሉት እንደማይችሉ እየገለጹ ነዉ። ዉጤቱ ዛሬ ይሰማል ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ። ምርጫዉ በሰላማዊ ሁኔታ እና በከፍተኛ የመራጮች ተሳትፎ መከናወኑ በታዛቢዎች ቢወደስም በታጣቂዎች ዉጊያ፤ ብሎም በመፈንቅለ መንግስት ስትዳከም ለቆየችዉ አገርና ህዝብ ነገ ምን እንደደገሰ እየተጠበቀ ነዉ።

ካትሪን ጌንዝለር

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ